2023-09-11 07:05:11
አልሸባብ በኢትዮጵያ ላይ ሥጋት ደቅኗል ተባለ
በሶማሊያ የሚገኘው የአፍሪካ ህብረት የሽግግር ተልዕኮ ወታደራዊ ኃይል (አትሚስ) በፈረንጆች 2024 ሙሉ ለሙሉ ከሶማሊያ ለቆ ሊወጣ በመሆኑ አልሸባብ ለኢትዮጵያ ስጋት ሆኗል ሲል ዓለም አቀፍ ጥናትና ትንታኔዎች በመስራት የሚታወቀው ዘጀምስ ታውን ፋውንዴሽን ባወጣው ዘገባ ገልጿል።
ይህም የሽብር ቡድኑ ከሶማሊያ ጋር ረዥም ድንበር የምትዋሰነውን ኢትዮጵያ በመጪዎቹ ዓመታት ረጅም የሆነ ግጭት ዉስጥ ሊያስገባት እንደሚችል ጠቁሟል።
አልሸባብ ከፈረንጆች 2006 እስከ 2009 በሶማሊያ ባደረገው ወረራ ይዞት ከነበረው በሞቃዲሾ የሚገኘው እስላማዊ ፍርድ ቤቶች ህብረት ከስልጣን እንዲወርድ መደረጉን ተከትሎ፤ በኢትዮጵያ ላይ ሰፊ ቅሬታ እንዳለውም ተመላክቷል።
ኢትዮጵያ ለ15 ዓመታት በሶማሊያ በቆየው የአፍሪካ ህብረት ወታደራዊ ኃይል ውስጥ ትልቅ ተሳትፎ የነበራት መሆኑን እና በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት ተልዕኮ እንዲሳካ ቁልፍ ሚና መጫዎቷምን ዘገባው ገልጿል።
አልሸባብ ለኹለት አስርት ዓመታት በሶማሊያ እያደረሰ ባለው ጥቃት ኢትዮጵያ የምትጫወተው ሚና የአልሸባብ የረጅም ጊዜ ዒላማ እንድትሆን አድርጓታል የተባለ ሲሆን፤ ታጣቂ ቡድኑ በኢትዮጵያ ላይ ያለው ጥላቻ እየጨመረ የመጣ ይመስላልም ነው የተባለው።
የአፍሪካ ህብረት የሽግግር ተልዕኮ ኃይል (አትሚስ) ባለፈው ሰኔ ወር ከ22 ሺሕ ወታደሮች መካከል 2 ሺሕ የሚሆኑትን ከሶማሊያ ያስወጣ ሲሆን፤ በመጪው መስከረም ወር 3 ሺሕ ወታደሮችን ሙሉ ለሙሉ ለማስወጣት ማቀዱን አመላክቷል።
ምንም እንኳን የአፍሪካ ህብረት የሽግግር ተልዕኮ ኃይል ዋነኛ ዓላማ የሶማሊያን ደህንነት በማረጋጋት ኃላፊነቱን ለሶማሊያ ፌደራል መንግሥት ማስተላለፍ ቢሆንም፤ የአልሸባብ ጥቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ ተገልጿል።
ኢትዮጵያ በአትሚስ ካላት ወታደራዊ ተሳትፎ በተጨማሪ ባለፈው መጋቢት ወር ኢትዮጵያ፣ ጅቡቱና ኬንያ ሞቃዲሾ ላይ ተገናኝተው ባደረጉት ምክክር ተጨማሪ 1000 ወታደሮችን ወደ ሶማሊያ ልካለች።
በዚህም አልሸባብ የጥቃቱን ዋነኛ ትኩረት በውጭ ወታደሮች ላይ አንጣጥሮ ቆይቷል።
አልሸባብ ካለፉት ቅርብ ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ ድንበር ጥቃት ለማድረስ ሲሞክር የሚስተዋል ሲሆን፤ ባለፈው ሰኔ ወር ላይም በሶማሌ ክልል ዶሎ ከተማ ጥቃት ማደረሱ ይታወሳል።
በተለይም ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ሰፊ ድንበር የሚጋሩ በመሆናቸው፤ ቡድኑ በኢትዮጵያ ላይ ጥቃት ለመፈጸም ካለው ጽኑ ፍላጎት እና ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው የጸጥታ ችግሮች ጋር ተዳምሮ አልሸባብ በሚቀጥሉት ወራትና ዓመታት ተከታታይ የሽብር ጥቃት ሊከፍት እንደሚችል ነው የተጠቆመው።
የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ዋነኛ ስጋት የሆነው እስላማዊ ቡድን በተለይ በሶማሊያ በሚፈጽማቸው አውዳሚ ጥቃቶች የብዙዎችን ሕይወት እየቀጠፈ ይገኛል።
አዲስ ማለዳ
@Topmereja
16.3K views04:05