2023-01-07 21:03:18
“ስጦታው ደርሶሃል?”
ልደቱ ቤተ መንግሥት አናውጧል ፤ ቤተ ክህነት በጥብጧል፤ በሜዳ የነበሩ እረኞችን በደስታ አስደንግጧቸዋል ፤ ሰማይና ምድርን በአንድነት አስዘምሯቸዋል ፤ ሰብአ ሰገል አገር አቆራርጠው ሊሰግዱለት ተጒዘዋል። ንጉሥ ሄሮድስ ሊገድለው ሤራ ይጠነስስ ነበር። መጽሐፍ ዐዋቂዎችም ስለ መሲሑ ልደት ቦታ ጥቅስ ጠቅሰው ወደየቤታቸው ተመለሱ።...ገሚሱ በደግነቱ ሲያምን ገሚሱ እንደ “አሳች” ፈረጀው።
ይኸ መናወዝ ላለፉት ኹለት ሺህ ዓመታት እንደ ቀጠለ አለ። በተወሰኑ ሰዎች ታላቅ የምግባር መምህር ተደርጎ ተወድሷል፤ በሌሎች ደግሞ “ጻድቁ ነቢያቸው ” ኾኗል። መናፍቅ ብለው ራሳቸውን ያሳመኑም ነበሩ ፤ አሉም። ነገር ግን “እርሱ እንደ ተናገረው እንዲሁ የእግዚአብሔር ልጅ መሲሑ ነው ” በማለት ያመኑበትና በጌትነቱ ስር ወድቀው የሰገዱ እልፍ አእላፋት ሞልተዋል። በአጠቃላይ ማንም ይኹን ማን ፥ ስለ ኢየሱስ አንድ ነገር ሳይል እንዳያልፍ ሰማይ ወስኗል፤ ኢየሱስ “ጥያቄ” ነው።
[ይኼ አንቀጽ የተቈረሱ ነፍሶች መጽሐፍ ውስጥ ጸሐፊው የመሲሑ መምጣት ከመደበኛው ክስተት የተለየና አነጋጋሪ መሆኑን ከሚያስረዳበት ክፍል የተወሰደ ነው]
ጸሐፊው ይቀጥልና ከላይ አነጋጋሪ ጥያቄ ያለውን - መልሱም ራሱ ነው ይለናል። (እንዴት አይነት ማራኪ አገላለጽ ነው?)
እግዚአብሔር የዓለምን ጥያቄ ሁሉ የመለሰው በልጁ በክርስቶስ በኲል ነው። እርሱ ካልመለሰልን ሕይወታችን አልተመለሰም ፤ ዘላለማችን ተስፋ የለውም ፤ ነፍሳችን ተቅበዝብዛ መጥፋቷ ነው።
ለሕይወታችን መትረፍ የሚያስፈልገው መድኃኒቱ መጠን የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስን ያህል ነው ።
***
ዛሬም፤
በመልአኩ የተበሰረው “ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች ” አዋጁ ትኩስ ነው። በሰብአ ሰገል አምልኮ ውስጥ የተመሠጠረው የልደቱ ፋይዳ ሕያው ነው። በእናቱ ማርያም ቅኔ ውስጥ “አምላኬ...መድኃኒቴ” ያለቺው እርሱ የፍጥረታት ሁሉ ጌታና አዳኝ ነው።
በዚህ “መሲሕ” በኩል ለሚመጡና በስሙም ለሚያምኑ የሰው ልጆች ሁሉ “የእግዚአብሔር ልጅ” እንዲሆኑ ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል። ሐዋርያው ጴጥሮስ ጮክ ብሎ እንዳለው፡- መዳን በሌላ በማንም የለም! እንድንበት ዘንድ ከሰማይ በታች የተሰጠን ሌላ ስምም - አዳኝም - ምግባርም - አቋራጭ መንገድም የለም!
እግዚአብሔርም ዓለሙን የወደደበትን ጥግ ሊያሳይ አንዲያ ልጁን ሰጠን። በውልደቱ፣ በትምህርቱ፣ በተግባሩ፣ በሞትና ትንሣኤውም ከርሱ ጋር ሕይወትና ተስፋን ተቀበልን። የልደት መታሰቢያውም ትርጉም የሚኖረው ወደ ሰጪው አሻቅበን “የላክልኝ ውዱ ስጦታህ ደርሶኝ ተቀብያለሁ፤ አመሰግናለሁ” ማለት የቻልን እንደሆነ ብቻ ነው!
ይኼ የሰማይ ውድ ስጦታ ደርሶሃል?ደርሶሻል? የደረሰው ከልቡ ያመስግን - ያልደረሰው በነጻ ይቀበል!
እንኳን ለብርሃነ ልደቱ አደረሳችሁ።
ፍጹማን ግርማ
@nazrawi_tube
690 viewsΒενιαμίν, 18:03