2022-06-15 14:57:24
ህውሃት ለድርድር ዝግጁ መሆኑን አስታወቀ
የትግራይ ኃይሎች ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ከ18 ወራት በላይ ሲያደርጉት የነበረውን ጦርነት ለማብቃት በኬንያ መንግሥት አሸማጋይነት በሚካሄድ ድርድር ላይ ለመሳተፍ ዝግጁ መሆናቸውን አስታወቁ።
በህወሓት ሊቀመንበር እና በክልሉ ፕሬዝዳንት ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል ተፈርሞ የተሰራጨው ደብዳቤ የወጣው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው መንግሥታቸው ጦርነቱን በሰላም ለማብቃት ፍላጎት እንዳለው ካሳወቁ በኋላ ነው።
ከህወሓት በኩል የወጣው ደብዳቤ ከዚህ በፊት ቡድኑ ለድርድር ያቀረባቸውን ቅድመ ኹኔታዎች አላካተተም።
የኬንያውን ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ላደረጉት ጥረት አድናቆቱን የገለፀው ህወሓት፣ በድርድሩ ላይ ለመሳተፍ የሚችል ከፍተኛ የመልዕክተኞች ቡድን ወደ ኬንያዋ መዲና ናይሮቢ ለመላክ ዝግጁ መሆኑን አመልክቷል።
ደብዳቤው የአፍሪካ ሕብረት የሚጠበቅበትን ያህል አለማከናወኑን በመግለጽ አጥብቆ የተቸ ሲሆን፣ ባለፉት ወራት ሰላም ለማውረድ ከመቀለ አዲስ አበባ ሲመላለሱ በነበሩት የአፍሪካ ሕብረት ልዩ መልዕክተኛ ላይም ጥያቄ አንስቷል።
ለድርድር ዝግጁ መሆናቸውንም በተመለከተ “ለሰላም ተጨማሪ ርቀት ለመሄድ ዝግጁ መሆናችን ከደካማነት ወይም ከስግብግብነት በመነጨ የቆምንለትን መርህ ለመተው እንደ መዘጋጀት ተደርጎ መታየት የለበትም” ብሏል።
በዚህ ድርድርም በኬንያ መንግሥት መሪነት የአፍሪካ ሕብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት፣ አሜሪካ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ተሳታፊ እንዲሆኑም መጠየቁንም ቢቢሲ ዘግቧል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ማክሰኞ ትናንት ሰኔ 07 ቀን 2014 በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው እንደተናገሩት፣ መንግሥታቸው ከየትኛውም ወገን ጋር ሰላም ማውረድ እንደሚፈልግ ለዚህም ኮሚቴ ተዋቅሮ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ኮሚቴው በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚመራ እንደሆነና በገዢው ብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ መሰየሙን አመልክተው፤ ሰላሙን በተመለከተ መሳካት ያለባቸው ተግባራትን፣ እንዲሁም ስለሚጠበቁ ነገሮች እያጠና መሆኑን አመልክተዋል።
“ከህወሓትም ይሁን ከማንኛውም ሰላም ፈላጊ ጋር የምንፈልገው ሰላም ነው፤ የሚቻል ከሆነ ለሰላም መቆም ችግር የለውም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ጦርነት እንደማያተርፍና ከኹለቱም ጎን የሚያለማ ወጣት እየረገፈና አገሪቱም የምታወጣው ገንዘብ ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከህወሓት ጋር በሚደረገው ድርድር ይኸው ኮሚቴ ተደራዳሪ መሆኑን እና ኮሚቴው በቅርቡ የደረሰበትን ለፓርቲው ሲያቀርብ በይፋ ለሕዝብ በዝርዝር የሚቀርብ ይሆናል ብለዋል።
ቢቢሲ
13.1K views11:57