2023-05-31 07:59:36
አሏህ አስገኚ ነው!
ክፍል ሁለት
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡
59፥24 እርሱ አላህ ፈጣሪው፣ አስገኚው፣ ቅርጽን አሳማሪው ነው፡፡ ለእርሱ መልካሞች ስሞች አሉት፡፡ هُوَ اللَّهُ الْخَالِقُ الْبَارِئُ الْمُصَوِّرُ ۖ لَهُ الْأَسْمَاءُ الْحُسْنَىٰ
በዐረቢኛ "አብ" أَب ማለት "ባለቤት" በሚል ይመጣል፥ ለምሳሌ፦ የዐብዱል ሙጧሊብ ልጅ ዐብዱል ዑዛ በቁርኣን "አቢ ለሀብ" أَبِي لَهَب ተብሏል፦
111፥1 የአቡ ለሀብ ሁለት እጆች ከሰሩ፥ እርሱም ከሰረ፡፡ تَبَّتْ يَدَا أَبِي لَهَبٍ وَتَبَّ
"አቢ" أَبِي የሚለው ኢሥሙል መጅሩር "አብ" أَب የሚለውን መደብ አመላካች ነው፥ "ለሀብ" لَهَب ማለት "መንቀልቀል" ማለት ነው። "መንቀልቀል" የተባለው እሳት ጀሀነም ውስጥ ነው፦
111፥3 የመንቀልቀል ባለቤት የኾነችን እሳት በእርግጥ ይገባል፡፡ سَيَصْلَىٰ نَارًا ذَاتَ لَهَبٍ
77፥31 አጠላይ ያልኾነ ከእሳቱም ላንቃ የማያድን ወደ ኾነው አዝግሙ፡፡ لَّا ظَلِيلٍ وَلَا يُغْنِي مِنَ اللَّهَبِ
በጥቅሉ "አቢ ለሀብ" أَبِي لَهَب ማለት "የመንቀልቀል ባለቤት" ማለት ነው ነው፥ "አብ" أَب እዚህ ዐውድ ላይ ወላጅ "አባት" ማለት ሳይሆን "ባለቤት" ማለት ነው።
አምላካችን አሏህ አስገኚ፣ ዓለማትን የሚያስተናብር ጌታ፣ የንግሥና እና የፍርዱ ቀን ባለቤት መሆኑን በግልጽ እና በማያሻማ መልኩ በቁርኣን ተቀምጧል።
በባይብል ደግሞ "አብ" אָב የሚለው የዕብራይስጥ ቃል "አስገኚ" ለሚለው ቃል ሥነ-ዘይቤአዊ አገላለጽ"analogical expression" ሆኖ መጥቷል፦
ዘዳግም 32፥6 የገዛህ አባትህ አይደለምን? የፈጠረህ እና የመሠረተህ እርሱ ነው። הֲלוֹא־ הוּא֙ אָבִ֣יךָ קָּנֶ֔ךָ ה֥וּא עָֽשְׂךָ֖ וַֽיְכֹנְנֶֽךָ׃
አንዱ አምላክ ስለ ፈጠረ እና ስለ መሠረተ "አብ" אָב መባሉ በእማሬአዊ "ወላዲ" ሳይሆን በፍካሬአዊ "አስገኚ" ማለት ነው። አምላክ "አባት" መባሉ "ባለቤት" መባልን ያሳያል፥ ለምሳሌ የዮሐንስ የማዕረግ ስም "አቡ ቀለምሲስ" ሲሆን "የራእይ ባለቤት" ማለት ሲሆን "አባ ወራ" እራሱ "ባለቤት" ማለት ነው። የዝናብ ባለቤት አምላክ ሲሆን ለዝናብ አባት ተብሏል፦
ኢዮብ 38፥28 በውኑ ለዝናብ "አባት" አለውን ወይስ የጠልን ነጠብጣብ "የወለደ" ማን ነው? הֲיֵשׁ־לַמָּטָ֥ר אָ֑ב אֹ֥ו מִי־הֹ֝ולִ֗יד אֶגְלֵי־טָֽל׃
እዚህ አንቀጽ ላይ "አባት" ተብሎ በዕብራይስጡ የገባ ቃል "አብ" אָ֑ב መሆኑን ልብ አድርግ! "አባት" ሲባል "ባለቤት" "አስገኚ" "ምንጭ" "ባለቤት" በሚል ቀመር ከተረዳን ዘንዳ የኢየሱስ "አባት" ሲባል የኢየሱስ "አስገኚ" በሚል እንረዳለን፦
ቆላስይስ 1፥3 የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን አባት አምላክን ሁልጊዜ እናመሰግናለን። Εὐχαριστοῦμεν τῷ Θεῷ Πατρὶ τοῦ Κυρίου ἡμῶν Ἰησοῦ Χριστοῦ.
አንዱ አምላክ የኢየሱስ "አባት" ነው ሲባል የኢየሱስ "አስገኚ" በሚል ተቀጽሎ እንደመጣ በቀላሉ እንረዳለን። አንዱ አምላክ ሁሉንም አማንያን ስለሚያስተናብር "አንድ አባት" ተብሏል፦
ሚልክያስ 2፥10 ለሁላችን አንድ አባት ያለን አይደለምን? አንድ አምላክስ የፈጠረን አይደለምን? הֲלֹ֨וא אָ֤ב אֶחָד֙ לְכֻלָּ֔נוּ הֲלֹ֛וא אֵ֥ל אֶֽחָ֖ד בְּרָאָ֑נוּ
ዮሐንስ 8፥41 አንድ አባት አለን፥ እርሱም አምላክ ነው። ἕνα Πατέρα ἔχομεν τὸν Θεόν.
