2022-12-09 19:01:36
የዛሬ 21 ዓመት #6
መድረስ አይቀርም ሳምንቱ ደረሰና አዲሶቹ ወዳጆቼ መጡና ወደ ቤተክረስቲያን ይዘውኝ ሄዱ። እንደ ባለፈው ሳምንት በታላቅ ጥንቃቄ ተራ በተራ ወደ ፀሎት ቤቷ ውስጥ ገባን። መርሃ ግብሩ ተጀመረ። ይዘምራሉ። ታዲያ ሲዘምሩ ከልባቸው ነው። በትግሪኛ ይዘመራሉ። በአማርኛም ይዘምራል።
“አዚእካ ኣቢይካ መውዳድርቲ ዘይብልካ…..ንስዕካ ዕይካ ጎይታ”
("በጣም ትልቅ ነህ ተወዳዳሪም የለህም... አንተ ነህ ጌታ" ማለት ነው)።
“ከኢየሱስ ጋር ኑሮ ይሻለኛል……
አክሊል ከምደፋ በአለም
የኢየሱስን መስቀል ልሸከም
ሰይጣን ከሚያቆላምጠኝ
ኢየሱሴ በእግሩ ይርገጠኝ”
እያሉ በአማርኛም ደግሞ በደስታ ይዘምራሉ። እኔም ከስር ከስር ከእነርሱ እየሰማሁ አብሬ እዘምራለሁ። እዚህ ስብስብ ውስጥ ሁሉም ነገር ከልብ እና በፍቅር ነው የሚደረገው። ከውጪ ያለባቸውን ጫና የሚቋቋሙት በዚህ መንገድ ነውና።
የዛሬው ለእኔ ሁለተኛ ፕሮግራሜ ነው። ሁሉም መሬት ነውና የሚቀጠው እኔም ቀጭኗ ፑልፒት ስር ግድግዳ ተደግፌ ተቀምጫለሁ። የስብከቱ ሰዓት ደርሶ ሰባኪው ይሰባካል። የስብከቱም ትኩረት "በዚህ ፍፁማዊ የእስልምና ተዕዕኖ ባለበት ምድር በመንፈስ ቅዱስ ኀይል መኖር" የሚል ነበር። ሁሉም የመንፈስ ቅዱስን ሃይል አጥብቆ መፈለግ እንዳለበት ያስረዳል። የተለያዩ ጥቅሶችን እያነሳ ይሰብካል። በአጋጣሚ ሆኖ ደግሞ ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ የመንጃ ፈቃድ ትምህርት ቦታ ያገኘሁት እና ወደ እዚህ ያመጣኝ ሰው በመንፈስ ስለ መሞላት የሚያብራራ መፅሐፍ ሰጥቶኝ ሳምንቱን ሳነበው ነበር የቆየሁት።
ሰባኪውም ስብከቱን ሲጨርስ ፀሎት የምትፈልጉ ወደ መሃል ኑና እንፀልይላችሁ አለ። የተወሰኑ ሰዎች ወደ መካከል ወጡ። እኔም አብሬ ወጣሁ እና ተንበረከኩ። የዚያን ዕለት በልዩ ሁኔታ የሆነ ሃይል ተሰማኝ። በአዲስ ቋንቋም ተናገርሁ። በጣም ደስ አለኝ። ይህ ለእኔ ልዩ ክስተት ነበር። መርሃ ግብሩ አልቆ በወንድማዊ ፍቅር ወደ ምኖርበት ጊቢ እያበረታቱ ወሰዱኝ።
በመንፈሳዊ ህይወቴ እየጠነከርኩ መጣሁ። ማንበቤን እና መፀለዬንም ቀጥያለሁ። የእግዚአብሔር ቃል በተለየ ብርሃን ነው በውስጤ የሚገባው። እግዚአብሔር ያስተምረኛል። አንድ ቀን እንዲያውም የሆነ ድምፅ ከቤት እንድወጣ ይገፋፋኛል። ተነስቼ ወጣሁ። ማታ ነው። "በዚህ ሂድ" "በዚህ ታጠፍ" የሚለኝ አይነት የውስጥ ግፊት ነበር። መጨረሻ ላይ አርብ አርብ የምንሰግድበት “መስጂድ ሳራ” የሚባለው ትልቅ መስጊድ ጋር ስደርስ “ቁም” አለኝ። ከዚያ ዝም ብዬ መስጊዱን ተመለከትኩት። ማታ ስለሆነ መስጊዱ አናት ላይ ያሉት ጨረቃና ኮከብ በመብራት (ውስጣቸው በተገጠመላቸው) ደምቀው ይታያሉ።
