2021-02-09 10:21:49
ዱዓ ያስፈልገዋል
(ክፍል ሁለት)
ከአላህ ጋር መጽሐፍ
(ABX)
በርግጥም ከዱዓ በላይ ምን አለ!!፡፡ የሰማይ ቤት ወሬ እያነፈነፈች የምትኖር ትመስላለች ታለም፡፡ የሆነ መጥፎ ነገር ሊከሠት እንደሆነ ከሰማች አሊያም ወሬ ያመጡላት እንደሆነ ያንን ክፉ ወሬ በዱዓ ልትቆጣጠረው ትፎክራለች፤ “ቆይ ለሱም ዱዓ አለለት!” ትላለች፡፡ በዱዓ ትተማመናለች፡፡ በዱዓ ትዝታለች፡፡
እጅግ በዱዓ አድራጊነታቸው ከምገረምባቸው ከተሞች መካከል አንዷ ጎንደር ናት፡፡ ትላልቅ ዑለሞች ይገኙባታል፡፡ ጎንደር የበረካ አገር ነው፡፡ የበረከቱ ሚስጢር ዱዓ ይመስለኛል፡፡ ሙስሊሞቿ በደግነታቸው አይታሙም፡፡ በየምክንያቱ ሶደቃ ያበዛሉ፡፡ ብሉልን ጠጡልን ይላሉ፡፡ ገርነት፣ መውደድ የሕዝቡ ባህሪ ነው፡፡ ከዚህም ባለፈ በዱዓቸው ይታወቃሉ፡፡ በዱዓቸው ይተማመናሉ፡፡ የሆነ ነገር መከሠቱን ከሰሙ፣ አሊያም ሊከሠት እንደሆነ መረጃው ከደረሣቸው፣ በየመስጊዱ ይጣራሉ፣ ለዱዓ ይነግራሉ ያስነግራሉ፡፡ ዱዓ እንዲያደርጉ ያሳውቃሉ፡፡
ጠላት እያሴረባቸው መሆኑን ካወቁ፣ አገር በበላእ ሊታመስ እንደሆነ ምልክቱ ከመጣላቸው፤ መረጃዉም ከደረሣቸው ዝም ብለው እጃቸዉን አጣጥፈው አይቀመጡም፤ ተመቻችተው እንቅልፍ አይተኙም፡፡ ሁሉን መጥፎ ነገር ማስቆምና መመለስ ወደሚችለው ወደ አምላካቸው አቤት ይላሉ፡፡ ሌቱን በዱዓ ያነጋሉ፤ ቀኑን በፆም ያሳልፋሉ፣ ወደ አላህ (ሱ.ወ.) ይዋደቃሉ፤ ወደ ፈጣሪያቸው ይማፀናሉ፡፡
በበላእ ሰሞንም ሆነ አንዳች አሳሳቢ ነገር ሲያጋጥም እንደየበላው ሁኔታና ደረጃ ቀናትና ወራት ድረስ ሊዘልቅ የሚችል የዱዓ አዋጅ ይታወጃል፡፡ የዱዓ ሳምንትና የዱዓ ወር ይፀድቃል፡፡ ከዚያም ዱዓው በጥብቅ እና ከልብ ይደረጋል፡፡ የሚገርመው ምላሹም አይዘገይም፡፡ ዱዓው እየተደረገ ሳለ የተመደቡለት ቀናቶች ሳይጠናቀቁ፣ ብዙም ሳይቆይ የድል ብሥራት ይመጣል፡፡ ሊቀሰቀስ የነበረው በላእ ይከሽፋል፤ የተነሳው በላእ መንገድ ላይ ይቀራል፡፡ የታሰበ የጥፋት ድግስ ይከስማል፡፡ ጠላት መንገድ ላይ “እርሱ በርሱ” ተባላ የሚል ወሬ ይሰማል፡፡
እንዲህም ሆኖ በላው ተመለሰ ብለው ዱዓቸዉን አያቆሙም፤ እጃቸዉን አያወርዱም፡፡ እስከመጨረሻው በዱዓ ይፋለሙታል፡፡ በዚህ መልኩ ስጋት ይወገዳል፡፡ ፍርሃት ይነሳል፡፡ ሽብር ይገፈፋል፡፡ ዉጤት ካገኙበት በኋላም ይደሠታሉ፤ አምላካቸዉን አብዝተው ያመሰግናሉ፡፡
“ጎንደር በዱዓ ነው” የሚል መፈክር ሁሌ እሰማለሁ፡፡ አዎ ጎንደር በዱዓ ነው፡፡ በሚደረጉ ተደጋጋሚ ዱዓዎች ብዙ ዙር በላዎች በዱዓ ሲከሽፉ አይቻለሁ፡፡ 'ያዝልን!' ሲሉ ይይዝላቸዋል፣ 'አንሳልን!' ሲሉ ያነሳላቸዋል፣ 'እንዳያየን እንዳይሰማን አድርገው' ሲሉም ያደርግላቸዋል፡፡
በርግጥም የጎንደር ሙስሊም በዱዓ ነው፡፡ የአገሬው ሰው ሰው አይነካም፡፡ የነኩትንም በዱዓው ብቻ ነው ልክ የሚያስገባው፡፡ እንክትክቱን የሚያወጣው፡፡ የአገሬው አማኝ ከአላህ ጋር ነው፡፡ አላህም ከነርሱ ጋር ነው፡፡
