Get Mystery Box with random crypto!

ልደቱ --የለውጥ አብነቱ የዚህ ምድር ቋጥኝ የደም ግብር ምሱ ነው፤ ድንጋዩ ሁሉ፥ አፈሩ ሁሉ ሲ | ናዝራዊ Tube

ልደቱ --የለውጥ አብነቱ

የዚህ ምድር ቋጥኝ የደም ግብር ምሱ ነው፤ ድንጋዩ ሁሉ፥ አፈሩ ሁሉ ሲቀለብ የኖረው የአዳምን ልጆች የደም ዥረት ነው። የዓለማችን ቋሚ መልክ ጠብ ነው።ከዚያች የገነት ደጅ ጠብና ሽሽት በኋላ ሰብአውያን ግጭትና ቁርሾ፥ሁካታና ቱማታ መታወቂያችን ሆኗል። የሰማይ መላእክት አፍ አድጧቸው ቢናገሩ ምን ይሉን ይሆን?
"ውይ ! እነዚያ ሁከተኞች፥ እኒያ የሰላም ባይተዋሮች፥እኒያ የጠብ ዐርበኞች፥ ወርቅ ሲሰጧቸው ጠጠር የሚወረውሩ ሞገደኞች"ሳይሉን አይቀርም።እኔ የሰው ልጅ የምጣላው ባጣ፥ ዐናቴ ላይ ከበቀለው ጉተና ጋር፥ጉልበቴ ላይ ከፈረጠመው ሎሚ ጋር፥ከራሴውም ጋር ቢሆን ጠብ ማብቀሌ አይቀርም።
ቢርበኝ፥ ብጠግብም መዝናኛዬ ጠብ ነው። ታላላቅ መንግሥታት ፥ታናናሽ መንግሥታት ፥ የተማሩ ሕዝቦች፥ ማይማን ብሔረ ሰቦች፥ ሁሉም የሠለጠኑት ጠብ በመለኰስና ልኵሱን በማፋፋም ነው።

የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት የሰላም ልደት ነው።
"ስሙም ድንቅ መካር ፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል"....."ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም፥ሰላምም በምድር".....ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጦር በተሰበቀበት፥ የፈረስ ኮቴ በጎደፈረው ምድር ላይ የሰላም ባንዲራ ተከለ። ሃሌሉያ! መጀመሪያ ከአባቱ ጋር፥አያይዞም ከራሳችን፥ ከሰው ሁሉ ጋርም አስታረቀን። እርሱ የሰላም መንገድ ጠቋሚ ብቻ አይደለም፤ የሰላም ሰባኪም ብቻ አይደለም።" እርሱ ሰላማችን ነው።" በሰው ጥበብ ና ጉልበት የማይበቅል ሰላም ምንጭ ሆኖ ኢየሱስ ተወለደልን።

እንኳን ለብርሃነ ልደቱ አደረሰን።

"መስተአየት"ገጽ 133/4
ጋሽ ንጉሤ ቡልቻ
@nazrawi_tube