2023-05-08 21:35:12
#ግንቦትና_ልደት_መርገምና_በረከት
@zemarian
#ክፍል ፪
#ግንቦት
• ኢዮብ የተወለደበት
• እመቤታችን የተወለደችበት
• ጌታ ያረገበት
• መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት ላይ የወረደበት ወር ነው፡፡
ግንቦት በጥንት ዘመን የሚፈራ ወር ነበር፤ በብዛትም በዚህ ወር ሠርግ አይደረግበትም ነበር፤ ዋናው ምክንያት ደግሞ ኢዮብ የተወለደበት ወር በመሆኑ ነው፡፡ ከልደተ ኢዮብ ጋር ምን አገናኘው? ቢሉ ኢዮብ የተወለደበትን ቀን እንዲህ ብሎ ረግሞታል፦
"""" ከዚያም በኋላ ኢዮብ አፉን ከፍቶ የተወለደበትን ቀን ረገመ።
ያ የተወለድሁበት ቀን ይጥፋ፥
ያም ወንድ ልጅ ተፀነሰ የተባለበት ሌሊት።
ያ ቀን ጨለማ ይሁን፤
እግዚአብሔር ከላይ አይመልከተው፥ ብርሃንም አይብራበት።
ከቀኖች መካከል ደስ አይበለው፤ በዓመቱ በወሮች ውስጥ ገብቶ አይቈጠር።
እነሆ፥ ያ ሌሊት መካን ይሁን፤ እልልታ አይግባበት። """"" ኢዮ 3፡1-7፡፡
በማለት ረግሞታል፡፡ ይህ ወር ሰይጣን ጻድቃንን የከሰሰበት፤ ኢዮብን የፈተነበት ወር ነበር፤ (ኢዮ 2፡1-10)፤ በአንፃሩ የሰይጣን ወዳጆች ራሱን ሰይጣንን የሚጠሩበት ለሰይጣን መሥዋዕት የሚያቀርቡበት ወር ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት የጥንት ሰዎች ሩቅ መንገድ መጓዝ፤ ጋብቻ መፈጸም የመሳሰሉ ትልልቅ ጉዳዮችን አያከናውኑ ነበር፤ ወሩ ሰይጣን የሚሰለጥንበ ነው ተብሎ ስለሚታሰብ፡ ይህ ልማድ በብሉይ ኪዳን ነበር፡፡ እግዚአብሔር ቸር ነውና የዚህን ወር ርግማን ወደ በረከት ይቀይረው ዘንድ በዚህ ወር #ሦስት ታላላቅ ነገሮችን አከናወነበት፡፡
1. #ልደተ_ማርያም፦
እመቤታችን የተፀነሰችው ነሐሴ ሰባት ቀን ሲሆን የተወለደችው ግንቦት አንድ ቀን ነው፡ የእመቤታችን ልደት የመዳናችን ዋና መሠረት ነው፤ እርሷ ካልተወለደ ክርስቶስ በሥጋ አይወለድም፤ እርሱ በሥጋ ካልተወለደ ቤዛ የሚሆነን ዘመድ አይኖረንም ነበር፤ ቅዱስ ያሬድ " ከመ ትቤዙ ነቢያተ ወጻድቃነ.." (ለነቢያትና ለጻድቃን ቤዛ ትሆን ዘንድ (ክርስቶስን በመውለድ)) ብሎ ተናግሯል፤ የዕለቱ ምልጣን፡፡፡፡ የእመቤታችን ልደት የእውነተኛው ፀሐይ ክርስቶስ ልደት እስኪገለጥ ድረስ ሌሊቱን እንደ ጨረቃ እያበራ ያቆየን ተስፋች ነበር፡፡ እመቤታችን በራእዬ ቴክታ በጨረቃ የተመሰለችውም ይህንን ምሥጢር ያሳያል፡፡
• ኢዮብ የተወለደበት ይህ ወር እንዲጎድል ተረግሞ ነበር እመቤታችን ግን ሙሉ ጨረቃ ሆና እያበራች ወሩን ሙሉ (30) አደረገችው፡፡
• የኢዮብ ጨረቃ 29 ቀን ብቻ የምታበራ 1 ቀን ያጨለመች ናት (ኢዮብ ማለት ጨረቃ አበባ ማለት ነው) እመቤታችን ግን ሶልያና ተብላ 30ውን ሌሊት ሙሉ ያበራች ሙሉ ጨረቃ ናት (ሶልያና ማለት ሙሉ ጨረቃ ማለት ነው፤ የጨለመብንን ሌሊት ታብራልን!)
