2021-12-29 19:41:37
ትናናሽ ኃጢአቶች ወደ ትላልቆቹ የሚያድጉበት ምክንያቶች
ምንጭ ፣ 'ወደ አላህ ሽሹ' መጽሐፍ
1- በኃጢአት ላይ መዘውተር (ሙጭጭ ማለት) ፡-
የአላህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) “ ከመዘውተር ጋር ትንሽ የሚባል ኃጢአት የለም። ከተውበት (ንስሃ) ጋር ደግሞ ትልቅ ኃጢአት የለም።”
2- ኃጢአትን አሳንሶ መመልከት፡-
ኢብን መስዑድ (ረ.ዐ) እንዲህ ብለዋል፡- “አማኝ ሰው ሃጢአቱን ልክ በራሱ ላይ ሊወድቅ እንደሚያንዣብብ ተራራ አድርጎ ይመለከተዋል። ዝንጉ (ሙናፊቅ) ሰው ግን ኃጢአቱን እጁን ቢያወናጭፍ ሊያባርራት እንደሚችል ዝንብ ነው የሚያየው።”(ቡኻሪና ሙስሊም)
አነስ ኢብን ማሊክ (ረ.ዐ) እንዲህ አሉ፡- “እናንተ እንደ ፀጉር አቅልላችሁ የምትመለከቱትን ኃጢአት በነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ጊዜ ከአውዳሚ ወንጀል እንቆጥረው ነበር።” (ቡኻሪ ዘግበውታል)
ቢላል ኢብን ሰዕድ (አላህ ይዘንለትና) እንዲህ ይላል፡- “የኃጢአትህን ትንሽ መሆን አትመልከት የምታምጸውን ጌታ ታላቅነት ተመልከት።”
3- በኃጢአት መደሰት፡-
አንድ ሰው “የእገሌን ክብር እንዴት እንዳዋረድኩትና ሃፍረት እስኪይዘው ድረስ ኃጢአቱን እየዘረዘርኩ እንዳሸማቀቅኩት አላየህምን? “ በማለት ሊናገር ይችላል። አንዱ ነጋዴ ደግሞ ለጓደኛው “ያንን ሰው እንዴት እንዳታለልኩትና እንደተጫወትኩበት አልሰማህምን?” በማለት ወንጀሉን ገድል አድርጎ ሊያወራ ይችላል። እነዚህን የመሠሉ አባባሎች ትንሹን ኃጢአት ወደ ትልቅ የሚቀይሩ ምሣሌዎች ናቸው።
4- የአላህን ነውር የመሸፈን ፀጋ ችላ ማለት ፡-
አላህ የአንድን ባሪያውን ኃጢአት በመሰተርና በቅጣቱ ባለመቸኮሉ መዘናጋት ታናናሽ ኃጢአቶችን ወደ ታላቅ ይቀይራቸዋል።
5- የፈጸሙትን ኃጢአት በሌሎች ሰዎች ፊት ማውሳት፡-
አቡሁረይራ (ረ.ዐ.) የአላህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) እንዲህ ማለታቸውን አስተላልፈዋል፡- “ከኡመቶቼ የፈጸሙትን ኃጢአት ይፋ የሚያደርጉ ሲቀሩ ሁሉም ምህረት ያገኛሉ። ሰውዬው በሌሊት የፈጸመውን ኃጢአት አላህ የሰተረው ሆኖ እያለ ሲነጋ “እገሌ ሆይ! እንዲህ ዓይነት ኃጢአት ትናንት ፈጸምኩ” በማለት ያወራል።”
6- ኃጢአት የሚፈጽመው ሰው ሰዎች የሚመሩበት የዕውቀት ባለቤት ከሆነና የፈጸመው ኃጢአት ከታወቀ ወደ ታላቅ ኃጢአት ከፍ ይልበታል።
https://t.me/NejashiPP
1.0K views16:41