2023-01-05 10:04:44
አእምሯችንን ከ"አዲሱ ሃይማኖት" እሳቤዎች እንጠብቅ!
የአኗኗር ብልሃት አሰልጣኝ ወይም "ላይፍ ኮች" ነን የሚሉቱ ዘመነኞቹ የአነቃቂ ንግግር (ሞቲቬሽናል ስፒች) ባለሙያዎች ወይም በተገቢው ስማቸው የአዲሱ ሃይማኖት ሰባኪያን "የእኛ የሰው ልጆች ትልቁ ችግር የአምስቱ የስሜት ህዋሳታችን ጫጫታ ነው።" ይላሉ። ጫጫታውና ረብሻው ከዚህ ዓለም ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ካለውና በጊዜና በቦታ ከተወሰነው ንቁው የአእምሯችን ክፍል ጋር የተያያዘ ሰለሆነ እርሱን ችላ ብለን በከፊል ብቻ ንቁ በሆነው የአእምሯችን ክፍል ላይ ብናተኩር፣ ወደዚያ ጠልቀን ብንገባ ከግርግሩ መደበቂያ የሚሆን አንዳች ጉድባ፣ ፍሰሃ የሞላበት አንዳች ሰርጥ እናገኛለን ይላሉ። እውነተኛው ማንነታችን የሚገኘው በፍዙ የአእምሯችን ውስጥ እንዳለ ይሰብካሉ። ፍለጋውን "ሰልፍ ሪያላዜሽን" ይሉታል።
በእነዚህ ሰዎች አስተምህሮ ውስጥ ስሙ በጣም ጎልቶ የሚጠቀስ ኤክሃርት ቶሌ የሚባል ጉሩ ወይም መምህር አለ። የሰውዬው ትምህርት ሃይማኖታዊ ወይም መንፈሳዊ ነው። በኢቢ ኤስ ቴሌቪዥን የዳጊ ሾው መርሃ ግብር ሆስት የሆነችው እንስት አብዛኛው እሳቦቶች የተቀዱት ከዚህ ሰው እንደሆነ በሰይፉ ፋንታሁን ሾው ላይ ቀርባ የተናገረችውም በቅርቡ ነው። አብዛኞቹ እኝግዶቿ የዚህ ነገር ዝንባሌ ያላቸው መሆኑን ግን ቀድሞውንም ይታወቃል። ልጅት የኤክሃርት ቶሌ ደቀ መዝሙር መሆኗን በይፋ ሳትናገር ነው ቀስ በቀስ ዙሩን እያከረረች የመጣችው። መጻሕፍቶቹን ማንበብ፣ ትምህርቶቹን ማድመጥ ብቻ ሳይሆን ቡራኬውን ለመቀበል ጭምር ወዳለበት ሀገር ተጉዛለች።
በዳዊት ድሪምስ መድረክ ላይ ራሷን ስትሟሟቅ የሰነበተችው ዳግማዊት ክፍሌ በቅርቡ ደግሞ የኗኗር ብልሃት አሠልጣኝነትን (ላይፍ ኮች) ካባ ደርባ በግሏ ሥልጠና ለመስጠት መስታወቂያ ባወጣችበት ጥቂት ጊዜ ውስጥ ሦስት ሺህ ተመዝጋቢዎችን አግኝታለች። ሰይፉ ፋንታሁንም ይኼንኑ በግርምት ሲያነሳው ነበር። እርሱም ሆነ ብሎ ትቶት እንጂ በዚህ ሥልጠና አላባውያን ላይ ሊነሱ የሚገቡ ጥያቄዎች መኖራቸው አይጠፋውም ነበር። ዳግማዊት የኤርካቶሌን መንፈሳዊ አስተማሪነት እየነገረችው እንኳ በዚያ ላይ ምንም ማለት አልፈለገም።
ዛሬ ላይ የትኛውም አነቃቂ ንግግር አድራጊ የኤክሃርት ቶሌን "ዘ ፓወር ኦፍ ናው" እና የሮንዳ ባይርንን "ዘ ሴክሪት" የተሰኙ መጻሕፍት ሃሳቦች ባለውለታነት ሳይጠቅስ አያልፍም። የሕይወት መመሪያቸው ራሱ በአብዛኛው የተቀዳው ከነዚሁ መጻሕፍት ነው። ለአብነት ያህል የኤክሃርት ቶሌ ደቀ መዛሙርት ስለ "አሁን ኃይል" ሲናገሩ፦ "የአሁን ኃይል (ዚ ፓወር ኦፍ ናው) ከጊዜ ሃሳብ ወጥተን እውነተኛ ማንነታችንን እንድናውቅ፣ ከመንፈሳዊ ህመማችን ተፈውሰን ጥልቅ ውሳጣዊ ሰላም እንድናገኝ የሚረዳን መንፈሳዊ የራስ አገዝ መመሪያ ነው" ይላሉ።