• ኢዮብ የተወለደበትን ቀን ጨለማ እንዲሆን ብርሃን እንዳይኖርበት የረገመውን ቀን ድንግል "የብርሃን እናት" ሆና ተወለደችበት፤ ቅዱስ ያሬድ "ዮም ተወልደት እመ ብርሃን ማለቱም ለዚህ ነበር፡፡
• ኢዮብ የተወለደበትን ቀን "እልልታ አይደረግበት" ብሎ ረግሞት ነበር እመቤታችን ስትወለድ ግን እርግማኑ ተሻረ፤ ፍጥረት ሁሉ "እልል.." አለ፤ የሊባኖስ ተራሮች ብሥራተ ልደቷን ተናገሩ፤ እናት አባቷ እልል አሉ፤ እኛም ከቅዱስ ያሬድ አሁንም " ዮም ፍሥሐ ኮነ በእንተ ልደታ ለማርያም" እያልን እልል...... እንላለን፡፡
• ኢዮብ የተወለደበትን ከቀኖች ተለይቶ ቀን መካን ይሁን ብሎ ቢረግመው "ድንግል እልፍ ሆና" ተወለደችበት፤
"መልአት ምድረ ወሰማያተ ወሊዳ ዋሕደ ወተወሊዳ አሐተ ፤ መልአት ምድረ ወሰማያተ" እንዳለ ባለቅኔ (አንድ ሆና ተወልዳ፣ አንድ ብቻ ወልዳ ሰማዩን ምድሩን ሞላችው)፡፡፡
• ክርስቶስ አዳምን የረገመበትን ዕለተ ዓርብ ተሰቅሎበት መርገምን ሽሮ ዓርብን ቅዱስ ቀን እንዳደረገው ሁሉ እመቤታችንም ኢዮብ ተወልዶ የረገመውን ወር ተወልዳበት ባረከችልን!!!
• ድንግል ሆይ ልደትሽ በረከታችን ነው!!!
• ድንግል ሆይ የልደትሽ ቀን ሙላታችን ነው!!!
2. #ዕርገተ_ክርስቶስ፦
ጥንተ ዕርገት ግንቦት 8 ቀን ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን ሰይጣን እስከ ሶስተኛው ሰማይ ድረስ ሄዶ ሰዎችን የመክሰስ ሥልጣን ነበረው፤ አሁን ግን አይችልም! ከምድር እስከ ሰማይ ድረስ በደመ ክርስቶስ ማኅተም ተዘጋ፤ ወደላይ የሚወጡት ክርስቶስና መላእክት፤ ክርስቶሳውያን ብቻ ናቸው፡፡ ከሳሽነት ቀረ፤ አዳም ነጻ ወጣ፤ መንገድ ሁሉ ተባረከ!! ጌታችን ሲያርግ እጆቹን አመሳቅሎ እየባረከን ነበር!!! እየባረከ እንደባረከን የሰይጣንን ክስ አስቀርቶ በአባቱ ቀኝ ተቀመጠ!!! እንጠራለን እንጂ አንከሰስም! በዚህ ወር እስከ ሶስተኛው ሰማይ የወጣው ሰይጣን በዚህ ወር ተባረረ!!!
3. #ልደተ_ቤተ_ክርስቲያን (ርደተ ጰራቅሊጦስ)፦
መንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያት የወረደላቸው በዚህ ወር (ግንቦት 18) ነበር፡፡ ይህ ልደተ ቤተ ክርስቲያን እርግጥ የሆነበት ከ 3000 ሕዝብ በላይ የተጠመቀበት ዕለት ነበር፡፡ ኢዮብ መካን (መኻን) እንዲሆን የረገመውን ቀን መንፈስ ቅዱስ ባርኮት እልፍ አእላፍ ሆነን ተወለድንበት!!!!
#ይህን_ያደረገ_አምላካችን_የተመሰገነ_ይሁን!!!
#የእመቤታችን_የልደቷ_በረከት_ይደርብን!
#ምልጃዋ_ሀገራችን_ይጠብቅልን !!
#ሕሙማንን_ይፈውስልን!!!
#የተወለድንበትን_ቀን_ከምንረግምበት_ፈተና_ሁሉ_እግዚአብሔር_ይሠውረን!!!!
#አሜን!!
#መጋቤ_ሀዲስ_ኢንጂነር_ነቅዐ_ጥበብ
@zemarian
1.3K views18:35