Get Mystery Box with random crypto!

አልሃኩም አት-ተካሡር በብዛት መፎካካር (ጌታቸሁን ከመገዛት) አዘናጋችሁ ************** | ABX

አልሃኩም አት-ተካሡር
በብዛት መፎካካር (ጌታቸሁን ከመገዛት) አዘናጋችሁ
**************
ኢብኑ ከሢር እንዳብራሩት 'የሰው ልጅ ምቾትና ዕብሪት የተሞላባቸው ፉክክሮች የመጪውን ዓለም መጀመሪያ ተደርጎ የሚቆጠረውን መቃብርን ያስረሳሉ። ይህም ሰዎች በሞት አማካይነት ወደዚያ ወደሚጠሉት ጉድጓድ እስኪገቡ ድረስ በዝንጋቴ ላይ እንደሚዘወተሩ ያሳያል።' ብለዋል ።


ኢማም አሕመድ ዐብደላህ ኢብን አል-ሻኪር (ረ.ዐ) እንዲህ ማለቱን ዘግበዋል “የአላህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) 'አልሃኩም አት ተካሡር ”ን እያነበቡ መጣሁ፤ ከዚያ በኋላ እንዲህ አሉ፡-
“ የአደም ልጅ ገንዘቤ ገንዘቤ ይላል። ከተመገበዉና ከጨረሰው፣ ለብሶ ካሳለቀው፣ ወይም በምጽዋት  ከሰጠዉና ተቀማጭ ከሆነለት ውጭ ምንም የሌለው  ሲሆን።”

የአላህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) የሚከተለውን ሲናገሩ ሰማሁ በማለት አነስ ኢብኑ ማሊክ (ረ.ዐ) አስተላልፈዋል፡-
“ የአደም ልጅ ዕድሜው እያረጀ ሲሄድ ሁለት ነገሮች አይለዩትም፤ እነርሱም ዱኒያን መውደድና፣ ረዥም ዕድሜ ለመኖር መመኘት ናቸው።"

አል- ሓፊዝ ኢብን ዐሳኪር የአል-አሕነፍ ኢብን ቀይስን የሕይወት ታሪክ ሲጽፉ እንዲህ ብለዋል፡- “አንድ ጊዜ አሕነፍ አንድ ሰው ዲርሃም ይዞ ያያል። “ይህ ዲርሃም የማን ነው? አለ። የያዘው ሰው “የኔ ነው” አለው። አል-አሕነፍ በመልካም ነገር የአላህን ምንዳ በመሻት ካወጣኸው ያንተ ነው ካለው በኋላ፡-
 በመልካም ነገር ላይ ስታወጣው፣
  ሀብትህ  ቀላል ይሆናል ጣጣው
 ጨምድደህ በመያዝ ከሳሳህ
ያሳርህ ሰበብ ይሆናል የመከራህ ።
በማለት የአንድን ሰው ግጥም አነበበ።
“ተከልከሉ ወደፊት (ውጤቱን ታውቃላችሁ ከዚያም ተከልከሉ ወደፊት ታውቃላችሁ።) (አት ተካሡር 3-5) የሚሉትን አያዎች አስመልክቶ አል-ሐሰን አል በስሪ (አላህ ይዘንላቸውና) “ይህ ተደጋጋሚ ዛቻ ነው” ብለዋል።
  
