#እንኩዋን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዓመታዊ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ +*" #ልደታ ለማርያም ድንግል "*+ #ኢያቄም ወሐና ወለዱ ለነ ሰማየ: ሰማዮሙኒ አስረቀት ለነ ፀሐየ:: " ኢያቄምና ሐና ሰማይን ወለዱልን: ሰማያቸው ደግሞ ፀሐይን አወጣችልን (ወለደች-አስገኘችልን) " =>የዓለማችን ወላጆች ነቢያት ሐዋርያትን: ጻድቃን ሰማዕታትን ወልደው ከብረዋል: ተመስግነዋል:: ኢያቄምና ሐና ግን ፍጥረት ሁሉ በአንድነት ቢሰበሰብ በእግሯ የረገጠችውን ትቢያ እንኩዋ መሆን የማይችል: የሰማይና የምድር ንግሥት: የእግዚአብሔርን እናት: እመቤታችን ማርያምን ወለዱልን:: +ኢያቄም ወሐና ለእግዚአብሔር የሥጋዌ አያቶቹም ተባሉ:: እስኪያረጁ ድረስ በመካንነት አዝነው ፀልየዋል:: ንጽሕናቸውና ደግነታቸው ተመስክሮላቸው ድንግል ማርያምን አግኝተዋል:: +እመቤታችን ከአዳም ስሕተት በሁዋላ ያለ ጥንተ አብሶ የተወለደች የመጀመሪያዋ ሰው ድንግል ማርያም ሆናለች:: (ኢሳ. 1:9) +ለጨለማው ዓለም የብርሃን መቅረዝ ሆና ትጠቅመን ዘንድ: አንድም ትንቢቱና ምሳሌው ይፈጸም ዘንድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዚህ ቀን: በሊባኖስ ተራራ ከ2,022 ዓመታት በፊት ተወልዳለች:: "ሙሽራዬ ሆይ! ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነይ" (መኃልይ. 4:8) =>ከነገደ ይሁዳ የሚወለድ ቅዱስ ኢያቄም የሚባል ደግ ሰው ከነገደ ሌዊ (አሮን) የተወለደች ሐና የምትባል ደግ ሴት አግብቶ: በሕጉ ጸንተው: በሥርዓቱ ተጠብቀው ይኖሩ ነበር:: ነገር ግን በዘመኑ ሰዎች ልጅ የላችሁም በሚል ይናቁ ነበር:: +ኦሪታውያን ልጅ የሌለውን "ኅጡአ በረከት-ከጸጋ እግዚአብሔር የራቀ" ነው ብለው ያምኑ ነበር:: ኢያቄምና ሐና ልጅ እንዲሰጣቸው ሲያዝኑ: ሲጸልዩ ዘመናቸው አልፎ አረጁ:: እነሱ ግን የሚያመልኩት የአብርሃምና ሣራን አምላክ ነውና ተስፋ አልቆረጡም:: +የለመኑትን የማይነሳ ጌታ በስተእርጅናቸው ድንቅ ነገርን አደረገላቸው:: አንድ ቀን እርግቦች ከጫጩቶቻቸው ጋር ሲጫወቱ የተመለከተች ቅድስት ሐና ፈጽማ አለቀሰች:: "እንስሳትና አራዊትን: እጽዋትን ሳይቀር በተፈጥሯቸው እንዲያፈሩ የምታደርግ አምላክ ምነው ሐናን ድንጋይ አድርገህ ፈጥረሃታልን?" ብላ አዘነች:: +ይህን የተመለከተ ቅዱስ ኢያቄም ወደ ተራራ ወጥቶ ሱባኤ ያዘ:: ለ40 ቀናትም ሲጸልይና ሲማለል ቆየ:: በ40ኛው ቀን 2ቱም ሕልምን ያልማሉ:: እርሱ:- ነጭ ርግብ ሰማያትን ሰንጥቃ ወርዳ: በሐና ቀኝ ጀሮ ገብታ: በማሕጸኗ ስትደርስ አየ:: +እርሷ ደግሞ:- የኢያቄም በትር አብቦ: አፍርቶ: ጣፋጭ ፍሬውን ሰው ሁሉ ሲመገበው ታያለች:: ቅዱስ ኢያቄም ከሱባኤ እንደ ተመለሰ ያዩትን ተጨዋውተው "ፈቃደ እግዚአብሔር ይሁን" አሉ:: ለ7 ቀናትም በጋራ እግዚአብሔርን ሲለምኑ ሰነበቱ:: +በ7ኛው ቀን (ማለትም ነሐሴ 7) መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ክንፉን እያማታ ወደ እነርሱ ወረደ:: "ዓለም የሚድንባት: የፍጥረት ሁሉ መመኪያ የሆነች ልጅ ትወልዳላችሁ" ብሏቸው ተሠወራቸው:: እነርሱም ደስ ብሏቸው እግዚአብሔርን አመሰገኑ:: +እንደ ሥርዓቱም አብረው አድረው እመ ብርሃን ተጸነሰች:: "ኦ ድንግል አኮ በፍትወተ ደነስ ዘተጸነስኪ . . . ድንግል ሆይ! ኃጢአት ባለበት ሥጋዊ ፍትወት የተጸነስሽ አይደለም" እንዳለ ሊቁ:: (ቅዳሴ ማርያም) +"ለጽንሰትኪ በከርሥ: እንበለ አበሳ ወርኩስ: ወለልደትኪ እማሕጸን ቅዱስ . . ." "ድንግል ሆይ! መጸነስሽ ያለ በደል (ያለ ጥፋት) ነው: የተወለድሽበት ማሕጸንም ቅዱስ ነው . . ." (መጽሐፈ ሰዓታት, ኢሳ. 1:9) +እመቤታችን ነሐሴ 7 ቀን ተጸንሳ ግንቦት አንድ ቀን ተወልዳለች:: =>የእመቤታችን የዘር ሐረግ:- *አዳም-ኖኅ-አብርሃም-ይስሐቅ-ያዕቆብ= *በእናቷ:- -ሌዊ-ቀዓት-እንበረም-አሮን-ቴክታና በጥሪቃ-ሔኤሜን-ዴርዴን-ቶና-ሲካር-ሔርሜላና ማጣት-ሐና:: *በአባቷ በኩል:- -ይሁዳ-ፋሬስ-ሰልሞን-ቦኤዝ-እሴይ-ዳዊት-ሰሎሞን-ሕዝቅያስ-ዘሩባቤል-አልዓዛር-ቅስራ-ኢያቄም ይሆናል:: +ለጨለማው ዓለም የብርሃን መቅረዝ ሆና ትጠቅመን ዘንድ: አንድም ትንቢቱና ምሳሌው ይፈጸም ዘንድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም: በሊባኖስ ተራራ ከ2,026 ዓመታት በፊት ተወልዳለች:: =>የእመቤታችን ድንግል ማርያም ጣዕሟ: ፍቅሯ: ጸጋዋና በረከቷ ይደርብን:: =>ግንቦት 1 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት= 1.እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም (ልደታ) 2.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና 3.ቴክታና በጥሪቃ 4.አባ ሕርያቆስ ዘሃገረ ብሕንሳ http://t.me/ortodoxtewahedo 6.3K viewsedited 18:03