2022-05-13 10:05:54
#ቲንክአቢሲኒያ_የቡናቁርስ_መረጃዎች
1፤አቀፍ ተቋሟት በዲጂታል ዘርፉ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ ቀረበ። ኢትዮጵያ ምቹ የዲጂታል ስነ ምህዳር እየፈጠረች በመሆኑ አለም አቀፍ ተቋሟት በዘርፉ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶ/ር በለጠ ሞላ ጥሪ አቀረቡ። በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ለሁለት ቀናት በአዲስ አበባ ሲካሄድ የነበረው 19ኛው የኢኖቬሽን አፍሪካ ዲጂታል ጉባኤ ተጠናቋል። የዲጂታል ይዘትና አገልግሎት ላይ ትኩረቱን አድርጎ በተካሄደው በዚህ ጉባኤ ላይ ከ 26 በላይ ድርጅቶችና ከ390 በላይ ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ ተሳታፊዎች ታድመዋል። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶ/ር በለጠ ሞላ ኢትዮጵያ ምቹ የዲጂታል ስነ ምህዳር እየፈጠረች በመሆኑ አለም አቀፍ ተቋሟት በዘርፉ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አቅርበዋል። በቴሌኮም ዘርፍ የተጀመረው ማሻሻያ ለዲጂታል ቴክኖሎጂ ትግበራ ትልቅ አቅም ይፈጥራል ያሉ ሲሆን መንግስትም አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
2፤የጉሙዝ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ መንግሥት ፍትህ ላላገኙት እስረኞች አስቸኳይ መፍትሄ እንዲሰጥ ጠየቀ።የጉሙዝ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሺ እና አሶሳ ዞኖች ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ የታሰሩ 47 ሰዎች እስካሁን ለፍርድ አልቀረቡም ሲል ቅሬታውን ማሰማቱን ዶይቸቨለ ዘግቧል። ንቅናቄው መንግሥት ፍትህ ላላገኙት እስረኞች አስቸኳይ መፍትሄ እንዲሰጥ ጠይቋል። የክልሉ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ግን ፍርድ ቤት ያልቀረበ
ተጠርጣሪ እስረኛ የለም ሲል አስተባብሏል። የዞኑ ፖሊስ በበኩሉ፣ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ለአራት ዓመታት የታሰሩ ሰዎች መኖራቸውን አምኖ፣ ጉዳዩን ለሚመለከተው አካል ማሳወቁን
ተናግሯል።
3፤በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ ዓሳ የማርባት ሥራ ተፈቀደ።በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የዓሳ ማርባት ሥራ መፈቀዱን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ። ግብርና ሚንስቴር በሕዳሴ ግድብ ላይ አሳ ማርባት እንዲጀመር መፍቀዱን የዘገበው ሪፖርተር ነው። በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ጥናት መሠረት፣ ኢትዮጵያ በዓመት ከ94 ሺህ 500 ቶን በላይ አሳ የማምረት አቅም ያላት ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት እየተመረተ የሚገኘው ግን ከ60 ሺህ ቶን በታች ነው። ሰው ሰራሽ ሐይቆች ከዓመታዊ ምርቱ የ27 በመቶ ድርሻ አላቸው። የአንድ ኢትዮጵያዊ ዓመታዊ የአሳ ፍጆታ ከግማሽ ኪሎ ግራም በታች ሲሆን፣ በሌሎች የአፍሪካ አገራት ግን ፍጆታው ወደ 12 ኪሎ ግራም አድጓል።
4፤ ሩስያ ፊንላድ ኔቶን ከተቀላቀለች የአፀፋ እርምጃ እንደምትወስድ አሳወቀች። ፊንላንድ ያለምንም መዘግየት ኔቶን ለመቀላቀል ለማመልከት እንደምትፈልግ ገልፃለች። ስውዲንም ፊንላንድ ትከተላለች እየተባለ ነው። ይህ ደግሞ ሞስኮን ክፉኛ ያስቆጣ ሲሆን ፊንላንድ ኔቶን ለመቀለቀል ያሳየችውን ፅኑ ፍላጎት እና ዝግጁነት " ቀጥተኛ ስጋት " ስትል በመጥራት " ወታደራዊ-ቴክኒካል " እርምጃዎችን ጨምሮ አፀፋዊ ምላሽ እንደምትሰጥ አስፈራርታለች። ይህም በኢኮኖሚው ላይ የሚያሳድረው ጫና ለታዳጊ ሀገራትና ለመላው ዓለም የሚተርፍ ነው ተብሏል። ከዩክሬን ጦርነት በኃላ ሩስያ ፥ ፊንላንድ እና ስውዲን ኔቶን ለመቀላቀን ብታስቡ እጅግ " ጎጂ " የሆኑ ውጤቶች [ኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ] ይኖራል ስትል አስጠንቅቃቸው ነበር።
5፤ዛሬ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አንድ የአሜሪካን ዶላር በ51 ብር ከ4676 ሳንቲም እየተገዛ ይገኛል። እንዲሁም መሸጫ ዋጋው 52 ብር ከ4970 ሳንቲም መሆኑን ከድረገጹ ተመልክተናል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋው 59 ብር ከ9796 ሳንቲም እንዲሁም መሸጫው 61 ብር ከ1792 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ53 ብር ከ6859 ሳንቲም እየገዛ በ54 ብር ከ7596 ሳንቲም እየተሸጠ ሲሆን፣ አንድ የቻይና ዩዋን ደግሞ በ6 ብር ከ8611 ሳንቲም ተገዝቶ በ6 ብር ከ9983 ሳንቲም እየተሸጠ እንደሚገኝ ቲንክአቢሲኒያ ተመልክቷል።
6፤ተጠባቂው ጨዋታ በቶተንሀም አሸናፊነት ተጠናቋል።የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ተስተካካይ ጨዋታ በቶተንሀም ሆትስፐር ስታዲየም ቀጥሎ ሲካሄድ ቶተንሀም ከ አርሰናል ጋር ያደረገውን ጨዋታ 3 - 0 በሆነ ውጤት አሸንፏል ። የቶተንሀምን የማሸነፊያ ግቦች ሰን ሁንግ ሚን እና ሀሪ ኬን ሁለት ግቦችን አስቆጥረዋል ። ሀሪ ኬን በሰሜን ለንደን ደርቢ ላይ አስራ ሶስተኛ ግቡን ማስቆጠር ችሏል ። በአርሰናል በኩል ሮብ ሆልዲንግ በ 33ተኛው ደቂቃ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል ። ሚኬል አርቴታ አርሰናልን ከተረከበ በኋላ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ መድፈኞቹ 13 ቀይ ካርዶችን ተመልክተዋል ። ሰን ሁንግ ሚን በዘንድሮ የውድድር አመት ሀያ አንደኛ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ግቡን አስቆጥሯል ። ውጤቱን ተከትሎ አርሰናል በ 66 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ቶተንሀም በ 65 ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ።
• @ThinkAbyssinia •
1.4K views07:05