2023-04-12 21:41:16
✥ በዕለተ ሆሳዕና የተፈጸሙ ድንቅ ምሥጢራት
-> ሆሳዕና የዐቢይ ጾም ስምንተኛ ሣምንት
-> ሆስዕና :- እባክህ አድነን ማለት ነው:: መዝ 117፥25፣ ማር 11÷10፡ ዮሐ 12፥13)
. ሆሳዕና ለወልደ ዳዊት እምሆሳዕናሁ አርአየ ተአምረ ወመንክረ ፡፡ መድኃኒትነት ፤ መድኃኒት መኾን፤ መድኃኒት መባል ላንተ ለዳዊት ልጅ ይገባሃል። ማለት ነው። (ማቴ 21÷9:: ቅዳ ጎር)::
-> ሆሳዕና፤ የበዓል ስም፤ የሰሌን በዓል፤ ሰሌን ይዘው እያመሰገኑ የሚያወዱሰበት ለብሉይ የመጸለት 7ኛ ቀን፤ ለሐዲሱ ግን ከትንሣኤ
በፊት ያለ እሑድ፡፡ (ዘሌ 23፥39-44 /ስንክ መስ3)፡፡
-> በዚህ እለት የእስራኤል ህዝብ የዘንባባ ዝንጣፊ በመያዝ ሆሣዕና በማለት እየጮኹ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ አጀቡት ትንቢቱ ይፈፀም ዘንድ ውርንጫውን በወይን ግንድ ያስራል ተብሎ እንደ ተፃፈ (ዘፍ49÷1:: ዘካ 9፥9-10:: ኢሳ 40÷10) ያን ጊዜ ጌታ ከደቀመዛሙርቱሰቱን ላከ ‹‹በፊታችሁ ወደ አለ ሀገር ሂዱ አህያዋን ከውርንጭላው ጋር ታስራ ታገኛላችሁ ፈትታችሁ አምጡልኝ) አላቸው
. ሰው ሁሉ ከማዕሰረ ኃጢአት ለመፈታት እንደደረሰ ለማጠየቅ ፈትታችሁ አምጡልኝ አለ።
አንድም፦ ለሐዋርያት የተሰጣቸውን ሥልጣነ ክህነት ያስረዳል (ማቴ.18፥18)
- ምን ታደርጋላችሁ? የሚል ሰው ቢኖር ጌታቸው ይፈልጋቸዋል በሉ አላቸው
. በተፈጥሮ ጌታቸው ነውና (ዮሐ.1፥3)
- ይህ ሁሉ የተደረገው ጻድቅ የባሕርይ አምላክ የዋህ ንጉሥሽ በውርንጫና በአህያይቱ ተቀምጦ ይመጣልና ብላችሁ ለጽዮን ልጅ ንገሯት ብሎ ነቢዩ የተናጋረው ይደርስ ዘንድ ነው:: (ዘካ 9፥9-10:: )
. ልጅ እስራኤል ናቸው ጽዮን ኢየሩሳሌም ናት በሀገሪቱ ሰዎቹን መናገር ነው የአማራ ልጅ ፣ የትግሬ ልጅ እንዲሉ
. አንድም፦ ልጅ አይለወጥም ጽዮን ህግናት እናት ልጆቿን ሠርታ ቀጥታ እንድታሳድግ ሕግም ሕዝቡን ሠርታ ቀጥታ ታኖራለች
-> ደቀመዛሙርትም እንደ ታዘዙት ውርንጫዋን ከእነ አህያይቱ አመጡለት ልብሳቸውን ጎዘጎዙለት
. ኮርቻ ይቆረቁራል ልብስ አይቆረቀርም
የማትቆረቁር ሕግ ሠራህልን ሲሉ ።
. አንድም፦ ኮርቻ ያጽራል ልብስ አያጽርም :: የማታጽር ሕግ ሠራሕልን ሲሉ።
. አንድም፦ ልብስ ከአካል ያለውን ነውር ይሰውራል አንተም ከባቴ አበሳ ነህ ሲሉ
