Get Mystery Box with random crypto!

የሰርጓ ለታ (1) ** 'ነይማ እስቲ ኸዲጃ እምንወያየው ነገር አለ።' አሉ ሸይኽ ዐሊ ዛሬ ቀን | ABX

የሰርጓ ለታ (1)
**
"ነይማ እስቲ ኸዲጃ እምንወያየው ነገር አለ።" አሉ ሸይኽ ዐሊ ዛሬ ቀን ላይ ስለመጡባቸው እንግዶች ከባለቤታቸው ጋር መክረው ለመወሰን ብለው፡፡
እናት ኸድጃ ደግመው ባይሰሙት የሚመርጡት ወሬ ነበር። በርግጥም ከባልተቤታቸው ጋር መግባባት አልቻሉም።
“ትልቅና የተከበረ፣ የምናውቀው እና የሚያውቀን ቤተሰብ ነው፤ ልጃችሁን ለልጃችን እያሉ እንዴት እንከለክላለን?”  አሉ አባት ሸይኽ ዐሊ፡፡
"በይሉኝታ ታስረን ራሳችንንም ልጃችንንም መጉዳት የለብንም።" አሉ እናት ኸዲጃ ።
 “እሷስ ብትሆን ሊነገራት ይገባል፤ እንንገራትና ምን እንደምትል እንስማ !” አሉ ወ/ሮ ኸዲጃ ግራ እየተጋቡ፡፡
“ምን እሷ ምን ታውቃለች? እኛ ነን ክፉ ደጉን፤ ባለጌ ጨዋዉን አይተን የምንመርጥላት!” አሉ አባት፡፡
“እንግዲያዉስ እንዲያ ከወሰኑ እኔ የለሁበትም፤ የልጁን መጥፎነት እንደሁ አገር ያወቀው ነው፤ ገና የሚታወቅና የተከበረ ቤተሰብ ነው በማለት ምን ብዬ ነው ጨዋ ልጄን የምሠጥ!” አሉ እናት ክፉኛ ተናደው፡፡
እናትና አባት ኃይለኛ ሙግት ዉስጥ ገቡ፡፡ ዉዝግቡ ከረረ። አባት ፎከረ፡፡ የት ትወስጂያት እንደሆነ እናያለን አለ፡፡
እናትም ዛተች፣ ልጄንማ ለዚህ ከይሲ አትድሩትም! አለች፡፡

ጠያቂው ወገን መልስ ፍለጋ ድጋሜ ሽማግሌ ላከ፡፡ ቤተሰብ ተጨናነቀ፡፡ ሰፈር ጎረቤት ጉዳዩን ሰማ። ያልሆነ ወሬ ተወራ።
ቤተዘመድና ዘመድ ተሰባሰበና መከረ፡፡ ከብዙ ክርክር በኋላ የአባት ቃል አሸነፈ፡፡ ልጅትም ተለመነች። በመጨረሻም ሳትፈልግ፣ ሳትወድ በግድ ለማታውቀው ሰው ተሠጠች፡፡

በሰርጉ ቀን …
ሙሽሪት መንገድ ላይ ድንገት ታመመች፤ ድክምክም አደረጋት፣ አስመለሳት፣ እሷም፣ ባሏም አጃቢዎቿም ግራ ተጋቡ፣ መኪናው ይሁን ሙቀቱ አልታወቀም። አስሬ እያረፉና እየተናፈሱ እንደምንም ጉዞ ወደ ሙሽራው ቤት ሆነ፡፡ አይደረስ የለ ከብዙ እንግልት በኋላ ተደረሰ፡፡ ደማቅ ጭፈራ ነበር።
ሙሽራዉና ሙሽሪት ወደ ክፍላቸው እንዲገቡ ተደረገ፡፡ ሙሽሪት አሁንም እንደደከመች ነው፤ ምግብ አልቀመሰችም፣ የቀመሰችዉም ሆዷ ዉስጥ አልተረጋም፣ ቬሎዋን ጭምር ማውለቅ አቃታት፤ ሰዉነቷ ከዳት፣ ሄዳ እክፍሉ ዉስጥ ካለው ሶፋ ላይ ዘፍ አለች፡፡ ተጋደመች።
ባሏ ሊጠጋት ሲል አትንካኝ እዚሁ ልተኛ አሞኛል አለችው፡፡
አባባሏ ምቾት አልሠጠዉም፣ ተናደደ፣ ነብር ሆነ፣ 
እንዴት በዚህ ቀን ያማታል? የሚል ይመስላል ጥያቄው፤ ሌላ ነገርም እንደመጠርጠር አደረገው።
እንዳኮረፈ ሄዶ አልጋው ላይ ጋደም አለ፡፡

ሙሽሪት ትንሽ ሻል ሲላት ወደ አልጋው ሄዳ ከጎኑ ተኛች፣ እንዳኮረፈ ነው፤ እሱ ማባበል የሚገባትን ጭራሽ እሷ ታስረዳው ጀመር።
በዚሁ መሃል አሁንም ጋበዛት። ደክሞኛል አቅም የለኝም አለችው። በዚህን ጊዜ አልሰማትም፣ አላዘነላትም። ንቀትም መሰለው፣ ጠዋት ለጓደኞቹ ስለየትኛው ወንድነቱ ያውራ፣
ከሷ ህመምና ድካም በላይ ስሜቱ ጣርያ ነክቷል፤ ህሊናዉን ገፋ፣ እዝነቱን ተከላከለ፣ ስሜቱን አዳመጠ፣ ለሥጋው ጆሮ ሠጠ።

በዚያ ላይ ልጅት ጨዋ እንደሆነች ያውቃል፣ ትዝ ሲለው ቋመጠ፣ ምራቁን ዋጠ፣ ለሦስተኛ ጊዜ
ተጠጋት፣ ለመነችው፤ እሱ ግን ገፍቶ የመጣ ስሜቱን መቆጣጠር አልቻለም፤ የተወጣጠረ ሰዉነቱን ማርገብ ሞት ሆነበት፣ ንደረደረ፣ ተአስገድዶ የመድፈር ያህል በገዛ ሚስቱ ላይ እንደ አውሬ ሰፈረባት፤
ከዚያ በኋላ ስለራሱ እንጂ ስለሷ ሁኔታ ግድ አልነበረዉም፡፡ እሷም የሚሆነዉን በሰመመን ዉስጥ ሆና ከመታዘብ ዉጭ ምንም ማድረግ አልቻለችም፣ ራሷን መከላከል የማትችል ጀናዛ ነበረች …

ይቀጥላል

http://t.me/MuhammedSeidABX