2023-07-03 11:12:17
‹‹እለ ይዘርኡ በአንብዕ ወበኃሤት የአርሩ፤ በልቅሶ የሚዘሩ በደስታ ይሰበስባሉ›› (መዝ.፻፳፭፥፭)
ስንዱ እመቤት በሆነች ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የወቅቶች አከፋፈል መሠረት ከሰኔ ፳፮ ቀን እስከ መስከረም ፳፭ ያለው ጊዜ ዘመነ ክረምት ይባላል፡፡
“ክረምት” የሚለው ቃል ‘ከርመ፣ ከረመ’ ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲሆን ትርጓሜውም ወርኃ ዝናም፣ ወርኃ ነጎድጓድ፣ ዘመነ ባሕር፣ ዘመነ ነጎድጓድ፣ ዘመነ አፍላግ፣ ዘመነ ጠል፣ ዘመነ ደመና፣ ዘመነ መብረቅ… ማለት ነው፡፡ (ጥዑመ ልሳን ያሬድና ዜማው) ይህ ወቅት ከትርጓሜው እንደምንረዳው የሰው ልጅን ጨምሮ ተንቀሳቃሽ ለሆኑ ፍጥረት ሕይወት ከባድ የሚሆንበት ግን ደግሞ ለመኖር የሚያስችለውን ልብሱንና ጉርሱን የሚያገኘው በክረምት አማካኝነት እንደሆነ ከጥቅሱ እንረዳለን፡፡
ዘመነ ክረምት፡- የዝናም፣ የዘርና የአረም ወቅት በመሆኑ ምድር በጠል ዝናም ትረካለች፡፡ ዕፅዋት አዝርዕትና አትክልት በቅለው፣ ለምልመው የሚያድጉበት፣ ምድር አረንጓዴ ለብሳ በሥነ ጽጌያት የምታሸበርቅበት ወቅት ቢሆንም በሀገራችን አብዛኛው የግብርና ሥራ የሚከወንበት ጊዜ ስለሆነ በላይ ዝናቡ በውስጥ ርኃቡ በታች ዳጡ ማጡ የሚፈትነበት የመከራ ወቅት ነው፡፡ ‹‹እለ ይዘርኡ በአንብዕ ወበኃሤት የአርሩ፤ ሶበሰ የሐውሩ ወፈሩ እንዘ ይበክዩ ወፆሩ ዘርኦሙ፤ ወሶበ የአትው መጽኡ እንዘ ይትፌሥሑ፤ በሔዱ ጊዜ ዘራቸውን ተሸክመው እያለቀሱ ተሰማሩ፤ በተመለሱ ጊዜ ግን ነዶአቸውን ተሸክመው ደስ እያላቸው ይመጣሉ›› በማለት ቅዱስ ዳዊት ይናገራል፡፡ (መዝ.፻፳፭፥፭) ‹‹…….ክረምት ነበርና ስለውርጩ ጽናት ይንቀጠቀጡ ነበር›› እንዳለ ዕዝራ፡፡ (ዕዝ. ካል. ፱፥፲፩)
ወርኃ ክረምት የክርስትና ምሳሌ ነው፤ በክረምት ወር ገበሬ ብርዱንና ዝናሙን ሳይሰቀቅ ለሥራ ይሰማራል፤ በጋው እንደሚመጣ የደከመበትን፣ ዝናቡንና ርኃቡን፣ ድጡን ማጡን የታገሠበትን የድካሙን ፍሬ እንደሚያጭድ፣ ዘጠኝ ወር በጋም ፍሬውን እንደሚመገብ አምኖ የክረምቱን መከራም ይታገሣል፡፡ ክርስቲያንም በዚህ ምድር ላይ የሚደርስበትን መከራ ሁሉ ይታገሣል፤ በጸጋ የሚቀበለው በዚያኛው ዓለም ስለሚያገኘው ተድላና ደስታ ነው፡፡ ‹‹በዚህ ዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ›› የሚለውን አምላካዊ ቃል ያውቃሉና፤ (የሐ.፲፮÷፳) ‹‹ዝግባውም የክረምት ዝናብ በእርሱ ላይ ካልወረደ ከሥሩ ይነቀላል›› እንደተባለው ያለዝናም ዝግባ፣ ያለመከራ ክርስትና እንደሌለ እንረዳለን፡፡ (፩ኛመቃ.፰፥፴፬)
