2021-03-05 07:13:54
ሕይወትህን አድስ
(2)
በሙሐመድ ሰዒድ
ልብ ላላሉ ልቦች መጽሐፍ
**********የምን መድከም ! የምን ማዘን ! የምን ተስፋ መቁረጥ ! አላህ ሱብሓነሁ ወተዓላ እንዲህ እያለን
وَلَا تَهِنُوا وَلَا تَحْزَنُوا وَأَنتُمُ الْأَعْلَوْنَ إِن كُنتُم مُّؤْمِنِينَ ﴿١٣٩﴾
‹ አትድከሙ አትዘኑ የበላዮች ትሆናላችሁ እውነተኛ አማኝ እንደሆናችሁ ´› (3፡139) ብሎናልና ፡፡
አዎን .. ለህይወት ፈተናዎች እጅ መስጠት አያስፈልግም፡፡ ሲያጡ ብዙም አለመከፋት ፤ ሲከስሩ አለመደናገጥና አለመርበትበት ፤ ቢመቱ አለመጉበጥ አለመልፈስፈስ ያስፈልጋል፡፡
ሞተዋል እየተባልን አልሞትንም ከሆነ መልሳችን ፤ ትንሽ ናቸው ስንባል ብዙ እንደሆንን ካሣየን ፤ ስለድክመታችን ሲነገር ጥንካሬያችንን ካስመሰከርን .. ኢንሻአላህ ውጤት አለን፡፡ አዎን ቢኢዝኒላህ ውጤት አለን፡፡
ሙእሚን ለስኬት እንጅ ለውድቀት እጅ አይሰጥም፡፡ በኸይር እንጅ በመጥፎ ነገር እራሱን አያበስርም፡፡ በጥንካሬ እንጅ በድክመት ውስጡን አያሳምንም፡፡
ወዳጄ ሆይ ! ኢማንህ ሲወድቅ ወድቋል ተስፋ የለውም ብለህ አርቀህ ቆፍረህ አትቅበረው፡፡ ጥረትህ ሲበላሽ ‹ አልቆልኛል ዋጋ የለኝም ዳግም አላንሰራራም › ብለህ አትዘረር፡፡ ችግር ሲያገኝህ የማገገም እድሌ አክትሟል ብለህ አትሸበር ፡፡ ዱዓእ የማድረግ ስሜትህ ሲጠፋ ከቶ ሊመለስ እንደማይችል ገምተህ እጅህን አጣጥፈህ አትቀመጥ ፡፡
ህይወት አንድ ብቻ አይደለችም ዓይነት አላት፡፡ ዓለም ጎዳና ብቻ አይደለችም ጎዳናዎችም ናት፡፡ ዞር ብለህ ሌላ ስልት ይዘህ ፣ ሌላ ሰው ሆነህ አምርረህ ከተመለስክባት ታሸንፋታለህ፡፡ እሷ ድክመትህን እጅ መስጠትህን ካወቀች ትገድልሃለች፡፡ እንስም ማንነትህን በጥንካሬህ አሣያት፡፡
ሕይወት ለውጥን ትፈልጋለች ፣ መታደስንም ትሻለች ፡፡ ሌላው ቀርቶ በድሎትና ሀሴት ውስጥ ብቻ እንኳ በትዕግስት ለረጅም ጊዜ መሰንበቱ ይከብዳታል፡፡ ማር ሲበዛ ይመራታል ቅባትም ከልክ ሲያልፍ ያቅለሸልሻታል፡፡ እናም ነገሮች ሐላልና መልካም እስከሆኑ ድረስ የፍላጎቷን ልንጠብቅላት ይገባል፡፡
