2021-03-13 16:01:20
ኢስቲቃማ (በዲን ላይ መፅናት)
(4)
ከ”ህልም አለኝ” መጽሐፍ
በሙሐመድ ሰዒድ (ABX)
........
* ......
ለምንም ይሁን ለምን ለዓላማ የሚኖርን ሰው ‹ፅናት›አለው ይሉታል ሰዎች፡፡ ከጀነት በላይ ደግሞ ትልቅ ዓላማ የለም፡፡ ጀነት ዓላማው የሆነ ሰው ታላቅ ዓላማ ይዟልና በየትኛዉም ፈተና አይበለጥም፤ ፈፅሞ በሸይጧን አይበለጥም፤ በነፍስያ አይሸነፍም፤ ለእኩይ ስሜት እጅ አይሰጥም፤ በዱኒያና በጥቅሞቿ አይታለልም አይደለልም፡፡
በአላህ ዲን ላይ የፀናን ሰው ድሎት ይሁን ችግር፤ ረሃብ አሊያም ቸነፈር ከጌታው አያርቁትም፡፡ በዱኒያ ላይ የሕይወት ቆይታ ውስጥ ለውጥ ቢያገኝ ኑሮው ይለወጥ ይሆናል እንጅ በአላህ ላይ አይለወጥም፡፡ በጌታው ይፀናል፡፡ ለቃል ኪዳኑ ይታመናል፡፡ በቃልኪዳንና ቀጠሮው ያምናል፡፡ ፅኑ ነውና ከአላህ (ሱ.ወ) ነጥቆና ነጥሎ የሚወስደው ማንም ምንም ሀይል የለም። ባርነቱ ለጌታው ብቻ ነው፡፡ በዚህ አቋሙም እንደፀና ይኖራል፤ በአመላከከቱም መሬት ይይዛል፤ እውነተኛ መርጋትንም ይረጋል።
እውነተኛ ፅናት ያለው ሰው በየትኛውም ሁኔታና ቦታ አላህ (ሱ.ወ) እንደሚያየው ያውቃል፡፡ እንደሚከታተለውም ይገነዘባል፡፡ ስለሆነም ጌታውን አጥብቆ ይፈራል፡፡ ሰዎች አጠፉ ብሎ አያጠፋም፡፡ ሰዎች ስለጠመሙም አይጠምም፡፡ ከቀናት መለወጥ ጋር አይለወጥም፡፡ ዘመኑ ነዉና ሰው እንደሆነው ልሁን አይልም፡፡ በስኬትና በዕድገትም አይቀየርም። ከአፍሪካ ወደ አሜሪካ ቢሔድ፤ ከድህነት ወደ ባለፀጋነት ቢሸጋገር፤ ከተራነት ወደ ትልቅ ስልጣን ቢንደረደር፤ ከታዋቂና ታላላቅ ሰዎች ጎራ ቢሠለፍ፤ ለሱ ምንጊዜም ቢሆን አላህ (ሱ.ወ) ነው ጌታው፡፡ አሁንም በጌታው ይፀናል፡፡ ወደዚህች ዓለም ለምን እንደመጣ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ በመሆኑም ዲኑን አጥብቆ ይይዛል-- በክራንቻው ነክሦ፤ ከደሙ ጋር አዋህዶ፤ ከነፍስ ከሥጋው ቀላቅሎ… ከነፍሱ ጋር ካልሆነ በቀር ማንም ምንም ከአላህ (ሱ.ወ) አይነጥለውም፡፡ ለሱ አላህ ነው ጌታው፤ ኢስላም ነው መንገዱ፤ ቁርኣን ነው መመሪያው፤ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የአላህ መልዕክተኛ የርሱ ነቢዩ ናቸው።
