2023-10-16 11:35:16
“የተማሪዎች መውደቅ የትምህርት ሥርዓቱንና የትምህርት ሥርዓቱን የሚመራውን ተቋም ውድቀትና ክሽፈት ማሳያ ነው” እናት ፓርቲ
ፓርቲው ኹሉም ተማሪዎች ፈተናውን በድጋሚ እንዲፈተኑ ጠይቋል
የ2015 የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን 817 ሺሕ 832 ተማሪዎች መውደቃቸው የትምህርት ሚኒስቴርን የአሰራር ሂደት፣ የፈተና አወጣጥ፣ የግምገማ እንዲሁም መለኪያ መንገዶች ተአማኒነትን ጥያቄ ውስጥ ከማስገባቱ ባሻገር፤ ኹኔታው የተፈታኝ ተማሪዎችን መውደቅ ሳይሆን የትምህርት ሥርዓቱንና የትምህርት ሥርዓቱን የሚመራውን ተቋም ውድቀትና ክሽፈት ማሳያ ነው ሲል እናት ፓርቲ ገለጸ።
ፓርቲው የ2015 የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤትን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፤ “በትምህርት ሚንስቴር ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ መግለጫ የተሰጠበት የፈተናው ውጤት፤ ጥሮ ግሮ በመስራት "ልጄን ለቁምነገር አበቃለሁ" ብሎ ለዘመናት ያስተማረውን የአገራችንን ሕዝብ ክፋኛ አሳዝኗል፡፡” ብሏል።
በተጨማሪም ውጤቱ በተማሪዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ ተስፋ መቁረጥ እና የማይሽር ሥነ-ልቦናዊ ተጽእኖን ማሳደሩን ገልጿል።
ፓርቲው አክሎም፤ “አገራችን በጦርነት እና አለመረጋጋት ወስጥ መሆኗ እየታወቀ "97% ያህል ተማሪዎች ወድቀዋል" ማለት፤ የትምህርት ሚኒስቴር መስርያ ቤቱ ከመንግሥት ጋር የተዋዋለው ድብቅ አጀንዳ እንዳለው ያመለክታል።” ሲል ገልጿል፡፡
“ተማሪዎች የአገራችን ተስፋዎች ናቸው።” ያለው ፓርቲው፤ እነዚህን የነገ አገር ተረካቢ ኃይሎች በኢትዮጵያ ተስፋ እንዳያደርጉ ከጅምሩ ማምከን ተገቢ አለመሆኑን አመላክቷል፡፡
እንዲሁም “ባለፋት አምስት ዓመታት "ለውጥ እናመጣለን" በሚል ሰበብ እንዲሁም በቂ ምክክር፣ ምርምር እና ግምገማ ያልተደረገበትን አዲስ የትምህርት ፍኖተ ካርታ በፖለቲካዊ ውሳኔ በትውልዱ ላይ ለመጫን የተደረገው እርብርብ ትልቅ ኪሳራ አሳድሯል።” ብሏል፡፡
“ለትምህርት ሴክተሩ እየተሰጠ የሚገኘው ትኩረት አናሳ መሆን፣ ለተማሪዎች የመጻሕፍት አቅርቦት አለመኖር፣ ትክክለኛ የትምህርት ሰነዶችን የማጣራት ዘመቻው ደካማና የይምሰል መሆኑ፣ የተንሸዋረረ የጥያቄ አወጣጥ፣ የምዘና ሥርዓቱ ዝርክርክነት፣ የጥያቄዎቹ መልስ ይፋ አለመደረጉ፣ ዝቅተኛ የበጀት ድልድል ወዘተ… አሁንም በዋልፈሰስ መቀጠላቸው፤ ቀጣዩ ትውልድ በትምህርት መስክ ተስፋ እንዳያደርግ ምክንያት ይሆናሉ” ብሎ እንደሚያምንም ፓርቲው ገልጿል፡፡
በተጨማሪም ባለፋት ሰላሳ ኹለት ዓመታት መምህራን ክብር እንዲያጡ፣ በሙያቸው ከመኩራት ይልቅ እንዲሸማቀቁ፣ መሠረታዊ ፍላጎታቸውን መልሰው በችግር ፈቺ የምርምር ሥራዎች ላይ እንዳያተኩሩ የተፈጸመባቸው በደል ሁንም ተጠናክሮ መቀጠሉ ፓርቲውን እንደሚያሳስበው አመላክቷል፡፡
ስለሆነም “የትምህርት ሚኒስቴር የአሰራር ሥርዓቱን ከወሬ በዘለለ በተግባር ከፖለቲካ ጥገኝነት እንዲያላቅቅ” የጠየቀው ፓርቲው፤ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ከሥር መሠረቱ ስትራቴጂካሊ መስራት ሲገባው በስሜት ከአናቱ ለማስተካከል የሄደበት እርቀት የተሳሳተ በመሆኑ ሊታረም ይገባል ብሏል፡፡
እንዲሁም፤ የተማሪዎች ኹለንተናዊ አቅም እንዲያድግ መንግሥት በዋናነት ደሞዝን ጨምሮ የመምህራን አኗኗርና ሕይወት እንዲቀየር አፋጣኝ ወሳኔ በመስጠት ለተግባራዊነቱ እንዲሰራ አሳስቧል፡፡
በተጨማሪም፤ በ2015 የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የወደቁ የተማሪዎች ቁጥር እጅግ በጣም ከፍተኛ (817 ሺሕ 832) በመሆኑ፤ እንዲሁም የምዘና ሂደቱን በግልጽ ጥያቄ ውስጥ የሚከት በመሆኑ የተስተዋሉ ችግሮች በአግባቡ ተቀርፈው ኹሉም ተማሪዎች በድጋሚ እንዲፈተኑ ፓርቲው ጠይቋል፡፡
@Topmereja
13.7K views08:35