በሶሒህ የሚከተለው ተላልፏል፡-
ዑመር ኢብን አል-ኸጧብ (ረ.ዐ) ወደ አላህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ›ወ) ሲገቡ ባለቤቶቻቸው አናደዋቸው በአንድ ክፍል ውስጥ ጋደም ብለው አገኙዋቸው። የተጋደሙበት ምንም ዓይነት ምንጣፍ ያልተደረገበት ባዶ ሰሌን ላይ ነበር። በቤቱ ውስጥ ከዘንባባ ቅጠል የተሠራ ትራስ በስተቀር አንዳች ቁሳቁስ አልነበረም። ዑመር (ረ.ዐ) ይህን ሁኔታ ሲያዩ ማልቀስ ጀመሩ። የአላህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) “ለምን ታላቅሳለህ ዑመር ሆይ!” አሏቸው። ዑመር (ረ.ዐ)እንዲህ አሉ፡- “ የአለህ መልዕከተኛ ሆይ! ኪስራና ቄሳር እጅግ ባለፀጎች ሲሆኑ የዚህችን ዓለም ፀጋዎች ተስጥተው ይምባሻበሻሉ። እርስዎ ግን አላህ ከፍጡራኑ ሁሉ አስበልጦ የመረጠዎት ሆኖ ሳለ ይህን የመሠለ ሕይወት ይገፋሉ።” ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ አሉ “የኸጣብ ልጅ ሆይ! መጪው ዓለም ከቅርቢቱ ዓለም እንደሚበልጥ ትጠራጠራለህን? እነዚህ ሰዎች (የበጎ) ሥራዎቻቸውን ምንዳ በዚህች ዓለም ላይ እየተሰጡ ነው።”

  አቡ ሰዒድ አል-ኹድሪ(ረ.ዐ) እንዲህ ሲሉ አስተላልፈዋል፡- “የአላህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ሚንበር ላይ ተቀመጡ። እኛም በዙሪያቸው ተቀመጥን። እንዲህ አሉ፡- ከኔ(ሕልፈት) በኋላ የምፈራላችሁ የሚከፈትላችሁን የዚህችን ዓለም ተድላና ውበት(ጌጥ) ነው።” (ቡኻሪና ሙስሊም)
  
የአላህ መልዕክተኛ(ሰ.ዐ›ወ) ኃያሉ አላህ እንዲህ ብሏል በማለት መናገራቸውን አቡ ሁረይራ (ረ.ዐ) አስተላልፈዋል፡-
 “የአደም ልጅ ሆይ! እኔን በማምለክ ራስህን ብታስጠምድ ልብህን (በሃብት) በመሙላት ከድህነት አወጣሃለሁ። ካልሆነ ግን ልብህን (ደረትህን) በዓለማዊ ጉዳዮች በመሙላት ድህነት እንዳይለቅህ አደርጋለሁ።”

ዘይድ ኢብኑ ሣቢት(ረ.ዐ) የአላህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ›ወ) የሚከተለውን ሐዲሥ አል-ቁድስ ሲናገሩ ሰማሁ አሉ፡-
“ግቡ (ትኩረቱ) ሁሉ ለዚህች ዓለም ሕይወት የሆነ ሰው  ጉዳዩን ሁሉ በመበታተን ድህነቱን በሁለቱ ዓይኖቹ መሃል አደርግበታለሁ። እኔ የወሰንኩለትን እንጅ አንዳች አያገኝም። ግቡ(ትኩረቱ) ሁሉ የመጪው ዓለም ጉዳዮች የሆነ ሰው ሃብቱን ሁሉ በልቡ ውስጥ አደርግለታለሁ። ይህች ዓለም (ዱኒያ) ወዳም ሆነ ተገዳ ትመጣለታለች።” 

   አቡ ሁረይራ(ረ.ዐ) እንዳስተላለፉት የአላህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡-“ ከእናንተ (በሃብት) ዝቅ ወዳለው ሰው ተመልከቱ። ከፍ ወዳለው አትመልከቱ። ይህን ማድረጋችሁ የአላህን ፀጋዎችና ውለታዎች አሳንሳችሁ እንዳታዩ ይረዳችኋልና።”

አቡ ሁረይራ (ረ.ዐ) እንዳስተላለፉት የአላህ መልዕክተኛ(ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡-
“የዲናር የዲርሃምና የውብ አልባሳት ባሪያ ከሰረ። ሲሰጥ(ሲያገኝ) ይደሰታል። ካልተሰጠ(ካጣ) ደግሞ ይከፋዋል።”

ምንጭ ፦ ወደ አላህ ሽሹ መጽሐፍ
በአሕመድ ሑሴን (አቡ ቢላል)
ነጃሺ መፃሕፍት መደብር