2022-12-05 19:30:48
የዛሬ 21 ዓመት #2
……ኢማሙ ፀሎቱን አስጀመረ። ድምፁ በጣም ያምራል። “አልሃም ዱሊላሂ ረቢ ለዓለሚን አልራህማን አልረሂም…..” እያለ በተስረቀረቀ ድምፅ በዜማ ፀሎቱን አሰማ። የእኔ ነፍስ ግን ተጨንቃለች። ከኢትዮጵያ በመጣሁ በማግስቱ በፍፁም አስቤው የማላውቀው ቦታ ራሴን አግኝቼዋለሁ። መስጊድ ውስጥ። ራሴን በዚያች ቅፅበት እንደ ምንም ብዪ አፅናናሁ "አይዞህ ቴዲ ለአጭር ጊዜ ነው" አልኩ በልቤ። ከዚያ ጎንበስ ሲሉ ጠብቄ ጎንበስ፤ ቀና ሲሉ ቀና፤ ሲደፉ እየተደፋሁ እና አጠገቤ ያሉትን እየኮረጅሁ በምችለው ሞከርሁ (ለአጭር ጊዜ ነው እያልኩ ራሴንን እያፅናናሁ)። ነገር ግን በየመሃሉ እነርሱ ጎንበስ ሲሉ እኔ ቀና እያልሁ ብዙ ተሸወድሁ። የሆነ ሆኖ እንደ ምንም የመጀመሪያው "የመስጊድ ጊዜ" ተጠናቀቀ።
ከመስጊድ ስንወጣ የተወሰኑ ሰዎች ወደ ቤታቸው በግራና በቀኝ ተበታተኑ፤ አብዛኛው ሰው ግን የገባው ወደ እኛ ግቢ ነበር። ወደ ግቢ እየሄድን አንድ ሁሉም ሰው ከኋዋላቸው እንደ ማጀብ ያደረጋቸው ሽማግሌ አረብ በአንድ ደልደል ያለ ሰውነትና ሳቂታ ፊት ባለው ጥቁር ጎልማሳ ሰው ተደግፈው ከፊት ከፊታችን ሲሄዱ አየሁና አብድረሃማንን “እርሳቸው ማናቸው” ብዬ ጠየኩት። “ዓሚር ናቸው” አለና፣ ወዲያው “ልዑል ማለት ነው” ብሎ ተረጎመልኝ (በኋላ ስረዳ ይህ ጥቁር ሰው ሹፌራቸው ነው)። እርሳቸው የቤቱ ዋና ሰው ናቸው። ገራገር ነገር ይመስላሉ።
ከመስጊድ ወጥተን ወደ ቤት ስንጓዝ ሁሉም የለበሰው ጀለቢያ ነው። ሁሉም ነጯን ቆብ ራሱ ላይ ጣል አድርጓል። ቀዩዋን ዥንጉርጉር ሻሽ ያደረገም አለ። እኔ ብቻ ነኝ በቱታ የምታየው። ሽማግሌው ሰውዬ (ዐሚር) እንደምንም አንገታቸውን ጠምዘዝ አድርው ያዩኛል (ይሄ ነው አዲሱ ሰራተኛ የሚሉ ይመስላል)። ከዚያ ሳቂታ ደጋፊያቸው ጥቁር ሰው ጋርም የሆነ ነገር ያውራሉ። (ሰንብቶ ሲገባኝ እኚህን ሰው መደገፍ ብርን ራሱን ደገፍ እንደ ማለት ነው። ሰጪ ናቸው) የሁሉም ዓይን በእንክብከቤ ነው የሚመለከታቸው።