ኢማን ይጨምራል ይቀንሳል፡፡ ሙድ ይመጣል ይሔዳል፡፡ ሞራል ብቅ ይላል ይጠፋል፡፡ በሁኔታዎች ውስጥ እራሱን ያልቀያየረና በነገሮችም ውስጥ መስመሩን ወስኖ ምርጥ ምርጡን ያልያዘ ሰው የስኬት ጊዜው እሩቅ ነው፡፡ ለአካሔዱና ለጉዞው የተሻለውን መንገድ መጥረግ ትቶ በአንድ ዓለምና ሁኔታ ውስጥ መኖር የመረጠን ሰው ኑሮ ትርጉም አልባ ህይወትም የቁም እስር ዱኒያም የዘላለም ከርቸሌ ትሆንበታለች፡፡
የችግር ዓይነቶች ከወዲህ ወዲያ ቢቀራመቱህ ፤ ፈተናዎች በዚህ በዚያ ቢያዋክቡህ ፤ ችግሮች ከፊት ከኋላ ቢከቡህ ቆም ብለህ ጆሮ የምትሰጥበት ጊዜ እንዳይኖርህ፡፡ ወደፊት እንጅ ወደ ኋላ አትመልከት፡፡ ለመራመድ አታመንታ፡፡
ሀሳብ ተከታትሎ ቢሰፍርብህ ፤ ጭንቀት አሳድዶ ቢወርርህ ወዲያ በልና አሽቀንጥራቸው፡፡ ማንነቱን አሣልፎ በቀላሉ እጅ የሚሰጥ ሰው አትሁን ፤ የዕድል በሩ እያለለህም ሽንፈትን በፀጋ አትቀበል፡፡
ህይወት እኛ እንዳረግናት ናት ፤ እናስተካክላታለን እናበላሻታለን ፤ እናጣፍጣታለን እናመርራታለን ።
ብልህ ሰው በሞተ ነገር ላይ ነፍስ ይዘራል፡፡ ከምንም ተነስቶም ለቁም ነገር ይበቃል፡፡ ደካማ ግን በእጁ የገባውን አጋጣሚ እንኳ አይጠቀምም፡፡ ዕድልን እንድትፈልገዉ እንጂ ዕድልን ለመፈለግ ዝግጁ አይደለም፡፡ ስለሆነም በገዛ እጁ ጥፍጥናን ወደ ምሬት ይለውጣል ፤ ደስታን ወደ ሐዘን ይቀይራል ፡፡
ሞቻለሁ አትበል ተስፋ አትቁረጥ ሩሕህን መልስ፡፡ በህይወት አለህ ጠንከር በል አትለሣለስ፡፡ አልደርስም አትበል ትደርሳለህ፡፡ አላልፍም አትበል ታልፋለህ፡፡ አላህ ለምርጫና ለውሣኔ ነፃ አድርጎ ፈጥሮህ ሳለ ለምን ባርነትን ትመርጣለህ ! ፡፡
ምድር ሰፊ ናት እይታህን አስፋ አትጨናነቅ፡፡‹ ኢንሻአላህ/ በአላህ ፈቃድ › በል ሁሉንም ነገር በብቃት ትወጣለህ፡፡ መንገድ ቢዘጋ መንገዶች አሉ፡፡ ምርጫ አያልቅም አማራጮች ሞልተዋል፡፡
‹እንችላለን› የሚሉ በአላህ ፍቃድ ይችላሉ፡፡ ‹እናሣካለን› የሚሉ ኢንሻአላህ ያሣካሉ፡፡ በአላህ ላይ እርግጠኛነትህ (የቂንህ) ይጨምር፡፡ መመካትህም በሱ ይሁን፡፡ በሀሳቦች መሐል አትዋልል፡፡ በሁለት ልብም አትጓዝ ፡፡‹ አገባለሁ › በልና ኳሷን ወደ ጎሉ ምታ ትገባለች፡፡ ‹አሸንፋለሁ› በልና በሙሉ ልብ ወደ ውድድሩ ግባ ታሸንፋለህ፡፡ ‹አልፋለሁ› በሚል ሙሉ ሀሣብ ከፈተናው ክፍል ግባ ታልፋለህ፡፡ ‹እደርሳለሁ› በልና ጉዞህን ጀምር ፡፡ ‹እጨርሳለሁ ውጥንህን ቀጥል፡፡ ሁለት ሃሣብ ካንዱም ያሳጣል ፤ ሁለት አባራሪ አንዱንም ያጣል፡፡
