2023-07-04 14:21:50
ማኅበረ ቅዱሳን በትግራይ ክልል አስቸኳይ ሰባዊ ድጋፍ እንዲደረግ ለኦርቶዶክሳውያንና የሚመለከታቸው አካላት ጥሪ አቀረበ።
የማኅበሩ ዋና ጸሐፊ መምህር ዋሲሁን በላይ ዛሬ ሰኔ26/2015 ዓ.ም ረፋድ መግለጫ ሰጥተዋል።
+++++++++++++++++++++++++++++++++
"አብነት ት/ቤቶች ተበትነዋል፤ ገዳማትና አድባራትም ከፍተኛ ማኅበራዊ ድጋፍ ይፈልጋሉ" ያሉት ዋና ጸሐፊው በርካታ ታላላቅ ገዳማት፣ማስመስከሪያ ጉባኤ ቤቶች፣ በርካታ ሊቃውንት እና በርካታ ምእመናንን ያሉበት በመሆኑ በተለይም ኦርቶዶክሳውያን አስቸኳይ ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ማኅበረ ቅዱሳን በጦርነቱ፣ በግጭት እና በተፈጥሮ አደጋ ለተጎዱ ለቦረና፣ ሻሸመኔ፣አዲስ አበባ ዙርያ፣ ሰሜን ሸዋ፣ ሰላሌ ፍቼ፣ አምቦ፣ ዋግሕምራና ጎንደር አዘዞ ለሚገኙ የተለያዩ አህጉረ ስብከቶች በያዝነው ዓመት ድጋፍ ማድረጉንም አስታውሰዋል።
በጦርነቱ ወቅት ቀይ መስቀልን በመሰሉ በዓለም አቀፍ ተቋማት በኩል ድጋፍ ሲልክ መቆየቱንም ተናግረዋል።
ከጦርነቱ በኋላ ከወር በፊትም ትግራይ ክልል ለሚገኙ ለ10 ገዳማትና አብነት ት/ቤቶች በባንክ አካውንቶቻቸው ብር በመላክ ለመርዳት ሞክረናል ያሉት ዋና ጸሐፊው ነገር ግን ካለው ችግር አሳሳቢነት አንጻር በማኅበሩ አቅም ብቻ የሚቻል ባለመሆኑ ጥሪ ለማቅረብ ተገደናል ብለዋል።
መምህር ዋሲሁን በላይ አክለውም በአከባቢው አስተዳደራዊ ችግር እንዳለ ይታወቃል ነገር ግን ልዩነቶች በአባቶች ውይይት ይፈታሉ ብለን እናምናለን ሲሉ ተናግረዋል።
ዘላቂ መፍትሔ እስኪገኝም ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች ያሉ ብፁዓን አባቶች በዚህ በጎ ተግባር ተሳታፊ ብቻ ሳይሆን ባለቤት በመሆን እንዲያስተባብሩም ጠይቀዋል።
ይህ የድጋፍ ዘመቻ ዋግምኽራ ሀገር ስብከትን እንደሚያካትት የገለጹት ዋና ጸሐፊው ማንኛውም ድጋፍ ማድረግ የሚፈልግ አካል በማኅበሩ በኩል ወይም አከባቢው ባለው የቤተ ክርስቲያን ሕጋዊ መዋቅር ወይም በቀጥታ ለገዳማትና አብነት ት/ቤቶች መለገስ እንደሚችሉ ገልጸዋል።
ይህ ዘመቻ እንደተጠናቀቀም በባለሙያዎች የተጠና ሪፖርት እንደሚቀርብ ታውቋል።
በትግራይ ክልል ዓለም አቀፍ እርዳታ ሰጭ አካላት ከወጡ በኋላ የከፋ ችግር ውስጥ መሆናቸውን በተለያዩ ሚዲያዎችና ተቋማት እየተገለጸ መሆኑ ይታወቃል።
@ortodoxtewahedo
2.7K viewsedited 11:21