Get Mystery Box with random crypto!

ጳውሎስ ስለቈላስይስ አማኞች የሰማው በወንጌል አጋሩ ከነበረው ኤጳፍራ ነበር። ለእነርሱ መንፈሳዊ ሕ | ናዝራዊ Tube

ጳውሎስ ስለቈላስይስ አማኞች የሰማው በወንጌል አጋሩ ከነበረው ኤጳፍራ ነበር። ለእነርሱ መንፈሳዊ ሕይወት ጤንነት እንዲሁም ፍሬያማነት ዘወትር በመንፈስ ይጋደል ነበር። "ስለ እናንተና በሎዶቅያ ስላሉት እንዲሁም በአካል አይተውኝ ስለማያውቁ ሁሉ ምን ያህል እየተጋደልሁ እንደሆነ እንድታውቁ እፈልጋለሁ . . ." (ቈላስይስ 2:1-2)። መጋደል (ἀγῶνα agōna - agonize) የሚለው ቃል ከልብ የሆነ፣ ያማያቋርጥ የውስጥ ብርቱ መሻትንና ያልተቆጠበ ታጋትን ያሳያል። ይህም የሐዋርያው ጳውሎስ ከጌታ ለተቀበለው አገልግሎትና ለቤተ ክርስቲያን ያለውን የመሰጠት ጥልቀት ያሳየናል።

ጳውሎስ የሚጋደለው ስለ ምንድነው?

1) ልባቸው በፍቅር እንዲጽናና - በሰሙት ወንጌል ጸንተው እንዲኖሩ፣ እንዳይናወጡ እንዲሁም በየጊዜው እግዚአብሔር በማወቅ እንዲያደጉ ይጸልያል፤ ደግሞም ያስተምራቸዋል። "ጌታ ክርስቶስ ኢየሱስን እንደ ተቀበላችሁት እንዲሁ በእርሱ ኑሩ" (2:6)።

2) እርስ በእርስ ያላቸው ኅብረት በፍቅር የተሳሰረ እንዲሆን። ለኤፌሶን አማኞች፣ “ይልቁንም እውነትን በፍቅር እየተናገርን፣ ራስ ወደ ሆነው ወደ እርሱ በነገር ሁሉ እናድጋለን፤ እርሱም ክርስቶስ ነው፤ ከእርሱም የተነሣ፣ ** አካል ሁሉ በሚያገናኘው ጅማት እየተያያዘና እየተጋጠመ፣ እያንዳንዱ ክፍል የራሱን ሥራ እያከናወነ በፍቅር ያድጋል *፤ ራሱንም ያንጻል።” (ኤፌ. 3:15-16)” በማለት እንደጻፈው፣ ለቈላስይስ የነበረውን ተመሳሳይ ታጋት እንመለከታለን።

3) ቤተ ክርስቲያንን አያይዞ ያጸናው ፍቅር መሆኑን እንዲረዱ - አማኞች የተሳሳሩበት ዘላላማዊ የሆነው የክርስቶስ ፍቅር ነው! ፍጹም የሆነውን የመረዳት ብልጥግና አግኝተው የእግዚአብሔር ምስጢር የሆነውን ክርስቶስን እንዲያውቁ - ይህ የፍቅር ትስስር የእግዚአብሔር ቀጥተኛና ሙሉ መገለጥ የሆነውን ክርስቶስ በማወቅ ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይገባዋል።

4) በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ የተገኘውን ድነት የማይጨመርበት፣ ሙሉ የሆነ፤ ዘላለማዊና የአንድ ጊዜ ሥራ መሆኑን የበለጠ እንዲያውቁ። ይህን ማወቅ ብቻ ነው ሰውን ምሉዕ (complete) የሚያደርገው። ይህ ፍቅር ከስሜት ያለፈና ክርስቶስን በማወቅ ላይ ያረፈ ነው። “ፍቅራችሁ በጥልቅ እውቀትና በማስተዋል ሁሉ በዝቶ እንዲትረፈረፍ (overflow) እጸልያለሁ።” (ፊል. 1:9)። ክርስቶስ በልባቸን በማደሩ ዐይናችን በርቷል፤ ይህን የሚተካ ዕውቀት የለም! ክርስቶስ ሙሉ ነው! ምክንያቱም፣ “የተሰወረ የጥበብና የዕውቀት ሀብት ሁሉ የሚገኘው በእርሱ ዘንድ ነውና”። እግዚአብሔር ራሱን በክርስቶስ ገልጧል። ሰው እንዴት ከኀጢአት ድነት እንደሚያገኝ እግዚአብሔር ያዘጋጀው መንገድ አሁን እውን ሆኗል። ምስጢር አይደለም - እርሱ በክርስቶስ እቅዱን ሁሉን እውን አድርጓል። “በክርስቶስ ያቀደውንም የፈቃዱን ምስጢር እንደ በጎ ሐሳቡ እንድናውቅ አደረገ። በዘመን ፍጻሜ ይሆን ዘንድ ያለው ሐሳቡ በሰማይም በምድርም ያሉትን ነገሮች ሁሉ ራስ በሆነው በክርስቶስ ሥር ለመጠቅለል ነው: (ኤፌ. 1:9-10):: ነቢያትና ጻሕፍት የመሰከሩለትና በተስፋ የተጠበቀው መድኅን ክርስቶስ ተገልጧል።

5) እርሱን ማወቅ ለሰው ልጅ እንቆቅልሽ ሁሉ መልስ መሆኑንን እንዲረዱ! ሰውን ከኀጢአት ጨለማ፣ ከተለየበት የእግዚአብሔር መንገድና ከሚሄድበት የዘላለም ሞት የሚያስጥል ሌላ ልዩ ዕውቀት የለም! ክርስቶስ ብቻ - እርሱን ማወቅ እግዚአብሔርን ማወቅ ነው! ይህን መረዳት የሚተካ ሌላ የተሻለ የተሰወረ ዕውቀት “hidden” (apocryphi) የለም! ስለዚህ ከዚህ መረዳት “ማንም ንግግር በማሳመር (enticing words) እንዳያታልላችሁ (እንደ ጎደላችሁ፣ የሆነ ተጨማሪ ሌላ ዕወቀት እንደሚያስፈልጋችሁ በማሳመን የእምነታችሁን መሠረት እንዳይሸረሽር) ይህን እነግራችኋለሁ። ምንም በሥጋ ከእናንተ ርቄ ብገኝ በመንፈስ ከእናንተ ጋር ነኝና በሥርዐት (በተገለጠው ክርስቶስና በቅዱሳን ኅብረት በመሰጠት፣ በትጋትና በጽናት እያደገ በሚሄድ ሕይወት) መኖራችሁንና በክርስቶስ ያላችሁን ጽኑ እምነት (ከክርስቶስ ጋር አንዲሁም እርስ በእርስ) እያየሁ ደስ ይለኛል"።

ለእኛም ክርስቶስን በማወቅና በማሳወቅ የማያቋርጥ የማደግ ተጋድሎ ይሁንልን። አሜን!
Dr. Girma Bekele
@nazrawi_tube