ጭንቀት የሰውን ትኩረትን ይበትናል፡፡ የሀሳብ ክምችት የሰውን ልጅ አያሠራም፡፡ አለመረጋጋት ለምንም ውጤት አያበቃም፡፡ አጉል ፍራቻና ስጋት ወደፊት አያራምድም፡፡ ከፈራህ ወይንም እርጋታ ካጣህ አትጀምርም አትቀጥልም አታጋምስም አትጨርስም፡፡
በሙእሚን ቤት ለዱኒያ ፈተናዎች መታጠፍ እንጅ መሰበር የለም፡፡ ብሩህ ተስፋና መልካም ጥርጣሬ እንጅ ተስፋ አልባ ጉዞ አይኖርም፡፡ ማንሠራራት እንጅ መሞት አይታሰብም፡፡
በዚህ መልኩ ይህችን ህይወት እንኖራለን፡፡የዱንያ መንገድ አልጋ ባልጋ እንዳልሆነ እናውቃለን፡፡ በድሎትም ይሁን በችግር ውስጥ ፈተና አለ፡፡ እናም እጃችንን ሰብስበን ሱሪያችን ከፍ አርገን እንፋለማለን፡፡ በፊልሚያ ሜዳ የሚገኘው ድል ጣፋጭ ነው፡፡ በድካም የሚጨበጥ ነገር እርካታ ነው፡፡ ለዚሁ ነው አላህ ሱ.ወ. ለሽልማት ያንን ውድ ሀገር ጀነትን ያህል ፀጋ ያዘጋጀው፡፡
ሥራ መፍታትና ረጃጅም ክፍቶተች አላስፈላጊ ነገርን ያሳስባሉ፡፡ ነፍስያና ሸይጣንም የሰውን ልጅ ሊያስቱበት ይህንኑ ዕድል ይጠቀማሉ፡፡ ክፍተቶችን በሥራ ማራቅ ያስፈልጋል፡፡ ማንኛውም ሐላል ስራ ጥሩ ኒያ ከታከለበት ኢባዳ ነውና አጅር አለው፡፡ ሥራ መንፈስን ያድሳል ሀሳብንም ይቀንሳል፡፡
ለዱኒያና ለአጠቃላይ ተፅዕኖዎቿ አንሸነፍ፡፡ ‹የቀደር ጉዳይ ነው › ብለንም ከእውነተኛው ሞት በፊት ሺህ ጊዜ አንሙት፡፡ ብዙዎች የወረቀት ላይ አንበሳን ይሸሻሉ፡፡ አሻንጉሊትንና አርቲፊሻል ነገሮችን ይፈራሉ፡፡ ለሰባራ ሽጉጥ እጅ ይሰጣሉ፡፡ ሰውነታቸው ስለቀዘቀዘ ብቻ ሞተናል ብለው ከመንቀሣቀስ እጅ እግራቸውን ያሰሩ ፤ ሳይመቱ የሚወድቁ ፤ በማስጠንቀቂያ የሚበረግጉ ፤ ጩሀት ሁሉ ወደነሱ የሚመስላቸው ብዙ ናቸው፡፡
አማራጮች እያሉ በአንድ ሁኔታ ውስጥ ብቻ እራስን ማሰር ሞኝነት ነው፡፡ ምድር ሰፊ ናትና ተነስ ተንቀሳቀስ ፣ ሒድ ተመለስ ፤ ሙድህን ፈልግ ህይወትህን አድስ፡፡
‹ደብሮኛል› ብሎ ለረጅም ሰዓት ተጠቅልሎ የሚተኛን ሰው አንደኛ ነገር ድብርቱ አይለቀውም ሁለት - ጊዜ ቆሞ አይጠብቀውም ሶስት - በድርጊቱ ኪሳራ እንጅ ትርፍ የለውም፡፡ አንዴ ወንጀል ውስጥ ወድቄያለሁና ተስፋ የለኝም ብሎ እዚያው የሚንቦጫረቅ ሰው አንደኛ- ለውስጡ ሰላምን አያገኝም ሁለት - ሀጢዓቱ አይቀንስለትም ሶሰተኛ - አላህም አይታረቀውም ፡፡
http://t.me/MuhammedSeidABX
1.4K viewsedited 04:13