2023-01-26 20:38:11
Q: ይኼኛው አካኼድ ከድጥ ወደ ማጥ መሆኑን አይተናል። አሁንስ ብንመለስ ምን ይሆናል?
“ወይስ የእግዚአብሔር ቸርነት ወደ ንስሐ እንዲመራህ ሳታውቅ የቸርነቱንና የመቻሉን የትዕግሥቱንም ባለጠግነት ትንቃለህን?” (ሮሜ. 2:4)
በክርስትና እምነት ከሚገኙ መንፈሳዊ ልምምዶች አንዱ ኃጢአትን የመናዘዝና ተጸጽቶ በንስሓ የመመለስ ልምምድ ነው። ንስሓና መመለስ አንዴ ለሁሌ ሳይሆን በቃሉ መነጽር ሕይወታችንን እየፈተሽን አካኼዳችንንም በመንፈሱ ሚዛን እየመዘንን በየጊዜው የምንፈጽመው ክርስቲያናዊ የእርምት እርምጃ ነው።
ንስሓ በኔ እምነት ምዕመናን ኃጢአታቸውን ተናዝዘው፥… በድርጊታቸው ተጸጽተው፣ … ወደ ፊት ሌላ ጊዜ ወደዚያ ትፋት ላይመለሱ ወስነው፥… የጌታን ምሕረትና ይቅርታ ለመቀበል ወደ ፊቱ ራሳቸውን ዝቅ አድርገው የሚቀርቡበት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሥርዓት ነው።
ንስሓ በተለያዩ ጥፋቶች ውስጥ የሚገኝ ሰው ራሱን የሚያነጻበት ሻወር ነው። የልጁ የክርስቶስ ኢየሱስ ደም ከኃጢአት ሁሉ እንደሚያነጻ ያመነ ሰው ከቁጭትና ከሕሊና ጸጸትም የሚጸዳበት ሳሙና ነው ንስሓ። ንስሓ ሁለንተናን ከዕድፍና ከጉድፍ ያጠራል። “ኃጢአቱን የሚሰውር አይለማም፤ የሚናዘዝባትና የሚተዋት ግን ምሕረትን ያገኛል። (ምሳ. 28:13) በተባለው መሠረት መናዘዝ፣ መመለስ፣ መተው በንስሓ ውስጥ አሉ።
ባለንበት ዘመን በምትገኝ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከመቼውም በላይ ዓለማዊነት፣ አመጸኝነት፣ ግፈኝነት፣ ጨካኝነት፣ ጠላትነት፣ ቂም በቀለኝነት፣ ርኩሰት፣ ዝሙት፣ መዳራት፣ ስካር … ሁሉ ልንደብቀው በማንችልበት ሁኔታ ሞልቶ ወደ ውጪ እየፈሰሰ ነው። በዚህም ምክንያት ትዳር እየፈረሰ፣ ኑሮ እየታመሰ፣ ሕይወት በብዙ ውጥንቅጥ ውስጥ እየገባ ነው። ማኅበረሰብ ገብቶ በማያውቀው የሕይወት ዝቅጠት ውስጥ ገብቶአል። በዘመነ ኤሊ ክብር በሌለበት ኢካቦድ ሆኖ እየተሸነፈችና እየተማረከችም እሥራኤል እልልታዋ ደማቅ ጩኸቷ ከፍተኛ እንደነበረ ያንን እየደገምን ኖረናል።
የልጅነትና የቃል ኪዳን ሚስታቸውን ፈትተው ልጆቻቸውን ሜዳ ላይ በትነው ሌላ ሚስት ያገቡትን ሰዎች በአደባባይ የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት መሪ ወደ ማድረግ ተደርሷል። አስደንጋጭ የነበሩ ነገሮችን ለምደን ቤተኛ አድርገን ኖረናል። በጣም ግዴለሾች ሆነናል። ከጋብቻ በፊት በሚደረጉ ወሲባዊ ልምምዶች ውስጥ ከርመው እያስረገዙና እያስወረዱ መሆናቸው እየታወቀ ሰዎችን ማስጨፈር ስለቻሉ ብቻ በታላላቅ የአደባባይ ላይ ኮንፈራንሶች የሚጋበዙ አገልጋዮች ቁልል ናቸው። ቁጥር አይገልጻቸውም። የወንጌል አማኞች የምናምነው ወንጌል የቱ እንደሆነ በሚያጠያይቅ ደረጃ በርዘናል። ዝሙት በመዝሙር ካባ ይሸሸጋል።