-> በሁለቱም ጌታ በአንድ ጊዜ ተቀመጠባቸው ከደብረ ዘይት እስከ ኢየሩሳሌም 16 ምዕራፍ ነው 14ቱን በእግር ሂዲል ሁለቱን በአህያይቱ ሂዷል ፥ በዕዋል(ውርንጫ) ሆኖ ቤተመቅደሱን 3 ጊዜ ዙራል
. ምሳሌ 14ቱን በእግሩ መሄዱ፤ አሥሩ (10) የአስርቱ ቃላት አራቱ (4) የአራቱ ኪዳናት (ኪዳነ ኖህ፣ ክህነተ መልከ ፄዴቅ፣ ግዝረተ አብርሃም፣
ጥምቀተ ዮሐንስ) ናቸው
በአህያ መቀመጡ ለምን ቢሉ ትንቢቱን ምሳሌውን ለመፈጸም ነው።
. ትንቢቱ አጠፍዕ ሠረገላ እም ኤፍሬም ወአፍራሰ እምይሁዳ (ዘካ.9፥10)
. ምሳሌው ቀድሞ አባቶች ነቢያት ዘመነ ጸብዕ የሆነ እንዲሆነ በፈረስ ተቀምጠው ዘገር ነጥቀው ይታያሉ። ዘመነ ሰላም የሆነ እንደሆነ በአህያ ተቀምጠው መነሳንስ ይዘው ይታያሉና ዘመነ ሰላም ደረስ ሲል ትንቢቱን በአወቀ አናግሮአል ምሳሌውንም አስመስሎአል፡፡
. ምሥጢሩ እንደምነው ቢሉ በአህያ የተቀመጠ ሸሽቶ አያመልጥም አሳዶ አይዝም ከሹኝ አልታጣም ካልሹኝ አልገኝም ሲል ነው::
አንድም፦ ከመ እንተ ዕድግት ነፍስቶሙ እንዲ በንጹሓን ምእመናን አድራባቸው እኖራለሁ ሲል
ዕድግት የእስራኤል ምሳሌ ቀንበር የለመደች እንደ ሆነች እስራኤልም ሕግ መጠበቅ ለምደዋልና ፥ ዕዋል የአሕዛብ ምሳሌ ቀንበር ያልለመደች እንደ ሆነች አሕዛብም ህግ መጠበቅ ያለመዱ ናቸውና።
. አንድም እድግት የኦሪት፣ ዕዋል የወንጌል ዕድግት ቀንበር መሸከም የለመደች እንደሆነ ኦሪትም የተለመደች ህግ ናትና ፥ ዕዋል ቀምበር መሸከም ያልመደች እንደሆነ ወንጌልም ያልተለመደች ሕግ ናትና። አንድም:- ሕግ መጠበቅ ላልለመዱ ለአሕዛብ ወንጌልን አስተምሩ ሲል ነው።
-> እኒህስ አህዮች ከምን የተገኙ ናቸው ቢሉ ለገበያ ብለው ያዘዋቸው የመጡ ናቸው ኋላስ ምን አድርጓቸዋል ቢሉ ኋላማ ምን ያደርጓቸዋል
ለባለቤታቸው መልሷቸዋል ።
የሚበዙ ሕዝብም ልብሳቸዉን በጎዳና አነጠፉ አንተ የተቀመጥክባት አህያ መሬት መንካት አይገባትም ሲሉ
. አንድም :- በኢዩ ልማድ ፦
- ኤልሳዕ ከደቂቀ ነቢያት አንዱን ቀርነ ቅብዑን ይዘህ ሂደህ ኢዩን ቀብተህ አንግሠኸው ፈጥነህና፤ ከሰው ጋራ አትነጋገር ብሎ ላከው ። ቢሄድ ኢዩን ከባልንጀሮቹ ጋራ ሲጫወት ባደባባይ ተቀምጦ አገኘው ብየ መልእክት አለው ። እምኔነኑ እምኅበ መኑ አለው ። ከኛን ነው ከሌላ ቢለው ኀቤከ መልአክ ወዳንተ ተልኬ መጥቻለሁ አለው ። ከእልፍኝ ይዞት ገባ ።
ከመዝ ይቤ አምላከ እስራኤል ቀባዕኩከ ትንግሥ ላዕለ ሕዝብየ እስራኤል ብሎ ቀብቶት ሩጦ ሄደ ።