ከዚያ ውስጤ የሚጮህ ድምፅ ይሰማኝ ጀመር “እየሰገድክ ያለኸው ለጨረቃና ለከዋክብት ነው። ይህ ደግሞ ጣዖት አምላኪነት ነው። ጣዖትን ማምለክ ደግሞ በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላ ነው” እያለ ያነበብኳቸውን የተለያዩ የመፅሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች እያስታወሰ ለረጅም ደቂቃ ወቀሰኝ። ተቆጣኝ ብል ይሻላል። ከዚያ ወደ ቤት ተመልሼ ላብ በላብ እስከምሆን ድረስ የምጥ ፀሎት ፀለይኩ። የዛኑ ዕለትም "ስዕለት" ተሳልኩ። “እግዚአብሔር ሆይ ከዚህ ወስጥ ብታወጣኝ እድሜዬን ሁሉ ለአንተ እኖራለሁ የምትፈልገውን ሁሉ አደርጋለሁ” ብዬ ተሳልኩ።
ከዚህ በኋላ...በየቀኑ እየሔድኩ የመንጃ ፈቃድ ትምህርቴን እማራለሁ። ከእነዚያ ሶስት ሙስሊም ሃበሾች ጋር እከራከራለሁ። በዚያች ድብቅ ቤተክርስቲያን አርብ አርብ እየሄድኩ እማራለሁ። የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮችም የደህንነት ትምህርት መማር አለብህ አሉኝና ከጥቂት አዲስ አማኞች ጋር መማር ጀመርሁ። በቤቴ ያለኝ ፀሎትና ንባብም ቀጥሏል። በቃ አሁን ውስጤ በደንብ እየተደራጀ መጣ። የደህንነት ትምህርቱንም ቶሎ ቶሎ አስተማሩን እና የጥምቀት ጊዜያችን ደረሰ። እዚያችው ቤት ውስጥ ከሳሎኗ አጠገብ ባለች ክፍል ውስጥ ከፕላስቲክ በተሰራ ተገጣጣሚ ገንዳ ውሃ ተሞላና ተጠመቅን።
የመጠመቂያ ልብስ ብሎ ነገር የለም። ሰፋ ያለ ቢጃማ ተሰጠን ተጠመቅን። የጥምቀት መርሃ ግብሩ ደስ የሚል ነበር። አርብ ቀን ነው የተካሄደው። የገባነው ሃሙስ ማታ ነው። ለሊቱን በአዳር ፀሎት ነው ያሳለፍነው (በነገራችን ላይ ብዙ ጊዜ አዳር ፀሎት ይደረጋል)።
ከዚህ በኋላ ወደዚያ መስጊድ መግባት በግልፅ “ክረስቶስን መካድ” መስሎ ተሰማኝ። “ከስራ የተለየ እምነት የሞተ ነው” የሚለውና “በሰው ፊት የሚክደኝ...” የሚለው ቃል አይምሮዬን ሊለቀኝ አልቻለም። በሐዋርያት ስራ መፅሐፍ ላይም ያነበብኳቸው ለክርስቶስ ሲሉ የተሰዉ ሰዎችንም አስባቸዋለሁ። በቤተክረስቲያንም በየ ፕሮግራሙ በአረብ ሃገራት ስለ ክርስቶስ ሲሉ የተሰዉ ሰዎች ታሪኮች ይነበቡ ነበርና እንርሱንም አስባለሁ። አሁን አንድ ውሳኔ መወሰን እንዳለብኝ ደመደምኩ። ለአሰሪዎቼ የክርስቶስ ተከታይ መሆኔን መናገር እና የሚመጣውን መቀበል። ነገር ግን የእናቴ ጉዳይ በጣም አሳሰበኝ።