በርግጥ አስተውለን ከሆነ ራሳቸውን ወደ እግዚአብሔርነት ያጠጋጉ አስተምህሮዎችን አምጥተውብናል የምንላቸው “መንፈስ ነን” ባይ የርኩሰት መምህራኖች ከዘሩት መራራ ዘር አንዱ “በሥጋ የምንፈጽመው ማንኛውም ነገር ከሟችና ፈራሽ ሥጋ ጋር ይቀራል እንጂ መንፈሳችንን አያረክስም” የሚል ነው። ይኼው አደናቃፊ ክፉ የአጋንንት ትምህርት መናዘዝንና ንስሓን ከቤተ ክርስቲያን አካባቢ አርቆአል። እነዚህ የሰይጣን መልዕክተኞች ፍልፈል ላይ እንሰት ተካይ ተላላ ትውልድ አፍርተዋል።
ቃሉ ግን በግልጽ “በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው።” (1ዮሐ. 1:9) ይላል። የወንጌል አማኞች ነን የምንል ወገኖች በዓለም ዘንድም የነበረንን ክብርና ሞገስ ባጣንበት በዚህ ሁኔታ አማኙ ማኅበረሰብ ንስሓ ገብቶ ክርስቶስን ወደ መምሰል ተልዕኮውንም ወደመፈጸም እንዳይመለስ በውድቀቱ እንዲጸና ካደረጉት ከንቱ አስተምህሮዎችና ልምምዶች ለመውጣት ከኃጢአታችን መናዘዝና በንስሐ መመለስ አማራጭ ሳይሆን ግዴታ ነው። ጥያቄዬ ወደዚያ የቀደመው ልምምድ ብንመለስ ምን ይሆናል? የሚል ነው።
ሰዎች በኃጢአት ሲገኙ ወይም ድንገት ሲሰናከሉ ተናዝዘው በንስሓ ከመመለስና ለቃሉ ሥልጣን ከመታዘዝ ይልቅ አስጨፋሪና አዝናኝ ዜማ ባላቸው ዝማሬዎች ሥር ራሳቸውን ሸሽገው ምንም እንዳልተፈጠረ በማስመሰል እልልታቸውን አድምቀው ተጯጩኸው ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ የሚያደርግ ልምምድ እነዚህን አዳዲስ #ቃል አልባ ቃል አውጪዎችን ተከትሎ ወደ ወንጌላውያን አማኞች ኅብረት ሰተት ብሎ ገብቶአል። ይኼንን ከንቱ ልምምድ ጠራርገን ለማስወጣት ወደ ቃሉ ልምምድ መመለስ የግድ ነው።
የንስሓ… የጸጸትና የመመለስ ሕይወት ከሌለን ራሳችንን እያሳትን፣ ምንም ሳንሆን የሆንን እያስመሰልን፣ እንደተለሰነ መቃብር ውጪውን አሳምረን በውስጣችን ግን በስብሰን መቅረታችን አይቀርም። “… ነገር ግን ንስሐ ባትገቡ ሁላችሁ እንዲሁ ትጠፋላችሁ።” (ሉቃ. 13:3) ተብሏልና። “ሊቆም አይችልም ነገሬ፣…” “ጩኸት አለኝ እኔስ ጩኸት…” “ነገር አለኝ እኔስ ነገር…” በሚሉና በሌሎችም ከዝሙትና ከመዳራት ከስካርም መልስ በተገኙ የማደናገሪያ አስጨፋሪ ዜማዎች መዝለል አዋጭ አካኼድ አይደለም። አዎን አይደለም። እኔ በበኩሌ በነዚህ ዘፈኖች መዝለል ካቆምኩ ሰነበትኩ። ምንጩን ልይቻለሁ። ወደ ቀደመው ከጥፋት በንስሓ የመመለስ ልምምድ መመለሱ ይሻላል።
“ወይስ የእግዚአብሔር ቸርነት ወደ ንስሐ እንዲመራህ ሳታውቅ የቸርነቱንና የመቻሉን የትዕግሥቱንም ባለጠግነት ትንቃለህን?” (ሮሜ. 2:4)
ወርቅነህ ኮይራ
@nazrawi_tube
@nazrawi_tube
1.7K viewsΒενιαμίν, 17:38