ኋላ ኢዩ መጣ ። ምን አለህ ንገረን አሉት ። ኢተአምሩኑ ከመ በከ ይዛዋዕ ዝ ብእሲ ይህ ሰው ዋዛ ፈዛዛ እንዲናገር አታውቁምን አላቸው ።
ዕውነቱን ንገረን አሉት። ንገረንማ ካላችሁኝ ትነግሣለህ ብሎ ቀብቶኝ ሄደ አላቸው። እኛስ ሌላ ምን እንሻለን ብለው እኩሌቶቹ አንጽፈዋል ፤ እኩሌቶቹ ጋርደዋልና በዚያ ልማድ ።
ሌሎችም ቀጠል እየቆረጡ ከመንገድ ያነጥፉ ነበር።
-> ሰሌን (ዘንባባ) ነው ያሉ እንደሆነ ፦
. አብርሐም ይስሃቅን ፥ ይስሃቅም ያዕቆብ በወለዱ ጊዜ የሰሌን ቅጠል ይዘው እግዚአብሔርን አመሰግነዋል፡፡(ኩፋ 13፥20-22)
. እስራኤልም ከግብጽ በወጡ ጊዜ እስከ ሰባት ቀን ሰሌን በመያዝና በማክበር እግዚአብሔርን አመስግነዋል (ዘሌ23÷40-42፡፡
ዮሐ12፥13)
. ዮዲት ጠላትዋን ሆሎፎርኒስን ድል ባደረገች ጊዜ ይህንን ሥርዓት ፈጽመዋል፡፡ በዚህ ልማድ በሰሌን አመስግነዋል።
አንድም፦ ሰሌን (ዘንባባ) እሾኻም ነው ትእምርተ ኃይል ትእምርተ መዊዕ አለህ ሲሉ ።
አንድም፦ ዘንባባ ደርቆ እንደገና ህይወት ይዘራል የደረቀ ሕይወታችንን የምታለመልም አምላክ ነህ ሲሉ ነው
አንድም፦ ሰሌን እሳት አይበላውም ለብልቦ ይተወዋል አንተም ባሕርይህ አይመረመርም ሲሉ
- ማስታወሻ ፦ በኢየሩሳሌም ሰሌን (ዘንባባ) የለም (አይበቅልም ነበር) ጌታችን በሕፃንነቱ ወደ ግብፅ በተሰደደ ጊዜ ከመንገድ አግኝቷት ሂደሽ በእስራኤል ደብረ ዘይት ተተከይ ብሎ አዟት ተነቅላ ሂዳ ተተክላለች። ይህም ይታወቅ ዘንድ ዛሬ በእስራኤል በደብረ ዘይት ከተማ ዘንባባ በብዛት ይገኛል። ሕዝቡም ለጌታችን ከዚያ ይዘው ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው ነው ያነጠፉለት።
-> ተምር ነው ያሉ እንደሆነ ፦
. ተምር ልዑል ነው ልዑለ ባሕርይ ነህ ሲሉ
አንድም፦ ተምር ፍሬው አንድ ነው (የተምር ዛፍ ፍሬ በውስጡ ያለው ፍሬ አንድ ነው ) ዋህዶ ባሕርይ ነህ ሲሉ
አንድም፦ ተምር ፍሬው በእሾህ የተከበበ ነው
ባሕርይህ አይመረመርም ሲሉ
አንድም፦ የቴምር ዛፍ ፍሬ ጣፋጭ ነው፦ በኃጢአት የመረረውን ሕወታችን የምታጣፍጥልን አምላክ ነህ ሲሉ ነው።
-> ዘይት (የወይራ ዛፍ ዝንጣፊ) ነው ያሉ እንደሆነ :-
. የወይራ ዛፍ (ዘይት) ጽኑዕ ነው ጽኑዓ ባሕርይ ነህ ሲሉ ።
አንድም፦ ዘይት ብሩህ ነው ብሩሃ ባሕርይ ነህ ሲሉ ። እርሱ በጨለማ ኃጢአት ፣ ኦሪት ይኖር ለነበረ ሕዝብ ብርሃን የሆነ እርሱ ነውና።
353 views18:41