እናቴ በድህነት ነው ያሳደገችኝ። ገና በአስራ ሰባት ዓመቷ ከአክሱም ተሰዳ አዲስ አበባ መጥታ በነበረበት ጊዜ ነው ከአባቴ ጋር ተጋብተው የወለደችኝ። አባቴም የአየር መንገድ ሰራተኛ ማህበር ሰብሳቢ ስለነበር ከኢሃፓ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ደርግ አሰረው። እናቴ እኔን አርግዛ ነበር እርሱ የታሰረው። ሲፈታ ተወልጄ የወራት ዕድሜ ላይ ነበርኩ። እንደ ተፈታም ከአገር ጠፍቶ ሄደ። በቃ ሄደ። ሲሄድ ለአጭር ጊዜ ነው ብሏት ነበር የሄደው ነገር ግን ድምፅም ጠፋ።
እናቴ አዲስ አበባ ከአንድ ወንድሟ በቀር የምታውቀው ሰው አልነበረምና እርሱ ጋር ተጠጋች። በዚያም ለመኖር ምቹ ስላልነበር ምርጫ ስታጣ እኔን ይዛኝ ሰው ቤት በሰራተኝነት ተቀጠረች። በቃ ከዚያ በሁዋላ ስራዋ የሰው ቤት ሰራተኝነት ሆነ። እኔን ለማሳደግ ህይወቷን ነው የከፈለችው። በመጨረሻም ሳውዲ ሄደች። ከአምስት አመት በኋላ እኔን ወደ ሳውዲ እንድመጣ አደረገች።
ሳውዲ ከገባሁበት ምሽት ጀምሮም እንግዲህ እሰከ አሁን የተረክሁላችሁ ታሪክ ተፈጠረ። እናቴ እኔን በጣም ተስፋ ታደርግ ነበር። ሳውዲ ውስጥ እኔን መስመር አስይዛ ከሌላ የወለደቻት ታናሽ እህትም አለቺኝ (አዲስ አበባ ዘመድ ጋር የተወቻት) እርሷንም መስመር አስይዛ ከዘመናት የሰው ቤት ስራ ማረፍ ነው የምትፈለወገው። ይህንን በደንብ አውቃለሁ። እንደ አንድ እናቱ ዋጋ እንደከፈለችለት ልጅም የሚገባትን ማድረግ ግዴታዬ ነው።
ነገር ግን በልዩ ብርሃን የተገለጠልኝን ክርስቶስን የሚያስክድ ህይወት ውስጥ እየኖርኩ ይህንን ለማድረግም ከበደኝ። የእናቴም ሁኔታ አስጨነቀኝ። ነገር ግን ከእናቴ ክርስቶስን ማስቀደም እንዳለብኝ ስለተረዳሁ በብዙ እንባ ውስጥም ሆኜ ቢሆን የእናቴ ጉዳይ ለእግዚአብሔር ተውሁለት። “ማንም እናቱን ክእኔ ይልቅ ቢወድ ለእኔ ሊሆን ኤእችልም” የሚለው ቃል ገዢ ሆኖ በልቤ ተቀምጧል።
አሁን ውስጤ ጢም ብሎ ሞልቷል። የክረስቶስ ተከታይ መሆኔን ለማንኛውም ሰው ለመናገር ድፍረት አግኝቷል። መጀመሪያ ውሳኔዬን ለእናቴ ነገርኳት። ከዚህ በኋላ የክርሰቶስ ተከታይ መሆኔን ለዓሚር ስዑድ ልነግረው ነው አልኳት። እሪታዋን አቀለጠችው። አንዲት ኤርትራዊ እና አንዲት ኢትኦጵያዊ ሰራተኞች ነበሩ እነርሱም ተጠሩ። በብዙ ለመኑኝ። ይህ አቋሜ መሆኑን ብዙ እንዳሰብኩበትም አስረዳኋቸው። ሊገባቸው አልቻለም ተነስቼ ወደ መኝታ ቤቴ ሄድኩና በጌታ ፊት ብዙ አለቀሰኩ (በእነርሱ ፊት ማልቀስ አልፈለኩም)። ውሳኔዬ ግን አልተለወጠም።
609 viewsΒενιαμίν, 16:01