ኤፌሶን 4፥6 አንድ አምላክ የሁሉም አባት አለ። εἷς Θεὸς καὶ Πατὴρ πάντων,
እኛ እያንዳንዳችን ወላጅ አባት አለን፥ ወላጃችንን "አባት" ብለን እንጠራለን፥ ኢየሱስ "አንዱ የሰማዩን አምላክ እንጂ "ማንንም "አባት" ብላችሁ አትጥሩ" ሲለን "አባት" የሚለው ካለመኖር ወደ መኖር ያስገኘ "አስገኚ" ብቻ አመላካች ነው፦
ማቴዎስ 23፥9 "አባታችሁ አንዱ እርሱም የሰማዩ ነውና" በምድር ላይ ማንንም፦ "አባት" ብላችሁ አትጥሩ። καὶ πατέρα μὴ καλέσητε ὑμῶν ἐπὶ τῆς γῆς· εἷς γάρ ἐστιν ὑμῶν ὁ Πατὴρ ὁ οὐράνιος.
"አባት" ለአንዱ አምላክ ሲቀጸል በራሱ "አስገኚ" "አስተናባሪ" "ተንከባካቢ" ማለት እንጂ "የባሕርይ አባት" ማለት አይደለም። ለምሳሌ፦ አምላክ "እሳት" ተብሏል፦
ዕብራውያን 12፥29 አምላካችን በእውነት የሚያጠፋ "እሳት" ነው።
ዘዳግም 4፥24 አምላክህ ያህዌህ የሚበላ እሳት እና ቀናተኛ አምላክ ነው።
"እሳት" ማለት "ቁጠኛ" "ቀጪ" የሚለውን ለመግለጽ የመጣ ፍካሬአዊ አነጋገር መሆኑን ከተረዳን ዘንዳ በተመሳሳይም "አባት" ማለት "አስገኚ" "አስተናባሪ" "ተንከባካቢ" "ባለቤት" በሚል እንረዳለን። አምላክ "ድንጋይ" ተብሏል፦
ዘዳግም 32፥4 እርሱ "ዓለት" ነው። הַצּוּר֙
"ዓለት" ማለት "ድንጋይ" ማለት ነው፥ "ድንጋይ" ማለት "መሸሸጊያ" "አንባ" የሚለውን ለመግለጽ የመጣ ፍካሬአዊ አነጋገር መሆኑን ከተረዳን ዘንዳ በተመሳሳይም "አባት" ማለት "አስገኚ" "አስተናባሪ" "ተንከባካቢ" "ባለቤት" በሚል እንረዳለን።
በ 325 ድኅረ ልደት የተከናወነው የኒቂያ ጉባኤ፦ "ከአምላክ የተገኘ አምላክ" በማለት አሏህን ወላዲ መሢሑን ተወላዲ በማድረግ ለአሏህ ቁራጭን አደረጉለት፦
43፥15 ከባሮቹም ለእርሱ ቁራጭን ልጅ አደረጉለት፡፡ ሰው በእርግጥ ግልጽ ከሓዲ ነው፡፡ وَجَعَلُوا لَهُ مِنْ عِبَادِهِ جُزْءًا ۚ إِنَّ الْإِنسَانَ لَكَفُورٌ مُّبِينٌ
አሏህ አንድ ነው፥ እርሱ ከማንነቱ እና ከምንነቱ ማንንም አልወለደም። ከእርሱ ማንነት እና ምንነት የተወለደ ማንም የለም፥ ከእርሱ የተወለደ ማንም አምላክ የለም፦
112፥1 በል «እርሱ አላህ አንድ ነው፡፡ قُلْ هُوَ اللَّهُ أَحَدٌ
112፥3 አልወለደም፤ አልተወለደምም፡፡ لَمْ يَلِدْ وَلَمْ يُولَدْ
23፥91 አላህ ምንም ልጅን አልወለደም፡፡ ከእርሱም ጋር አንድም አምላክ የለም፡፡ مَا اتَّخَذَ اللَّهُ مِن وَلَدٍ وَمَا كَانَ مَعَهُ مِنْ إِلَـٰهٍ
“ወለድ” وَلَد የሚለው ቃል “ወለደ” وَلَدَ ማለትም “ወለደ” ከሚል ሥርወ-ቃል የመጣ ሲሆን “ወልድ” ወይም “ልጅ” ማለት ነው። "ከአምላክ አካል አካልን ወስዶ እና ከባሕርይው ባሕርይን ወስዶ፥ አብን መስሎ እና አህሎ መገኘት ወይም መወለድ" የሚለውን እሳቤ ቁርኣን ስለማይቀበል ወደዚያ የሚጠጋ "አባት" የሚለውን ስያሜ ለአሏህ አይጠቀምም። እኛ ሙሥሊሞችም አንጠቀምም፥ ከዚያ ይልቅ "አብ" የሚለው ትርጉሙ "አስገኚ" ወይም "አስተናባሪ" "ተንከባካቢ" አሊያም "ባለቤት" የሚል ፍቺ ካለው በቁርኣን በግልጽ አሏህ "አስገኚ" የተባለበትን "አል ባሪእ" الْبَارِئ እና "አስተናባሪ" "ተንከባካቢ" የተባለበትን "አር ረብ" الْرَبّ እንዲሁ "ባለቤት" የሚለውን "አል ማሊክ" الْمَالِك እንጠቀማለን።
አምላካችን አሏህ በተውሒድ ሙዋሒድ አርጎ ያጽናን! አሚን።
ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
https://t.me/Wahidcom
ወሠላሙ ዐለይኩም
8.2K viewsedited 04:59