2021-03-29 18:05:57
የሰርጓ ለታ (4)
*“የሰርጓ ለታን ትረካ ምነው ጨርስልን እንጂ!” አሉኝ አንዳንዶች በዉስጥ መጥተው፡፡
ብዙ ሰዎች ትረካዎች የገሃዱ ዓለም ተጨባጭ አይመስላቸዉም፡፡ የሌላ ዓለም ሕይወት ይመስላቸዋል፡፡ ለዚህም ነው አጨራረሱን ለማየት ይናፍቃሉ፤ ያቺን ምስኪን ልጅ የት አደረሳት ብለው ይጠይቃሉ ፤ ዱንያ እኮ በሚስኪኖች የተሞላች ናት። እርግጥ ነው ለሰዎች ብለን የምናበጀው የተለየ አጨራረስ የለም፡፡ የምንተርክላቸው ሰዎች በኛው መሃል ናቸዉና የእነርሱን ሕይወት በማየት ብቻ ሌላዉም ትረካዉን ማስቀጠል ይችላል፡፡
“የሰርጓ ለታ” ትረካ በሰርጉ ዕለት ምሽት በረከቱ ለሆነችው ለሚስቱ ከማዘን ይልቅ ኃይልና ጉልበትና ተጠቅሞ የአንዲትን ልጃገረድ ሥነልቦና ክፉኛ ስለጎዳው አንድ “አውሬ” ወጣት ነው የሚያወጋው፡፡ አላህ ሐላል ያደረገለትን የወሲብ ስሜት በፍቅር፣ በቀስታና በእንክብካቤ ከመወጣት ይልቅ ስሜቱ ጋልቦት እና እልህ አሸንፎት ከአዕምሮው ይልቅ ጡንቻዉንን በመጠቀሙ ምክንያት የአንዲትን እህት ሕይወት አበላሸ፡፡
ትረካው የአንድ እና ሁለት ሴቶች ታሪክ ብቻ ነው ብዬ አላምንም፡፡ ለዚህም ነው ለጀማዓው ያቀረብኩት ።
ዱንያ እንዲህ ናት እንግዲህ ወዳጆቼ፤ በአንዲት ቅጽበትና አጋጣሚ ነገሮች ይለዋወጣሉ፤ ሁኔታዎችም ይቀያየራሉ፤
ለአንዳንዱ የሰርጉ ዕለት የረጀም ደስታው መነሻ ሊሆን ይችላል፤ ለአንዳንዱ ደግሞ ከሰርጉ የሚተርፈው ነገር ቢኖር ትዝታ፣ ሐዘንና መጥፎ ጠባሳ ብቻ ይሆናል፡፡
ያች ልጅ እስከዚያች ቀንና ሰዓት ድረስ በሕይወቷ ደስተኛ ነበረች፤ ፍልቅልቅ ሳቂታም ነበረች፡፡ በያን ቀን ባጋጠማት ችግር ምክንያት የረጅም ጊዜ ደስታዋ ራቃት፤ ፈገግታዋም ሸሻት፣ ሕይወት አስጠላት፣ መኖርም ቀፈፋት፡፡
ዛሬ ላይ ወንድ ልጅ በተጠጋት ቁጥር ትፈራለች፣ ትሸክካለች፣ ትንቀጠቀጣለች፣ ነፃ ሆና ለማውራት ትቸገራለች፡፡ በዚህም የተነሳ ብዙዎችን ግራ አጋብታለች፣ እሷም ብትሆን በርካቶች እያገለሏትና እየራቋት እንደመጡ ታዝባለች፡፡ ሁኔታዋን ለማስተካከል ዉስጧ ቢፈልግም፤ የተቻላትን ያህል ከራሷ ጋር ታግላ ብትሞክርም ይህን ችግሯን መቅረፍ ግን አልቻለችም፡፡
በዚሁ ዙርያ የሚከተሉትን በመምከር መቋጫ እናበጃለን፡-
1- የሰርግ ዕለት በወጣት ተጋቢዎች ሕይወት ዉስጥ ወሳኙ ዕለት ነው፤ ተጣማሪዎች አንደኛው ከሌላኛው ኸይር ይጠቀሙ ዘንድ ሁለት ረከዓ ሰግደው ዱዓ ማድረግ ይኖርባቸዋል፤ የሙሽሮች ዱዓ ተቀባይነት አለው ተብሏል፡፡
