Get Mystery Box with random crypto!

የሰርጓ ለታ (3) ********** የተወለደው ልጇን ሥሙን ሷቢር አለችው፡፡ ከብዙ ትዕግስትና ፈ | ABX

የሰርጓ ለታ (3)
**********

የተወለደው ልጇን ሥሙን ሷቢር አለችው፡፡ ከብዙ ትዕግስትና ፈታኝ ፅናት በኋላ ነበር የተወለደው፡፡ አንዳንድ ሀሳቦች አልፎ አልፎ ከሚረብሷት በስተቀር ከሰዉዬው ቤት ከወጣችበት ጊዜ ጀምሮ ሰላም አገኘች፡፡ አይታ እንዳላየች፣ ተጎድታ እንዳልተጎዳች ሆና ለመኖር ታገለች፡፡ በአራስነት ጊዜዋ ከወላጆቿ ጥሩ እንክብካቤ አገኘች፡፡

 ቀናት ሄዱ፣ በአንድ ቀን  በሰርጓ ዕለት በተፈጠረ ግብግብ ካገኘችው ልጇ ጋር አርባ ቀናትን ተኝታ አሳለፈች፡፡ የልጇም ሆነ የሷ ጤና ጥሩ ነው፡፡ የልጇ ነገር ግርም ይላታል፡፡ ዕድሉ ነው እንግዲህ፤ ጀሊሉ ቀድሞዉኑ ተፈጠሪ ያላት ነፍስ ማንም ምንም ሊያስቀራት አይችልም ለካ! ትላለች፡፡

የአራስ ቤት ጊዜ አለፈ፣ በሂደት ልጇም ጠነከረ፣ እሷም ተነሳች፣ በአካልም በመንፈስም በደንብ ለመቆም ሞከረች፣ ሥራም ጀመረች፡፡
አቤት የሴት ልጅ ፈተናዋ!፡፡

የተወለደው ልጅ እንዳያድግ የለ በዋናነት በአያቶቹ ቤት አደገ፤ ሦስት እና አራት ዓመትም ሆነው፡፡ ያኔ ሰዉነቷ ሳይጠነክር ገና በ16 ዓመቷ ነበር ያገባችው፡፡ በልጅነት ዕድሜዋ ልጅ ታቀፈች፣ ወልዳ ተነስታም ቢሆን ገና አንድ ፍሬ ልጅ ትመሰላለች፡፡ እንደገና ቆነጀች፣ እንደገና ተመለሰች፣ እንደ አዲስ በራች፣ በሥራ ቦታና በየአጋጣሚው ሁሉ ዐይን ዉስጥ ገባች፣ በተመልካቾች ታየች፣ ፈላጊዎቿም ተከታትለው መጡ፣ ለትዳር ጠየቂዎቿ በረከቱ፡፡

ግና በተጠየቀች ቁጥር በረገገች፣ ደነበረች፣ ባነነች፡፡ የሰርጓ ለት ጉዳቷ ዛሬም ድረስ እየታወሳት ይረብሻታል፤ ለብሳ ቢያምርባትም ዉስጧ አልተደራጀም፣ ህመሟ አልሻረላትም፣ ቁስሏ አልደረቀም፣ ጠባሳዋ አልጠፋም፣ ሰዉነቷ አልተዘጋጀም፣ መንፈሷ አልጠገገም፡፡ በሷም ይሁን በቤተሰብ በኩል አድርገው የሚመጡ ጥያቄዎች ከቀን ወደ ቀን በዙ፡፡

ሀያ ዓመቷ ላይ ያለች ትኩስ አፍላ ወጣት ናት፡፡ ግና በወንድ ምክንያት ወንድ የሚባል ፍጡር ሁሉ አስጠላት፣ ሁሉም አንድ መሰሏት፣ ስሜታቸዉን ብቻ ተከትለው የሚንጉዱ ጨካኝ አረመኔዎች ። አታምናቸዉም፣ በሙሉ ልብም አትቀርባቸዉም፣ ከአንድና ሁለት ቃላት በላይ አታወራቸዉም፡፡

አብዛኛው ሕይወቷ ብቸኝነት ነው፣ ሥራ እና ቤት፣ ክፍሏና ሳሎን፡፡ ብዙ ወሬዋ ከጌታዋ ጋር ነው፡፡  ሶላት፣ ዱዓና ፆሟ ላይ ብርቱ ናት፡፡ ብርቱ! በዚህ ፈታኝ ዓለም ብርቱነቷ እስከመቼ ይቀጥል ይሆን!