ዛሬ በዱኒያም ሆነ ነገ በአኺራ አጠቃላይ የሁለቱን ዓለም ስኬት የምንፈልግ ከሆነ እኔም ሆንኩ አንተ አንቺ የእስልምናን ጉዳይ ቀለል አድርገን እንዳንመለከት እመክራለሁ፡፡ በዲን ላይም ፅናት ይኖረን ዘንድ እማፀናለሁ፡፡ ብንፀና የምንጠቀመው እኛው ነን፡፡ ብንንሸራተትም ተጎጂዎቹ ራሣችን ነን። ደግሞም ልብ እንበል …
ትራስ ተንተርሦ ጀነት አይታሠብም፡፡ ከውድ ነገርም በቀላሉ አይደረስም፡፡ ዓለማችን መንፈሳዊነትን በሚያስቱ ከኢማንም በሚያዘናጉ በርካታ ነገሮች ተሞልታለች፡፡ ጀነት ዙሪያዋ አስደሣች ባልሆኑ ነገሮች ታጥራለች፡፡መንገዷ ልፋትን ይጠይቃል፡፡ ውጣ ውረዱ ብዙ ፈተናና መሰናክሉም ከባድ ነው፡፡ ዛሬን ካላለቀሱ የነገ ሣቅ አይታሰብም። መከራ ችግሮችን የመቋቋም፤ ፈተና መሰናክሎችን የማለፍ እጅግ የበረታና የፀና አቋም ካለን ግን በመጨረሻም ከሲራጥ ማዶ የምናገኘው ነገር ቢኖር ጀነት ነው። አዎን ኢንሻአላህ ጀነት... ጀነት ደግሞ እንደ ዱኒያ ጠፊ ሣትሆን ቋሚ አገር ነች፡፡ ስኬቱም ዘላለማዊ።
“እነዚያ «ጌታችን አላህ ነው» ያሉ. ከዚያም ቀጥ ያሉ፡- «አትፍሩ፤ አትዘኑም፤ በዚያችም ተስፋ ቃል ትደረግላችሁ በነበራችሁት ገነት ተበሰሩ፤» በማለት በነሱ ላይ መላእክት ይወርዳሉ፡፡ «እኛ በቅርቢቱም ሕይወት. በመጨረሻይቱም ረዳቶቻችሁ ነን! ለናንተም በርሷ ውስጥ ነፍሶቻችሁ የሚሹት ሁሉ አልላችሁ፤ ለናንተም በርሷ ውስጥ የምትፈልጉት ሁሉ አልላችሁ፤ «መሓሪ አዛኝ ከኾነው አላህ መስተንግዶ ሲኾን፤» (ይባላሉ)፡፡” (ፋሲለት፡ 30-32)
ወረት አስቀያሚ ፀባይ ነው። በዲን ላይ መፅናትን (ኢስቲቃማን) የመሰለ ትልቅ አቋምና ዕድል የለም፡፡ አደራችንን- ለአምላካችን ተለዋዋጭ ፊትና ባህሪ አናሳይ፡፡ በረመዳን ስንሰግድ ከርመን ከረመዳን ውጭ አናቋርጥ፡፡ዛሬ ጀምረን ነገ አንሠላች፡፡ ሰዎች በብርታትና ፅናታችን እስኪያውቁን ድረስም ለአኺራችን እንልፋ። መልካም ነገር ብናቋርጥ እንኳን አስታውሰን ተመልሰን ወደ መስመሩ እንምጣ፡፡
የሰው ልጅ ወጥ በሆነ ባህሪ የማይረጋ ቅጠ-ቢስ መሆኑን ያወቁት ታላቁ ነቢዩ በርካታ ዱዓዎችን አስተምረውናል። ከነዚህም ‘ያሙቀሊበ-ል-ቁሉቢ ሰቢት ቀልቢ አላ ዲኒክ’ የሚለው ዋንኛው ነው፡፡ ትርጉሙም ‘ቀልብን የምትገለባብጥ የሆንክ ጌታ ሆይ! ቀልቤን በዲንህ ላይ አፅናልኝ’ ማለት ነው።
በፅናት አቻ የማይገኝላቸው ታላቁ ነቢይ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ይህንን ዱዓዕ በተደጋጋሚ ያደርጉ ነበር። የኢስቲቃማ ችግር ያለብን እኛ ግን እጅጉን ተዘናግተናል። ይህን ዱዓዕ ዘወትር ማድረግ ለተቁነጥናጭ ልብ ሁሉ መድሀኒት ነው፡፡ ላልሰከነች ነፍስም እርጋታ።