2- ሁሌም ቢሆን ስሜት ከየትኛዉም ዓላማ በላይ እንዳይነግስ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፤ ወጣትነት እሣት ነው፤ በተለይ በዚያች ቅጽበት ራስን መቆጣጠርና መግራት ግድ ይላል፡፡
3- “አንዳችሁ እንደ እንሠሣ ሚስቱን አይገናኝ …” ይላሉ ነቢያችን ( ሰ.ዐ.ወ.)። ከሚስት ጋር በሚደረገው እዝነት፣ ልስላሴ፣ ቀስታ፣ መግባባት፣ መናበብ መቅደም ይኖርበታል፡፡
4- “ለተሰባሪዎች እዘኑላቸው …” ይላሉ የአላህ ነቢይ (ሰ.ዐ.ወ.)፡፡ ወንድ ልጅ በአልጋ ጨዋታ ራሱን ብቻ ማዳመጥ የለበትም፤ በአካልም ሆነ በሥነልቦና በሙሽሪት ላይ ጉዳት ከማድረስ ሊጠነቀቅ ይገባል፡፡
5- “ሴቶች የወንዶች እህቶች ናቸው፡፡” ብለዋል የአላህ ነቢይ (ሰ.ዐ.ወ.) ፡፡ እህትህን በምትይዘው መልኩ ሚስትህን ያዝ፡፡ ሴት ልጅ እዝነት፣ ልስላሴ፣ ፍቅር፣ እንክብካቤ፣ ክብር ያስፈልጋታል፡፡
እህት ሆይ!
6- ከጉዳት በኋላ መጠንከርና ወደፊት ማየት ብቻ ነው የሚያዋጣው፤ የፈሰሰ ዉሃ አይታፈስም፤ ያለፈዉን የጉዳት ሕይወትሽና ታሪክሽና ዝጊበት፣ ለትምህርት ካልሆነ አታንሺው፤
7- ያለሽበትን ሁኔታሽን ለማስተካከልም አትፍሪ፤ አትፈሪ፣ አትሳቀቂ፡፡ መፍራትም ሆነ ማፈር ነገሮችን ሊያስተካክሉ አይችሉም፡፡
8- ከጉዳትሽ ለማገገም መልካም የዲን እህቶችንና ወንድሞችን አማክሪ፡፡ ከነርሱም ጋር ዋዪ ተመካከሪ፡፡
9- በሥነልቦና ባለሙያ ታዪ፤ ምክሮችንም ተቀበዪ፡፡ በሽታዉን ያልተናገረ መድኃኒት አይገኝለትም፡፡
10- ተስፋ የለኝም አትበይ፤ ራስሽንም አታግልይ፤ ተስፋ የሌላቸው የሞቱ ብቻ ነው፡፡
11- አላህ አሁንም ሰው ጥሩ ሰዎች ሞልተዉታል፤ በእውነት አፍቅሮ የቀረበሽ፤ በሥነምግባሩ ጥሩ እና ታማኝ የሆነ ሰው ለጥምረት ከጠየቀሽ ችግርሽን በግልጽ ንገሪው፤ ተወያዩበት፡፡ ኢንሻአላህ በትዕግስትና በእምነት አብራችሁ ትፈቱት ይሆናል፡፡
12- በራስ መተማመንሽን አዳብሪ፤ ኢንሻአላህ ሁሉም መልካም ይሆናል በይ፡፡
13- ዱዓ፣ ሶደቃ እና መልካም ሥራ የማይፈቱች ችግር ምን አለ!!…
ጌታዬ የተጎዱትን ሁሉ ይጠግን፣ የታመሙትን ይዳብስ።
እሱ በሁሉ ነገር ላይ ቻይ ነዉና።
ሰላማችሁ ይብዛ፡፡
መልካም ምሽት
http://t.me/MuhammedSeidABX
1.4K views15:05