ሁላችንም ወደ ቤት ገባን እና ተመልሰን ተኛን። ትንሽ ረፈድ ሲል ከመኝታዬ ተነስቼ ይህንን ጉደኛ ግቢ ልጎበኘው ብዬ ትንሽ ዞር ዞር አልሁ። ግቢው ዙሪያውን አራት ትልልቅ የመኪና መግቢያ በር አለው። በግቢው አራቱም የውጪ አቅጣጫ የመኪና መንገድ ነው (አስፋልት ነው)። ያ ማለት አጠገቡ ሌላ ግቢ አንኳን የለም ማለት ነው። ብቻውን ሰፈር ነው። (በኋላ ስሰማ ልጆችና የልጅ ልጆች ሁሉ በአንድነት የሚኖሩት ግቢ ነው)። ሙሉ ግቢው ሴራሚክ መሰል ሸካራ ንጣፍ ተንጥፎለታል። ንፁህ ነው። ናጂር የሚባል የባንግላዲሽ ሰው በየዕለቱ ያፀዳዋል። ናጂር ግቢውን መንከባከብና የተቃጠለ አምፖል በግቢና በየክፍሉ እየፈለገ መቀየር ተጨማሪ ስራው ነው። በጣም የገረመኝ ከአራቱ የመኪና መግቢያ በሮች አንደኛው (የፊት ለፊት በር የሚባለው) በሪሞት ኮንትሮል ነው የሚሰራው። ሁሉም ሹፌር የየራሱ ሪሞት አለው፤ እየከፈተ ይገባል! ይወጣል!። መጀመሪያ ሰሞን መኪኖች ሲመጡ በሩ እራሱ ሲከፈት ገርሞኝ ነበር (የፋራ ነገር)።
ሌላው ግቢው የራሱ ስልክ ቤት የሚባልና ስልከኛ አለው። (እነርሱ ሴንትራል ይሉታል)። ስራው ስልክ ሲደውል ማንሳትና “የዓሚር መሃመድ ቤት ነው! ማንን ላገናኝዎ” እያለ ወደ ተፈለገው ሰው በውስጥ መስመር የማገናኘት ብቻ ነው። ሱዳናዊ ነው። ይህ ሰው በቃ ስልክ ብቻ ነው ሰራው። ግቢውን ጎብኝቼ እና ቁርሴን በልቼ እንደጨረስኩ ከተማው በጩኸት ድብልቅልቅ አለ። የስድስት ሰዓት ስግደት እንደደረሰ ምዕመናኑን ለመጥራት ከመስጊድ ስፒከሮች የወጣ አዛን (ጥሪ) ነበር።
እንዲህ ያለ የድምፅ ጩኸት ገጥሞኝ አያውቅም። የእኛ ሀገር መስጊዶች በጣም የተራራቁ ስለሆኑ (በተለይ በ90ዎቹ መጀመሪያ) ከመስጊድ የሚወጡ ድምፆች በርቀት ነው የሚሰሙን። ሳውዲ ግን መስጊድ በየ መቶ ሜትሩ ነው ያለው ማለት ይቻላል። አየሩ በከባድ ጩኸት ተናወጠ። አሁንም እንደገና ወደ መስጊድ ልገባ ነው ማለት ነው አልኩ በልቤ። አልቀረልኝም፤ ገባሁ። እንደ ነገሩ “ሰገድሁ” እና ወጣሁ። ዘጠኝ ሰዓት ላይ፥ አስራ ሁለት ሰዓት፥ ማታ ሁለት ሰዓት ብቻ ምን አለፋቸወሁ ሳውዲ በገባሁ በሁለተኛው ቀን ስሰግድና ስበላ ዋልኩ። በማግስቱም ተደገመ። በሶስተኛው ቀን አንዲሁ። እኔ ነፍሴ ተጨነቀች። የግቢው አባላት ደግሞ ስለ እስልምና ብማር ጥሩ እንደሆነ መመካከር ጀምረዋል። በቶሎ ከዚያ ግቢ እወጣለሁ ብዬ ስጠብቅ አዲስ ዕቅድ አወጡልኝ። እንግዲህ ምርጫ የለም! አንዴ ጀምሬው የለ? ያለሁበትም ግቢ በቀላሉ የምጋፋው ዓይነት አልሆነም።
