2023-04-29 21:04:58
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
ጉዳዩ፡- በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ የፊታችን ግንቦት 2015 ዓ. ም. በሚካሄደው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ላይ ጳጳሳት እንዳይሾሙ ስለ መጠየቅ
በቅርቡ መንግሥታዊው ሥርዐት ፈጥሮት የነበረው ቤተ ክርስቲያናችንን የመከፋፈልና የማዳከም ተግባር ምን ያህል አደጋ ፈጥሮ እንደ ነበር ሁላችንም የምናስታውሰው ነው፡፡ ከፊታችን ግንቦት በሚኖረው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ አዳዲስ ኤጲስ ቆጶሳት እንዲሾሙ ከፍተኛ ፖለቲካዊ ግፊትና ጫና እየተደረገ እንደሆነ እንሰማለን፡፡ በሕገ ወጡ ሲመት ተሳትፈው ከነበሩትም በሲመቱ ውስጥ እንዲካተቱ ከፍ ያለ ፖለቲካዊ ፍላጎትና ግፊት መኖሩ ይሰማል፡፡
እኛ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ ምእመናን ይህ በፊታችን ግንቦት 2015 ዓ. ም. ላይ እንዲደረግ እየታሰበ ያለው ሲመተ ኤጲስ ቆጶሳት ለቤተ ክርስቲያናችን የማይበጅ ስለሆነ ቢያንስ ወደ ቀጣዩ ዓመት እንዲተላለፍ ቢደረግ ስንል እንጠይቃለን፡፡ ይህን ከምንልባቸው ብዙ ምክንያቶች መካከልም፡-
1) በቅርብ ጊዜ በተካሄደው ሕገ ወጥ ሲመት የተሳተፉት በቤተ ክርስቲያን ቀኖና መሠረት እንኳንስ ወደ ኤጲስ ቆጶስነት እንዲመጡ ሊደረጉ ይቅርና የተሳተፉባቸው ተግባሮች ከክህነትም የሚያሽሩ ከባድ ኢክርስቲያናዊ ተግባራት በመሆናቸው (በመማለጃ ኤጲስ ቆጶስ የተሾመ ይሻር፤ በዚህ ዐለም መኳንንት [ለሹመት] ቢረዳ ከእነርሱም ዘንድ ለቤተ ክርስቲያን ቢሾም ይሻር፤ እርሱና ግብረ አበሮቹ ሁሉ ይለዩ፡፡ . . . በተንኮል ቢሾምም የተለየ ነው፡፡ በእናንተም ዘንድ እንደ አረማዊ ይሁን፡፡ ከእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ይለይ፡፡ ፍትሐ ነገሥት 5 አንቀጽ ቁ. 173-176)
2) ባለፈው ተሞክሮ ያልተሳካውና ለጊዜውም ቢሆን ቆም ያለ የመሰለው ፈተና መልኩን ቀይሮ በውጭ የታጣውን በውስጥ የማስፈጸም ነገር ላለመኖሩ እርግጠኛ መሆን ስለማይቻል፤
3) በባለፈው ሲመት የተሳተፉት ግለሰቦች በእነርሱ ሕገ ወጥ ተግባር ምክንያት ከ50 በላይ ክርስቲያኖች እንዲገደሉና ብዙ ደም እንዲፈስ ያስደረጉ በመሆናቸው፤ ከዚህ የተነሣም ከእነዚህ መካከል ይሾም የሚባል ቢኖር ይህን ሰው በአባትነት ለመቀበል በእጅጉ የምንቸገር በመሆኑና በቤተ ክርስቲያን አንድነት ላይም ችግር ሊፈጥር ስለሚችል፤
4) አገራችን አሁን ካለችበት ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር፤
ስለዚህ ቅዱስ ሲኖዶስ የዚህን ዐመት ሲመተ ኤጲስ ቆጶሳት ጉዳይ እንዲያስተላልፈው ስንል በልጅነት መንፈስ እንጠይቃለን፡፡
ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሲኖዶሳዊት መሆኗ የታወቀ ነው፣ ሲኖዶሳዊት ማለት ደግሞ ከቅዱስ ፓትርያርኩና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳስት ጀምሮ እያንዳንዱ ምእመን ያለባት የሁላችን የሆነች ቤተ ክርስቲያን እንደ መሆኗ፣ ብፁዓን አባቶቻችን የባለፈውን ፈተና ከልጆቻችሁ ጋር በመሆን እንደ ተወጣችሁት አሁንም እኛ ልጆቻችሁ ለቤተ ክርስቲያናችን ያለንን ጭንቀት በአባትነታችሁ እንደምትረዱንና ጥያቄያችንን እንደምትቀበሉን እናምናለን፡፡
ቡራኬያችሁ አይለየን!
1.9K views18:04