"በአሁን ጠንካራ ሁኔታ ውስጥ ስንገኝ፣ ከጥልቁ ንቃተ ህሊና ምላሽ እናገኛለን፣ በህይወት የደስታ ባህር ውስጥ እንሳፈፋለን" ሲሉም በግኝታቸው ይጓደዳሉ። ካሻቸው፦ "ኢየሱስ 'በእኔ የሚያምን የሕይወት ውኃ ወንዝ ከሆዱ ይፈልቃል' እንዳለው አይነት ነው" ብለው ሊጠቅሱም ይችላሉ። የሁሉን አቃፊው አዲሱ ሃይማኖት ጠባይ እንደህ አይነት ነው። ኤክሃርት ቶሌም ከየትኛውም ሀይማኖት ይበጀኛል ብሎ የሚያስበውን ሃሳብ እንደሚወስድ፣ የዜን ቡዲዝምንና የሱፊዝም ትምህርቶችን እንደሚጠቀም፣ ከሂንዱይዝምና ከመጽሐፍ ቅዱስ ቃሎች እንደሚጠቅስ ይታወቃል።
የዳጊ ሾው አዘጋጅና አቅራቢ ዳግማዊት ክፍሌ በዚሁ ሳምንት እንግዳዋ ከነበረችው ወጣት ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ ያደመጠ ሰው አዲሱ ሃይማኖት ምንኛ በደጃችን እያደባ እንዳለ ጥቁምታ ይሰጣል። በእሳቦትቱና በባህርይው ከቃል እምነት አስተምህሮ ጋር ኩታ ገጠም እንደሆነም ይገነዘባል። አዲሱ ሃይማኖት እንደ ቃል እምነት (ዎርድ ኦፍ ፌዝ) እንቅስቃሴ ሁሉ የሃሳቡ ቀደምት አመንጪዎችና አዳባሪዎች እንጂ እገሌ የሚባል መሪ የለውም። ለሰዎች ሌላ ሃይማኖት እንደሆነ የማይረዱትም ለዛ ነው።
ዳግማዊት ክፍሌ እና ታዳጊዋ ወጣት ካደረጉት ቃለ ምልልስ ጥቂቱን ልጥቀስ። ወጣቷ፦ "ሎው ኦፍ አትራክሽን ላንቺ ምንድነው? ተብላ ስትጠየቅ፦ "ሎው ኦፍ አትራክሽን አንድን ነገር በአእምሯችን ደጋግሞ በማሰብ ወደ እውኑ ዓለም የምንለውጥበት ኃይል ነው።" በማለት ስትመልስ፤ ጠያቂዋ፦"እስቲ ስለ ማኒፌስቴሽን ደግሞ ንገሪኝ" ባለቻት ጊዜ ደግሞ የታዳጊ ወጣቷ ፌቨን መኮንን ምላሽ፦"ለእኔ ማኒፌስቴሽን ማለት አንድ እንዲሆንልኝ የምፈልገውን ነገር አጠንክሬ ካሰብኩት ፈጣሪ ይሰጠኛል፣ ያሳካልኛል ማለት ነው። ወይም እንደዛ ብዬ ነው የማምነው። ማኒፌስቴሽን የምለው ያንን ነው። ስለ ማንፌስቴሽን ያወቅሁት በዚያ ላይ የተጻፈ መጽሐፍ አንብቤ ነው።" የሚል ነው። ማኒፌስቴሽን ራሱን የቻለ ትምህርት እንዳለው ልብ ይሏል።