ዱዓ ከመሣርያዎች ሁሉ የሚበልጥ ትልቅ መሣርያ እንደሆነ አምናለሁ፡፡ አላህ ከሠጠን ፀጋዎች ሁሉ ዱዓ ትልቁ ፀጋ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ግና ይህንን መሣርያ አባክነነዋል፡፡ በአግባቡ አልተጠቀምንበትም፡፡ በትክክልም ሥራ ላይ አላዋልነዉም፡፡ እስቲ ምን ያህሎቻችን ነን ቢያንስ ከሶላት በኋላ ትዕግስት አድርገንና ጊዜ ወስደን ለአምስት ደቂቃ ያህል ዱዓ የምናደርግ? ለራሣችን ጥቅም መሰሰታችን ያሳዝናል፡፡
የታሰረ ማለትስ እጁ ከዱዓ የታሠረ ነው፡፡ የተነፈገ ማለትስ ዱዓ ከማድረግ የተነፈገ ነው፡፡ በርግጥ አላህ በልብ ያሰቡትንም ይሠጣል፡፡ ግና አላህ ባርያው እጁን አንስቶ ሰለምነው ይወዳል፡፡
ዱዓ ምድር ከሰማይ የምትገናኝበት ገመድ ነው፡፡ ባሮች ከአምላካቸው ጋር የሚተሳሰሩበት ሠንሠለት ነው፡፡ እጃችንን ካላነሳን፣ በምላሳችን ካልተማፀንን ግንኙነቱ ይቋረጣል፡፡ ብዙ ነገር መተው እንችላለን፡፡ ዱዓ ግን ፈጽሞ አንተው፡፡ ከዱዓ አንዘናጋ፡፡ በዱዓ ሕያው እንሆናለን፡፡ በዱዓ የተመኘነዉን እናገኛለን፤ ያለምነዉን እናሳካለን፤ የጠፋብንን እናገኛለን፣ የጎደለብንን እንሞላለን፡፡
ዱዓን ሲቸግረን ብቻ አይደለም ማድረግ ያለብን፡፡ ሲጨንቀን ብቻ አይደለም ወደ አላህ መሮጥ ያለብን፡፡ በዱዓ የሌለንን ብቻ ሳይሆን ያለንንም፣ ያልገባንን ብቻ ሳይሆንን የገባንን፣ የማንችለዉን ብቻ ሳይሆን የምንችለዉን ሁሉ ከአላህ እንጠይቃለን፡፡ ያለንን እንዲባርክልን፣ ያጣነዉን እንዲለግሰን፣ ያለቀብንን እንዲተካልን እንማፀናለን፡፡
በዱዓ ስላለንበት ሁኔታ ሁሉ ለፈጣሪያችን እንገልፃለን፡፡ ከፍታና ዝቅታችንን፣ መውደቅ መነሳታችንን ሁሉ እናሳስብበታለን፡፡
ዱዓ ለሰው ብቻ አይደለም ለሁሉም ነው፡፡ ለሰው ለእንሠሣም ነው፡፡ ለትዳርም ለብቸኝነትም ነው፡፡ ለአገርም ለዓለምም ነው፡፡
ዱዓ ጥቅሙ ሰፊ ነው፡፡ ዱዓ የሚደረገዉም ለራስ ነው፡፡ ሌሎች ስላላደረጉ ዱዓ አላደርግም አይባልም፡፡ ሌሎች ግድየለሽ ስለሆኑ ግድየለሽ መሆን አይገባም፡፡ ዓለም እንዲህ ችግሯ በዝቶ፣ ሁኔታዋ ከፍቶ፣ ሰላሟና ፍቅሯ ጠፍቶ .. ባለበት ሁኔታ የኔ ዱዓ ምን ሊለውጥ ብሎ ማጣጣልም ሆነ ተስፋ መቁረጥ ልክ አይደለም፣ ተገቢም አይደለም፡፡ ችግሮች እንዲህ በገዘፈ መልኩ ሊከማቹ የቻሉት በኛው ጥፋትና ቸልተኝነት ነው፡፡ እኔም፣ አንተም፣ አንቺም “ብቻዬን ጩኼ ምን ላመጣ!” ብለን እጃችንን አጣጥፈን በመቀመጣችን ነው፡፡ እኛ ካልጮኽን ሌላ የሚጮኽ ከየት ይምጣ ታዲያ፡፡
ዱዓ ማድረግ ሁሌም ከአላህ ጋር የመሆን ምልክት ነው፡፡ ዱዓ እናድርግ - ከአላህ ጋር እንሁን፤ ወደ አላህ እንቅረብ፡፡
ዱዓ ያልቻልነዉን ነገር ሁሉን ነገር ለሚችል ጌታ ማሳሰብ ነው፡፡ ማሰብም፣ ማሳሰብም ዱዓ ነው፡፡
ዛሬ ላይ ዱዓ የማያስፈልገው ነገር ምን አለ ወዳጆቼ!!
አዎ ሁሉም ነገር ዱዓ ያስፈልገዋል፡፡
http://t.me/MuhammedSeidABX
1.3K views07:21