ሳውዲ በገባሁ በሶስተኛው ቀን ጠዋት አብዱረሃማን ያለሁበት ክፍል መጣና “ያ ቲዱሩስ ተነስ የተወሰነ ልብስና ቢጃማህን ያዝና እንሂድ አለኝ” የት ነው የምንሄደው? ስለው፤ “አሚር ስዑድ ስልጠና ይውሰድ ብሏል” አለኝና በሚያስገርም ማርቼዲስ አሳፍሮ ይዞኝ ከግቢ ወጣን። ዓሚር ስዑድ የሽማግሌው ዓሚር አራተኛ ልጅ ነው። ዕድሜው ከሰላሳ አይበልጥም። ነገር ግን የግቢው መንፈሳዊ አባት እርሱ ነው። ደግ ይመስላል ነገር ግን በጎፈረ ጢም በተሞላው ቀይ ክብ ፊቱ ላይ የሆነ ጭካኔም የሚነበብበት ዓይነት ሰው ነው።
አብዛኞቹ የዓሚሩ ልጆቸ መዝናናት የሚወዱ ዓይነት ናቸው (ቆይቼ ሳጣራ)። በነገራችን ላይ ሽማግሌውን ዓሚር ጨምሮ ልጆችም የልጅ ልጆችም ሁሉ ከመንግስት ደሞዝ አላቸው። ንጉሳዊ ቤተሰብ ስለሆኑ ብቻ። ግቢው ውስት ሳይክል የሚነዳው አረብ ጩጬ ሳይቀር ሁሉም ደሞዝተኛ ነው። ዓሚር ስዑድ ደግሞ ሃይማኖቱን አጥብቆ የያዘ ዓይነት ሰው ነው። “ሼህ” ነው።በመንግስት ቢሮ የሀገር ውስጥ ሚኒስትር መስሪያ ቤት ውስጥ ከፍ ያለ ሃላፊነት ቦታ ላይ ይሰራል (በኋላ እንዳጣራሁት) የግቢው ሰራተኛ ሁሉ ተቆጣጣሪውም አለቃውም እርሱ ነው። አሚር ስዑድ ካለ አለ ነው!
ከአብድረሃማን ጋር ለሶስት ቀናት ስልጠና ይሰጥበታል የተባለው ቦታ ደረስን። ለሃላፊዎቹ አስረከበኝና እርሱ ተመለሰ። ልክ እንደ እኔ የእሰላምናን መሰራታዊያን ሊማሩ ከመጡና ሃያ ሁለት ከሚሆኑ የፊሊፒን ዜጎች ጋር ለሶስት ቀናት እንዴት እንደሚሰገድ፥ በየ ስንት ሰዐቱ እንደሚሰገድ፥ በእያንዳንዱ ስግደት ሰዓት ምን እንደሚባል፥ ምን እንደሚደረግና እንደማይደረግ ተማርን። በተለይ ዋና ዋና የሚባሉ ፀሎቶቸንና የቁርዓን ጥቅሶችን በቃል እንድናጠናቸው ተደረገ። አስተማሪያችን ፊሊፒናዊ ሲሆን ትምህርቱም በእንግሊዘኛ ቋንቋ ነበር የሚሰጠው። በፍጥነት ሁሉንም ነገር አጠናሁት፤ ቻልኩት (ያው እኔ ለአጭር ጊዜ እያስመሰልኩ አይደል)። ፊሊፒኖቹ ግን በጣም ያሳዝናሉ። አብዛኞቹ በአሰሪዎቻቸው እና በማህበረሰቡ ጫና ተገደው እንጂ አይፈልጉም።
ልክ ስልጠናው እንደ ተጠናቀቀ ሶስተኛው ቀን ላይ ከሰዓት በኋላ ሁለት ፂማቸው ደረታቸው ድረስ የጎፈረ አረብ “ሼሆች” መጡና በአንድ ትልቅ አውቶብስ ሁላችንንም ጭነው ከስልጠና ማዕከሉ ይዘውን ወጡ። ወዴት እንደምንሔድም አልነገሩንም። አውቶቢሱም በሪያድ ከተማ ያማሩና ሰፋፊ መንዶች ላይ ይዞን ሸመጠጠ……ይቀጥላል (ነገ ማታ 1 ሰዓት)
ቴዎድሮስ ተጫን
@nazrawi_tube
705 viewsΒενιαμίν, 16:30