በዳግማዊት ክፍሌ ቀጣዩ ጥያቄም ውስጥ ጭብጡ ተቀምጧል። "እንግዲህ ስለመጠየቅ፤ ከዚያ ደግሞ ስለማመን፤ ከዚያ ያመነውን ነገር ስለመቀበል እያወራን ነው። 'ዘ ሴክሪትን' እና 'ዘ ሎው ኦፍ ዘ ዩኒቨርስን' እንዳነበብሽም ነግረሺኛል። ከዚያ ስላገኘሽው ውጤት እንደምሳሌ የምታነሺው ምንድነው?" ስትል ዳግማዊት ላቀረበችው ጥያቄ ፌቨን መኮንን በሰጠችው ምላሽ፤ የትምህርት ቤት ጓደኞቿ ውጤት ለማምጣት ሲፈጉ፣ ፈተና ለማለፍ የመማሪያ መጽሕፍቱን ሁሉ በማንበብ ጊዜ ሲያጠፉ፣ መሉ ሰሚስተሩን ሲያጠኑ እርሷና የእርሷ ዓይነት እምነት ያላቸው ልጆች ግና በጥቂት ንባብ ውጤት ማምጣት እንደቻሉ፣ የሚፈልጉትን ነገረ የመጠየቅ፣ የማመንና በቀላሉ የመቀበል መርህ እንደሰራላቸው ገልጻለች። ይኼ ደግሞ ጃፒ በቤተ እምነቱ መድረክ ላይ እየተወራጨ ከሚሰብከው ስብከት የተለየ አይደለም።
በነገራችን ላይ የ"ዘ ሎው ኦፍ ዘ ዩኒቨርስ" ዋና ሃሳብ የአጽናፈ ዓለሙን ህግ የመለኮታዊ አንድነት ህግ ብሎ የማመን ጉዳይ ነው። ይህ ህግ ሁሉም ነገር እርስ በእርሱ የተገናኘ ስለመሆኑና ምንም ነገር ከሌላው የተነጠለ እንዳልሆነ የሚብራራበት የአዲሱ ሃይማኖት አስተምህሮ አንዱ ክፍል ነው። በዚህ ዓለም ላይ ምንም አይነት ሁኔታ ቢፈጠር የሰው ልጆች መንፈሳዊ ደረጃ ምንም ሳይቀንስ ከመለኮት ጋር እርስ በእርስ የተጋመደ መሆኑም ይታመናል። እዚህ ውስጥ የአዳም፣ ውድቀት፣ የእግዚአብሔር ቁጣና ምህረት ወ.ዘ.ተ ብሎ ነገር የለም። እንከን ቢገኝ ለመንጻት የክርስቶስ ደም ብቸኛው መድኅን አይደለም። የዚህ ሃይማኖት የመንጻት ሥርዓት አሉታዊ አስተሳሰብን ማስወገድ፣ ከትናንት ጸጸት፣ ከነገ ፍርሃት ሸሽቶ አሁንን የመኖር ሰዋዊ ብልሃት ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ ግና ስለ ፈጣሪያችንና አዳኛችን ሲናገር፦" እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፥ ቤዛነቱንም እርሱንም የኃጢአትን ስርየት ወዳገኘንበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት አፈለሰን። እርሱም የማይታይ አምላክ ምሳሌ ነው። የሚታዩትና የማይታዩትም፥ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት፥ በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር ነው። ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል። እርሱም ከሁሉ በፊት ነው ሁሉም በእርሱ ተጋጥሞአል። (ቆላ.15-17) እናንተንም ነውርና ነቀፋ የሌላችሁና ቅዱሳን አድርጎ በእርሱ ፊት ያቀርባችሁ ዘንድ፥ በፊት የተለያችሁትን ክፉ ሥራችሁንም በማድረግ በአሳባችሁ ጠላቶች የነበራችሁትን አሁን በሥጋው ሰውነት በሞቱ በኩል አስታረቃችሁ። (21-22)" ይላል።
824 viewsΒενιαμίν, edited 07:04