2021-03-19 18:46:18
የሚበልጠዉን ይዘናል … (1)
“አትጨነቁ” ከተሠኘው መጽሐፌ
ሙሐመድ ሰዒድ(ABX)
*,,,***,,,,,****
በዚህች ዱንያ ላይ በኖርኩበት ዕድሜዬ ከሰው ልጅ አንፃር ብዙ ነገሮች ሲለዋወጡ አይቻለሁ፡፡ አስደንጋጭ ነገሮችን ተመልክቻለሁ፡፡ ለ15 ዓመታት ያህል ከአልጋው ያልወረደን በሽተኛ አይቻለሁ፤ ዉብ ዐይኖች የነበራት ኮረዳ በቀኑ በብርሃኑ ብዥ ብሎበት በዚያው ሁለት ዐይኖቿ ጠፍተው አጋጥሞኛል፤ በበሽታ ምክንያት ፀጉሯ ረግፎ የተለወጠችዋንም እንዲሁ፤ ለጥቂት ዓመታት የተለየሁትን ጓደኛዬን አንደበቱ ታስሮ አግኝቼዋለሁ፡፡ ሰውነቱ ሙሉ በሙሉ ተሳስሮ ቤት ዉስጥ የቀረውንም እንዲሁ፡፡ ….
እነኚህ ሁሉ የአላህ ተዓምራት ናቸው፡፡ ዱንያ ትርዒቷ ማብቂያ የለውም፡፡ ጌታዬ አላህም እንደሻው ያረጋታል፡፡
ዱንያ ምንጊዜም ዱንያ ናት፡፡ ሰዉም ምንጊዜም ሰው ነው፡፡ ሕይወት በገጠመኝ የተሞላች ናት፡፡ አንዳንዴ ከልክ በላይ ደስተኛ እንሆናለን፤ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ምርር ብለን ራሳችንን እንጠላለን፡፡
ወንድም እህቴ ሆይ! ሁሉም ጫፍ የወጡ የዱንያ ስሜቶች ልጓምን ይፈልጋሉ፡፡ ሰከን ማለትና ተረጋግቶ ማሰብን ይሻሉ፣ ነገር ማሳደርን ግድ ይላሉ፡፡ በትኩስ መወሰን፣ በነሻጣ ቃል መግባት፣ በሐዘን ተስፋ መቁረጥ ለቁጭት ይዳርጋል፡፡
ነገር ሲያድር ይበስላል፤ የደፈረሰ ዉሃም ሲሰክን ይጠራል፡፡ በአንዲት ቅጽበት ስንደሠት ደስታው በርግጥም እውነተኛ ደስታ ስለመሆኑ መጣራት አለበት፡፡ ሐዘኑም ተጋኖ እንዳልሆነ መገምገም ይኖርበታል፡፡ ካልሆነ በጥድፊያ የሚወሰኑ ዉሳኔዎች ጉዳታቸው ያመዝናል፡፡ አደጋቸውም ይበዛል፡፡ ተረጋጉ፡፡
እና …
ከብዙ ማማረር በኋላ ዙሪያዬን ተመለከትኩ፡፡ ቆም ብዬና ጊዜ ሠጥቼ ዙሪያዬን ቃኘሁ፡፡ በዚህ የሩጫ ዘመን ጊዜ ወስደን ጥቂት ካልቆምን በስተቀር ልናያቸው የሚገቡ ብዙ ነገሮች ያመልጡናል፡፡ ያልተነካ ግልግል ያውቃል ብላችሁ በምሬታችሁ ከመቀጠላችሁ በፊት እስቲ ላንዳፍታ ቆም በሉ፡፡ ካልቆምን በስተቀር ብዙ የማይታዩን ነገሮች ይኖራሉና እስቲ ጥቂት እንቁም፡፡ እናም ቆሜ አስተዋልኩ …
በብዙ የአላህ ፀጋዎች ተከብብያለሁ፡፡ ትልቁ እምነት ነው - እስልምና ፡፡ ኢስላምን ለሠጠኝ ጌታ እኔ ምን ልሠጠው እችላለሁ!፡፡
ብዙ ነገርም ተሰጥቻለሁ፡፡ ከዋናዎቹ ብንቆጥር አንዱ ጤና ነው፡፡ አንዳንዴ ቆንጠጥ ቢያረገኝ ወደራሱ ሊመልሰኝ፣ እጄን ለዱዓ እንዳነሳ ቢያግዘኝ እንጂ ምን አደረገኝ፡፡ ጌታዬ ሆይ አንተ እንደፈለግክ አድርገኝ፡፡ እንኳን እኔ ታላቁ ነቢይ (ሰ.ዐ.ወ.) “ቁጣህ አይሁን እንጂ ምንም ብታረገኝ ግድ የለኝም፡፡” ይላሉ፡፡
ብዙ ንብረትም አለኝ፡፡ ትልቁ አዕምሮ ነው፡፡ አዕምሮን የተሠጠ ሰው ብዙ ነገር ተሠጠ፡፡ ሰው አዕምሮ ከሌለው ምድር ላይ የመገኘቱ ነገር ምንም ትርጉም የለውም፡፡
እናም አየሁ አየሁና እንዲህ አልኩ … አስተባበልን፣ ካድን እንጂ ብዙ ነገር ተሠጥተናል አልኩኝ፡፡ አላስተዋልንም እንጂ የሚበልጠውን ይዘናል፡፡
እንደኔ እንደኔ ሁሉ ነገር አለን፡፡ ቀረን የምንለው ነገር ቢኖርም የሚበዛው በእጃችን አለ፡፡ ትናንሽና ቅርንጫፍ ነገሮችን ሁሉ ባንታደልም ትልቁን ግንዱንና ዋናውን አትርፈናል፡፡ ትልቁ ነገር ዲናችን ነው፣ መሠረታዊው ጉዳይ የቆምንበት እምነት ነው፡፡ በፀና መሠረት ላይ የቆመ ሰው አይወድቅም፡፡ ዋናው ሀብት ዛሬ በሕይወት እያለን፤ ነገም ከሞት በኋላ ሊጠቅመን የሚችል ነገር ነው፡፡ እናም ወሳኙን ነገር ይዘናል፡፡ በላጩን ሀብት ጨብጠናል፡፡ ….
ይቀጥላል
http://t.me/MuhammedSeidABX
510 views15:46