በርግጥ መንገዶች ብዙ ናቸው፡፡ ትክክለኛውና ብቸኛው ግን አንድ ሲሆን እሱም- የአላህ (ሱ.ወ) እና የረሱል (ሰ.ዐ.ወ) መንገድ ነው። የአላህ (ሱ.ወ)ና የረሱሉ (ሰ.ዐ.ወ) ያልሆነ መንገድ ሁሉ ቀና ቢመስልም ጠማማ ነው፡፡ ብርሃን አይምሰለን ጨለማ ነው። መሪዎቹና አጃቢዎቹም ሸይጧን፣ እኩይ ስሜት፣ ደመነፍስና ክፉ ሰዎች ናቸው፡፡ ተከታዮቹም ጃሒሎች። እናም ዋስትና በሌለውና ማስረጃውም ሀሠት በሆነ መንገድ እንራመድ፡፡ መጨረሻው ገደል ነውና። በየዕለቱ ውሏችንን እንገምግም፡፡ ለአላህ (ሱ.ወ) ብቻ እንጂ ይህ ለስሜታችን ይህ ለሸይጣን ብለን የምንከፋፍለው ቀን አይኑረን፡፡ እግራችን ከአላህና ከረሰሉ መንገድ እንዳይንሸራተት ነቃ እንበል፡፡ የራቅን እንደሆነ እንመለስ፡፡ የተጠጋን ከሆነ ደግሞ ይበልጥ እንቅረብ።
ትንሽ ትልቁን፤ ብዙ ጥቂቱን፤ ቀልድ ቁምነገሩን የሚፅፉ ከመፃፍም የማይደክሙና የማይሠለቹ ፀሀፊ መላኢካዎች አሉብን። ካጠፋን ቶሎ እንቶብት፡፡ ክፋትን በመልካምነት እናስከትል፡፡ ትክክለኛ ኢስቲቃማ ይኑረን፡፡ ‹ወረት› የሚባለውን ባህሪ እናስወግድ፡፡ ዒባዳችን የመጣል የማንሳት የፋሽን ዓይነት እንዳይሆን።
ደግሞም ወንድሜ አደራህን፡፡ እህቴ አደራሽን... “እንደ እገሌ እንዳትሆኑ፡፡ የሌይል (የለሊት) ሶላት ይሰግድ ነበር ተወ፡፡” ሰኞ እና ሀሙስን ይፆም ነበር አቋረጠ።’ ይህ ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) ለአንድ ሰሐባቸው የመከሩት ነው።
ወዳጄ ሆይ! ኢስቲቃማ ይኑርህ- ዕድልህ አልለየምና፡፡ እጣ ፈንታህን አላወቅክምና። መቸም ቢሆን አትድከም፡፡ አልቻልኩም አልሆነልኝም አትበል፡፡ አትዘናጋ አትስነፍ፡፡ ለአላህ (ሱ.ወ) ያለህ ፍራቻም ተከታታይነት ይኑረው።
ጌታህን በማምለክና በመታዘዙ በርታ፡፡
‹እስከመቼ› ብሎ ለጠየቀ ደግሞ አላህ (ሱ.ወ) በቅዱስ ቃሉ እንዲህ ይላል።
“ሞትህ እስኪመጣ ድረስ ጌታህን አምልከው፡፡” (አል-ሒጅር፡ 99)
‹ጌታዬ ሆይ! አንተን በማውሣት፣ በማመስገንና አምልኮህን በማሣመሩ እርዳኝ፡፡› ከአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ዱዓዖች መካከል፡፡
http://t.me/MuhammedSeidABX
538 viewsedited 13:01