2022-09-06 02:06:37
በጥቁር ገበያ የአንድ ዶላር ምንዛሬ ዋጋ ከ90 ብር በላይ መድረሱ ተስተዋለ።
ለጥቁር ገበያው መስፋፋት ዋና የዶላር ምንጭ የሆነውን ሕገ ወጥ የሃዋላ እንቅስቃሴ ነው ያለው ብሄራዊ ባንክ ዝውውሩ የሚከናወንባቸውን የሒሳብ ቁጥሮችን የመለየት ሥራ እየሠራ መሆኑን ለባላገሩ አብራርቷል።
ከብር አንፃር የዶላር ዋጋ እለት ከእለት እየጨመረ ይገኛል፡፡
በአዲስ አበባ መደበኛ ባልሆነው በጥቁር ገበያ ባለፉት ጥቂት ቀናት ዶላር ከፍተኛ ጭማሬ ማሳየቱን የባላገሩ ዘጋቢ ባደረገው ቅኝት ተረድቷል።
ካሳለፍነው ሳምንት ጀምሮ አንድ ዶላር በጥቁር ገበያው ከ85 እስከ 87 ብር ድረስ በመመንዘር ላይ እንደሚገኝ እና በተለያዩ ሁኔታዎች ይህ ዋጋ እስከ 92 ብር ድረስ ከፍ እንደሚል ባላገሩ ቴሌቪዥን ብሔራዊ ቴያትር አካባቢ ከሚገኙት የጥቁር ገበያ መንዛሪዎች መረዳት ችሏል፡፡
በመደበኛው የምንዛሬ ገበያ አንድ ዶላር በ53 ብር አከባቢ እየተመነዘረ ይገኛል። በአሁኑ ጊዜ በጥቁር ገበያ እና መደበኛ ገበያው መካከል ያለው ልዩነት ከ26 ብር በላይ ሆኗል።
የዶላር ዋጋ መጨመሩ በአገሪቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመጣው ዋጋ ንረት ላይ የራሱን የሆነ ጫና የሚያሳድር መሆኑን የምጣኔ ኃብት ባለሞያው ዶ/ር አጥላው ዓለሙ ያነሳሉ፡፡
ለጥቁር ገበያው መናር የአገሪቱ ወጪ እና ገቢ ንግድ አለመመጣጠን መሠረታዊ ምክንያት መሆኑን የምጣኔ ሃብት ባለሞያው ደ/ር አጥላው ገልጸዋል፡፡
አገሪቱ በቂ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት ባለመቻሏ ነጋዴው ማህበረሰብ በቂ ዶላር በባንክ ቤቶች በኩል ማግኘት አለመቻሉን አንስተዋል፡፡
በዚህም ምርት ከውጭ የሚያስገቡ ነጋዴዎች የጥቁር ገበያውን እንደ ዋና የውጭ ምንዛሬ ምንጭነት እየተጠቀመበት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ይህም የውጭ ምንዛሬ ፍላጎቱን እንዳሳደገው አብራርተዋል፡፡
የጥቁር ገበያውን ለመቆጣጠር በዋናነት የባንኮችን የዶላር ክምችት ማሳደግ እንደሚገባ የምጣኔ ሀብት ባለሞያው የነሱ ሲሆን ለዚህም ምርትን በማሳደግ ላይ በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ የጠየቅናቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አቶ ፍቃዱ ድጋፌ ከሰሞኑ ሰሜናዊ የአገራችን ክፍል ዳግም ያገረሸውን ጦርነት ተከትሎ የጥቁር ገበያው የምንዛሬ ዋጋ ጭማሪ ማሰየቱን ጠቁመዋል፡፡
ሩሲያ እና ዩክሬን የገቡበትን ጦርነት ተከትሎ የዓለም ምርት ዋጋ ጭማሪ በማሳየቱ የውጭ ምንዛሬ ፍላጎት መጨመሩንና ይህን ተከትሎ በጥቁር ገበያ የምንዛሬ ዋጋ እድገት ማሳየቱን ምክትል ገዥው አብራርተዋል፡፡
በዓለም ገበያ ላይ የዩሮ ዋጋ እየቀነሰ መምጣቱን ያነሱት አቶ ፍቃዱ በተቃራኒው የዶላር ፍላጎቱ ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመዋል፡፡
ለጥቁር ገበያው መስፋፋት ዋና የዶላር ምንጭ የሆነውን ሕገ ወጥ የሃዋላ መሆኑን ያነሱት አቶ ፍቃዱ፤ ባንኩ የዚህ እንቅስቃሴ ማካሔጃ የሒሳብ ቁጥሮችን የመለየት ሥራ እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፤ በቅርቡም በዚህ እንቅስቃሴ ላይ ሲሳተፉ በተገኙ የሒሳብ ቁጥሮች ላይ እርምጀ እንደሚወሰድ ጨምረው አንስተዋል፡፡
በመደበኛ የዶላር ምንዛሬ ገበያውም ላይም ቢሆን ባለፉት ስድስት ወራት በአንድ ዶላር የምንዛሬ ዋጋ ላይ የ2 ብር ከ60 ሳንቲም ጭማሪ እንደተደረገበት ቁጥራዊ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
ይሳቅ አበበ
ባላገሩ ቴሌቭዥን
5.1K views23:06