2022-05-14 10:05:52
#ቲንክአቢሲኒያ_የቡናቁርስ_መረጃዎች
1፤በጅግጅጋ ከተማ ሲካሄድ የቆየው የሶማሌ እና የአፋር ክልሎች የጋራ ውይይት ተጠናቀቀ ።በመድረኩ የሰላም ሚኒስትሩ ብናልፍ አንዱአለም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከተከሰቱ ግጭቶች መካከል በአፋርና ሶማሌ ሕዝቦች መካከል የተስተዋለው ግጭት ይጠቀሳል ብለዋል። የተከሰተው ግጭት የሁለቱ ክልል ነዋሪዎችን ያፈናቀለና የአካባቢውን ሰላም ያደፈረሰ እንደነበረ ጠቅሰው ፣ሰው ሰራሽ ግጭቶችን ለመፍታት ተቀራርቦ መስራት አስፈላጊ ነው ብለዋል ሚኒስትሩ። በጅግጅጋ ከተማ ሲካሄድ በቆየው ውይይት በሶማሌና ወንድም ከሆነው የአፋር ሕዝብ መካከል የነበረውን ግጭት በውይይት ለመፍታት ዝግጁ መኾናቸውን የሁለቱ ክልሎች ርእሰ መስተዳድሮች አስታውቀዋል።
የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሁመድ በውይይት የተደረሠባቸውን ስምምነቶች ተፈፃሚ እናደርጋለን ብለዋል። የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ውይይቱ የህብረተሰቡን ሰላምና ልማት
ለማረጋገጥ የአመራር ቁርጠኝነት የታየበት ነው ብለዋል።
2፤ የኢትዮጵያ መንግስት ለችግሮች እልባት ለመስጠት እየተጓዘበት ያለው መንገድ አበረታች መሆኑን የአውሮፓ ህብረት ገለፀ። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የአውሮፓ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛን ዶክተር አኔት ዌበርን በፅህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል። አቶ ደመቀ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን እና በሰሜኑ ግጭት እና በድርቅ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች እየተደረገ ስላለው ሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ እና በቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ለልዩ መልዕክተኛዋ ገለጻ አድርገዋል ። የአውሮፓ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ዶ/ር አኔት ዌበር በበኩላቸው መንግሥት ያልተገደበ ሰብአዊ እርዳታ እንዲዳረስ ያሳለፈው የተኩስ አቁም ውሳኔ እና ለችግሮች እልባት ለመስጠት እየተጓዘበት ያለው መንገድ አበረታች ነው ብለዋል ።
3፤ከአልሸባብ የሽብር ተልዕኮ የተሰጣቸው ስድስት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ።በሶማሊያ በሚንቀሳቀሰው አልሸባብ የሽብር ቡድን ሰልጥነው በኢትዮጵያ የጥፋት ተልዕኮ ተሰጥቷቸው ወደ ስምሪት ሊገቡ የነበሩ ስድስት ተጠርጣሪ ግለሰቦች በአዲስ አበባ ከተማ እና በኦሮሚያ ክልል በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታውቋል። ተጠርጣሪዎቹ በኢትዮጵያ በህቡዕ ድጋፍ በሚያደርጉ አካላት አማካኝነት ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል ተሰባስበው ከየካቲት 2 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ወቅቶች ወደ ሶማሊያ እንዲገቡ የተደረገ ቢሆንም የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በአልሸባብ ቡድን ላይ በሚያደርገው ክትትልና የመረጃ ስምሪት መነሻነት የጥፋት እቅዱን ከውጥኑ ጀምሮ ሲከታተል ቆይቶ ከጸጥታ አካላት ጋር በተከናወነ ኦፕሬሽን ተጠርጣሪዎቹ በአዲስ አበባ ከተማ እና በኦሮሚያ ክልል በቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጉን ገልጿል።
4፤ቱርክ ፤ የፊንላንድ እና ስውዲን ኔቶን መቀላቀል እንደማትደግፍ አስታወቀች።የቱርክ ፕሬዜዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን ፤ ሀገራቸው ስዊድን እና ፊንላንድን ኔቶን በአባልነት የመቀላቀል እቅድ እንደማትደግፍ ገልፀዋል። ምንም እንኳን ፕሬዝዳንቱ በግልፅ ባያብራሩም የኖርዲክ ሀገራት የብዙ አሸባሪ ድርጅቶች መገኛ ናቸው ሲሉ ተናግረዋል። አንካራ ውስጥ ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት ኤርዶጋን ፥ " ስዊድን እና ፊንላንድን በሚመለከት ያለውን ሂደት እየተከታተልን ነው ፤ ነገር ግን በጉዳዩ ላይ አዎንታዊ አመለካከት የለንም " ብለዋል። ከዚህ ቀደም ኔቶ ግሪክን በአባልነት መቀበሉ ስህተት ነበር ሲሉም ተደምጠዋል። " እንደ ቱርክ ተመሳሳይ ስህተቶችን መድገም አንፈልግም " ሲሉ አክለዋል።
5፤ሲዳማ ቡና ጊዜያዊ ዋና አሰልጣኙን አሳውቋል፡፡ትላንት አመሻሹን ከአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ጋር የተለያየው ሲዳማ ቡና ጊዜያዊ ዋና አሰልጣኙን አሳውቋል፡፡ በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ23ኛ ሳምንት ጨዋታው በመከላከያ 5-3 የተረታው ሲዳማ ቡና ዋና አሰልጣኙ ገብረመድህን ኃይሌ ‘ክለቡ በጠበቀው የውጤታማነት መንገድ መሰረት እየተጓዙ አይደለም’ በሚል ከኃላፊነት ማንሳቱን አሳውቋል። የአሰልጣኙ ረዳት በመሆን የቆየው
ወንድማገኝ ተሾመ እስከ ውድድር ዓመቱ መጨረሻ ድረስ ክለቡን በዋና አሰልጣኝነት (ለሰባት ጨዋታዎች) እንዲመራ ተመርጧል፡፡ የቀድሞው የሲዳማ ቡና እና ሀዋሳ ከተማ የግራ መስመር ተከላካይ ወንድማገኝ እግርኳስን ካቆመ በኋላ የሲዳማ ቡና ከ20 ዓመት በታች ቡድን አሰልጣኝ በመሆን ያገለገለ ሲሆን ዘንድሮ ደግሞ የዋናው ቡድን ረዳት ሆኖ ያለፉትን ስምንት ወራት ሲሰራ ቆይቷል፡፡
• @ThinkAbyssinia •
4.2K views07:05