ጠያቂዎቿ እንቢተኝነቷን ሲያዩ ይገረማሉ፤ ሚስጢሯን ስለማያውቁ ግራ ይጋባሉ፡፡ ጎረቤት የመለሰቻቸዉን ወንዶች ይቆጥራል፣ ዘመድ ኃይለኝነቷን ያወራል፣ ባዳ ሴት መሆኗን ይጠራጠራል፡፡
ቆንጆ ናት፣ ወጣት ናት፣ ምንድነው ወንድ እንዲህ የሚያሸሻት ይላሉ ብዙዎች፡፡ በርሷ ሲደክማቸው በወንድሞቿና በጓደኞቿ በኩል ያስጠይቃሉ፣ መልሷ ቁጣ ነው፤ ንግግሯ ኩርፊያ ነው፣ ሁኔታዋ ሽሽት ነው፡፡ ረጋ ብላ ሻል ያለ መልስ ሠጠች ከተባለ ላስብብት ነው፤ ከዚያ ፈቃደኛ አይደለሁም፣ ዝግጁ አይደለሁም፣ ተወኝ፣ ልቅርብህ፣ … እና የመሣሠሉት፡፡

ቀናት ሄዱ፤ በቀናት መካከል አንዳንድ ጊዜ ቆም ብላ ታስባለች፤ የወደፊት ሕይወቷን አሻግራ ትመለከታለች፣ እስከመቼ ድረስ እንዲህ ልኖር ነው ግን? ትላለች፤ ግራ ይገባታል፡፡ ትጠይቃለች????? ዕድሜ ልኳን ወይንስ!! ....ስታስበው በመሃል ትባንናለች፤ ትደነግጣለች፣ ትሸበራለች፡፡

 አንዳንዴ ደግሞ መጥፎ ነገር ያሳስባታል፤ ያንን ሰዉዬ መበቀል ታስባለች፣ ያቺን ቀን፣ እጇን ይዘው የሠጧትን ወላጆቿን ሁሉ ትረግማለች፡፡ ዕድሏ እንዳበላሹ፣ ሕይወቷን እንዳሰናከሉ፣ ጉዞዋን እንዳደናቀፉ፣ ወጣትነቷን እንደቀጩ ይሰማታል፡፡

ባስ ሲልም ከፍተኛ ስጋት ያድርባታል፣ ፍርሃት ይወራታል፣ በቃ ካሁን ወድያ ወጣትነቷን ላታይ ነው፤ በዕድሜዋ ላትዝናና ነው፣ ፍቅርን ላታጣጥም ነው፣ ቤተሰብ ላትመሠርት ነው፣ ይህ ሁሉ ይመጣባትና ትጨነቃለች፡፡ ግራ ተጋባለች፣ ክንፏን እንደተመታች ወፍ ተስፋ ትቆርጣለች፡፡

 ልጇ መጽናኛዋ ነው፣ የኑሮ ትርጉሟ ነው፣ ተስፋዋ ነው፣ ጉልበቷ ነው፣ ማታ እሱን ታቅፋ ታድራለች፣ ቀን እሱ ይዛ ትወጣለች፣ ዚያራ ሽርሽር ትሄዳለች፡፡

የተቀረው ሕይወቷ ባዶ፤ ዙርያው የተከረከመ ይሆንባታል፤ … አንዳንድ ጊዜ መልካም ሀሳቦች ይመጡላታል፡፡ እዝነት አላቸው፣ ሻል ይላሉ ብላ ላሰበቻቸው ለሚጠይቋት ወንዶች ስለ ችግሯ ማማከርና መንገር ታስባለች፤ ግና ተመልሳ ትተወዋለች፣ ድፍረት ታጣለች፤ ቢስቁብኝስ፣ ቢሸሹኝስ፣ ሙድ ቢይዙብኝስ፣ ቢያስወሩብኝስ … እያለች ትጨነቃለች፡፡ ብዙ ሰዎች ዛሬ ላይ ራስ ወዳድ ሆነዋል፤ ችግሯን ቢያውቅላትም ከነእንከኗ የሚቀበላት፣ የሚሸከማት፣ ጊዜ ወስዶ ፣ ነገሩን ቀለል አድርጎ፣ ትዕግሥት ተላብሶ ... አካሏንና ሥነልቦናዋን የሚያክም ያለ አይመስላትም ...

 ለአንዳንድ በጣም ለምትቀርባቸው ሰዎች መንገር ታስብና ደግሞ እነርሱን ማስጨነቅ እንዳይሆንባት ትፈራለች፣ ለነርሱ ታስባለች …
በዚህ መልኩ ….

ይቀጥላል …

http://t.me/MuhammedSeidABX