2021-12-18 06:55:54
ተገኘች …
*ሳምንት ሆነው መሠለኝ፡፡
ከተቀጣጠርንበት ስደርስ በትንሷ ስኒ ከቀረበለት ማኪያቶ ጋር ተቀምጧል፤ ላዩ ላይ ያለዉን አረፋ በስሱ እየገፈፈ ነበር፡፡
“መርሐባ መሐመዱ!” አለኝ፡፡
አንዴ ፉት ካለለት በኋላ “አህ … ዋው.. አየህ ማኪያቶ ማለት ይህ ነው፤ …” አለና ፈጠን ያለዉን አዘዘልኝ፡፡
“እህ …” አልኩት ዉጤቱን ለመስማት፡፡
“አይቻት መጣሁ፡፡” አለኝ፡፡
“እናሳ”
“ማሜዋ አትሆንም”
“ምነው”
“እንደው ሰው የመጣም አልመሰላት፣ ሻሿ ወደኋላ ግማሽ ጭንቅላቷ ላይ ደርሷል፡፡ ዝምብላ ዉር ዉር ትላለች፡፡”
“እና”
“ልቤ አልፈቀደም፡፡” አለኝ፡፡ ወሬዉን በዚሁ ዘጋነው፡፡ ልብ ካልፈቀደ ሰው መግፋት አልወድ እኔ፡፡
ጠዋት አንድ ወዳጁ ነበር የሆነች ልጅ ላሳይህ ብሎ ይዞት የሄደው፡፡ ሲሄድ “ማሜዋ እስቲ ዱዓ አድርግበት የሆነች ልጅ ላይ ነው” ብሎኝ ነበርና፡፡
መስፈርቱ ብዙ አልነበረም “ረሕማ ያላት፣ የተረጋጋች” ይለኛል ብዙን ጊዜ፡፡
“ስንተኛህ ናት ይህች?” አልኩት ድንገት ፊት ፊቱን እያየሁኝ፡፡ “ለማየት” ማለቴ ነው፡፡
“ስድስተኛ ናት፡፡” አለኝ ቀለል አድርጎ፡፡
የሚፈልጋት ሴት ምን ዓይነት እንደሆነች በልቡ ከፃፈ ቆይቷል፤ አንዴ ጠቁሜው አትሆንም ካለኝ በኋላ እንዲህ እንዲያ አድርግ ብዬው አላውቅም፣ ይህችን ያችን አግባ ብዬም አልተጫንኩትም፡፡
አንዳንዴም ፍለጋ ጀምሮ በመሃል ያቋርጣል፡፡ ጉዳዩን ይረሳል፡፡ እንደገና ድንገት በሆነ ምክንያት ትዝ ሲለው ወይ እናቱ ስትማፀነው፣ ወይ እህቶቹ ሲጮኹበት እንደ አዲስ ይጀምራል፡፡
እኔም ልቡ በነገረው በራሱ ጊዜ ያድርገው ብዬ ከተውኩት ቆዩሁ፡፡
ባቀረበልኝ ሪፖርት መሠረት የተወሰኑትን ለምን እንደተው መለስ ብዬ ለማስታወስ ሞከርኩ፡፡
አንዷ - ዝምተኛ ናት፣ ምንም ምንም አትናገርም፣ እስቲ በዚህ ለፍላፊና በተጫዋት ባህሪዬ ከዚህች ጋር እንዴት እኖራለሁ! አለኝ፤
ሌላኛዋን ወዶ ነበር ግን አጠረችብኝ ደግሞም ልጅ እግር ናት፣ መግባባቱ የሚከብድ መሰለኝ አለኝ፡፡
ሦስተኛዋ ቀውላላም ቀልቃላም ናት፣ ሐያእ የፈጠረባት አትመስል፣ ትፈጥናለች ብዙ ታወራለች፡፡
አራተኛዋን ደግሞ ወደዳትና አነጋገራት፣ ራሷን ቆለለች፣ መስፈርቷን ደረደረች፣ ከመስፈርቶቿ ከአንዱም መውረድ አልፈለገችም፡፡ የራሷን ጥቅም አስጠባቂ ብቻ መሠለችበት፡፡ እናም ተዋት፡፡
ስድስተኛዋ የዲኗ ጥንካሬ ነገር አጠራጠረው፣ እኔም ደካማ እሷ ደካማ እንዴት ልንዘልቀው ነው ብሎ ፈራ፡፡ ከፈሩ ደግሞ መተው ይሻላል አለኝ፡፡
አምስተኛዋን በስድስቱ መካከል እኔ ረሳሁኝ፡፡ እነኚህን ማስታወሴም ራሱ በቂ ነው፡፡
ይኸው ዛሬ በሌሊቱ ቴክስተ አደረገልኝ፣ የተላከው ቴክስት ሌሊት ስምንት ሰዓት አካባቢ፡፡ አልተኛም ማለት ነው አስቡት፡፡
“ተገኘች” ይላል በአጭሩ፡፡
“አልሐምዱ ሊላህ!” ብዬ መለስኩለት፡፡
ዝርዝሩን ሌላ ጊዜ እናወራበታለን፡፡
ከሱ ጋር ማለቴ ነው፡፡
ግና አንድ ነገር ባስታዉስ ብዬ ወደድኩ፡፡
የደረሳችሁ ሴቶች ሆይ! ወንድማችሁ ወይም ሌላ ሰው አንድ ባዕድ ሰው ቤታችሁ ይዞ ከመጣ ሊያየኝ ነው ያመጣው ብላችሁም ጠርጥሩ እስቲ፡፡ ሆ ….
727 viewsedited 03:55