2023-03-11 21:47:06
ከሰሞኑ በሀላባ ትምህርት ቤት ውስጥ አንዲት ተማሪ በእምነቷ ምክንያት ታስራለች የሚል በተለይም በወንጌላውያን ዘንድ በሰፊው እየተራገበ ይገኛል። እውነታውን የማያቁ ሰዎችም መለስተኛ ውዥንብሮች ውስጥ ወድቀዋል። ያለውን ሁኔታ ከአካባቢው ለማጣራት እንደሞከርኩት ዝርዝር ጉዳዩን ከዚህ በታች ለማስቀመጥ እሞክራለሁ፦
..
1/ ልጅቷ የታሰረችበት ምክንያት በምትማርበት ትምህርት ቤት በርካታ ተማሪዎች ለህመም መዳረጋቸውን ተከትሎ ከህመማቸው ጀርባ መመረዝ እንዲሁም ድግምት እንዳለ በመታመኑ ሳቢያ ነው። በዚህ ተግባርም ቀጥተኛ ተሳታፊ ናት የሚሉ ጥርጣሬዎች በተማሪዎችም በህግ አካላትም በመኖሩ ሳቢያ ታስራለች። በወቅቱም "ገና ምን አይታችሁ?" የሚል ስሜታዊ ንግግር መናገሯን በቦታው ከነበሩ ሰዎች ለመስማት ችያለሁ።
...
2/ በእምነቷ ምክንያት ታሰረች የሚባለው ፈጽሞ ሀሰትና ጉዳዩን ለማጦዝ የተፈጠረ አስቂኝ ክስ ነው። በዋናነት ጉዳዩን አስመልክቶ ቀድሞ የታሰረውና እነዚያን ባዕድ ነገሮች እያዘጋጀ ይሰጣታል ተብሎ በቀዳሚነት የተከሰሰው ሰው ሙስሊም ሰው ነው። ተግባሩ እምነትን ያማከለ ቢሆን በአካባቢው የባህል ሀኪም ነኝ የሚለው አቶ ናሲር ቀድሞ አይታሰርም ነበር። ጉዳዩ ከእምነት ጋር የሚያያዝ አይደለምና ተጠርጣሪዎቹ ሙስሊምም ይሁኑ ፕሮቴስታንት የእምነት ልዩነት ሳይደረግ በተግባሩ ተጠርጥረው በህግ ቁጥጥር ስር ሊውሉ ችለዋል።
...
3/ አብዛኛው ሰው በዘመቻ መልክ ሳይቀር ስለታሰረችው ሴት ሲጮህ ተመልክተናል። በሚገርም ሁኔታ ግን እሷ በሰጠቻቸው ባዕድ ነገሮች ሳቢያ ታመው በህክምና ቦታዎች ስለሚገኙ ሴቶች ማናቸውም መናገር አይፈልጉም። የነሱ ጉዳይ ከህመም አልፎ ሞት እራሱ ቢመጣ ለነዚህ ሰዎች ግዳቸው አይደለም። በዚህ መልኩ ጉዳዩን በህግ አግባብ እንዲፈታ ከመጠየቅ ይልቅ በዘመቻ ጫና ለመፍጠር መፍጨርጨርን መርጠዋል።
...
4/ የዞኑ የጸጥታ ቢሮ ይህንን በተመለከተ የወሰደው እርምጃ እንደ አንድ ኃላፊነት እንደሚሰማው የመንግስት አካል ተገቢ ነው። በርካታ ሰዎች ታመዋል፥ የዚህ መነሻ ተደርጎ የተጠቀሰም ተጠርጣሪ አለ። በዚህ ሒደት ውስጥ ተጠርጣሪውን በህግ ከለላ ውስጥ አድርጎ ምርመራ ማካሔዱ በምን መልኩ እንደ ውግዝ እንዳስቆጠረው ሊገባኝ አልቻለም። ተጎጂዎች ጉዳዩ እንዲጣራላቸውና አጥፊው ተገቢውን ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድበት ይጠብቃሉ። ይህንን ጉዳይ ኃላፊነት ወስዶ የሚያጣራው ደግሞ የሚመለከተው የጸጥታ አካል ነው። ይህ ደግሞ ስራው ነውና የሚጠበቅ እንጅ የሚያስወግዝ አይደለም።
...
❐ ሲጠቃለል
...
በግሌ ከተለያዩ አካላት ለማጣራት እንደሞከርኩት ያገኘሁት መረጃ ይህ ነው። ከዚህ በዘለለ ሀላባን ሆን ተብሎ በሀይማኖት ስም በጅምላ ለማጠልሸት እየተሄደበት ያለው ርቀት እጅግ አሳፋሪ ነው። በጉያዋ በርካታ የተለያየ እምነት አማኞች ትላንትም ኑረዋል፥ ዛሬም በሰላም እየኖሩ ነው። ነጠላ ክስተቶችን ሰንጥቆ ሀገር ምድሩ የተናወጠ እያስመሰሉ በማኅበራዊ ሚዲያው ለማስተጋባት የሚሞከረው አካሔድ አይጠቅምም። መሬት ላይ ያለውንም እውነታ የካደ ነውና ቢታረም መልካም ነው።
___ የሕያ ኢብኑ ኑህ
https://t.me/Yahyanuhe
1.2K viewsedited 18:47