አምላካችን እግዚአብሔር ለኖኅ በገባለት ቃል ኪዳን መሠረት በጋና ክረምቱ፣ ብርድና ሙቀቱ፣ ቀንና ሌሊቱ በተወሰነላቸው ጊዜ እየተፈራረቁ ለሰው ልጆች ጥቅም እንዲሰጡ አድርጓቸዋል፡፡(ዘፍ.፰፥፳፪)
ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ወቅቶችን መሠረት አድርጋ ጌታዋን አብነት አድርጋ በወቅቶች እየመሰለች ወንጌልን ታስተምራለች፡፡ እናም የክረምቱን ዝናም፣ ነጎድጓድ፣ ጭቃውን፣ ብርዱን፣ ጨለማውን፣ ጎርፉን ወዘተ በክርስትናው መከራ እየመሰለች ስታስተምር እንዲሁም በዘሩ ቃሉን፣ በልምላሜው ተስፋውን፣ በመከሩ ምጽአቱን፣ በፍሬው መንግሥተ ሰማያትን እየመሰለች ትሰብክበታለች፡፡ ለዚህም አብነቷ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ወጸልዩ ባሕቱ ከመ ኢይኩን ጉያክሙ በክረምት ወበሰንበት፤ ነገር ግን ስደታችሁ በክረምት በሰንበት እንዳይሆንባችሁ ለምኑ›› በማለት አስተምሯልና፡፡ (ማቴ.፳፬፥፳) ለምን ቢሉ ክረምት ላዩ ውኃ ታቹ ውኃ ነው፤ አያሸጋግርምና ሰንበትም ዕለተ ዕረፍት ስለሆነ መንገድ ቢስቱ የሚያመላክት አይገኝምና፤ አንድም ‹‹ዐርፋለሁ ባለበት ጊዜ ስደት ቢመጣ ከቀቢጸ ተስፋ ይደርሳልና በሰንበትና በክረምት እንዳይሆንባችሁ ጸልዩ›› አለ፡፡
ቤተ ክርስቲያን ወቅቶችን እንዲህ በመከፋፈል በወቅቱ ከሚታየው የተፈጥሮ ሁኔታ ጋር ምእመናን ሕይወታቸውን እንዲመረምሩና ለንስሓ እንዲበቁ አጥብቃ የምታስተምራቸው ለዚህ ነው፡፡ በተለይ ቅዱስ ያሬድ በድርሰቶቹ ከደመናው፣ ከዝናቡ፣ ከልምላሜው፣ ከአበቦች፣ ከፍሬው ወዘተ እያስማማ ልብን በሚማርክ ዜማ በብዙ መልኩ አስተምሮናል፡፡ ‹‹ደምፀ እገሪሁ ለዝናም ሶበ ይዘንም ዝናም ይትፌሥሁ ነድያን፤ ይጸግቡ ርኁባን፤ የዝናም ድምፅ ተሰማ፤ ዝናም በዘነመ ጊዜ ችግረኞች ይደሰታሉ፤ ረኃብተኞችም ይጠግባሉ›› ሲል ያሰናስለዋል፡፡
የክርስትናችን ክረምት አልፎ ለመከር እንድንበቃ፣ ስደታችን በሰንበትና በክረምት ሆኖብን በቀቢጸ ተስፋ እንዳንጠፋ፣ በቅጠል ወራት ሳይሆን በፍሬ ወራት እያለቀስን ተሰማርተን፣ ደስ እያለን እንድንመለስ አብዝተን እንጸልይ፡፡ ‹‹እነሆ ክረምት ዐለፈ፤ ዝናቡም አልፎ ሄደ›› እንዳለ ጠቢቡ ሰሎሞን የክርስትናችን ክረምት የመከራችን ዝናብ ከእኛ ላይ በቶሎ ያልፋል፡፡ (መኃ.፪፥፲፩)
አምላካችን እግዚአብሔር መከራና ችግሩን ያሳልፍልን፤ አሜን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!
ከማህበረ ቅዱሳን ዋናው ማዕከል ቴሌግራም ላይ የተወሰደ
@ortodoxtewahedo
3.3K viewsedited 08:12