2022-09-22 11:06:32
ዐቃቤ ህግ ዶ/ር ሙሉቀን ሀብቱን ጨምሮ በ11 ተከሳሾች ላይ በሙስና ወንጀል ክስ መሰረተ
ዐቃቤ ህግ የኮንዶሚኒየም እጣ እንዲጭበረበር አድርገዋል የተባሉት የቴክኒክ ሙያ ሥልጠናና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ኃላፊ የነበሩትን ዶ/ር ሙሉቀን ሀብቱን ጨምሮ በ11 ተከሳሾች ላይ በሙስና ወንጀል ክስ መስርቷል።
ተከሳሾች፡-1ኛ. ዶ/ር ሙሉቀን ሀብቱ ምሩፅ (በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቴክኒክ ሙያ ስልጠናና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ የቢሮ ኃላፊ የነበረ)
2ኛ. አብርሃም ሰርሜሎ ኪዳኔ (በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቴክኒክ ሙያ ስልጠናና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ምክትል የቢሮ ኃላፊ የነበረ )
3ኛ. ኩምሳ ቶላ ገኖ (በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን የአይሲቲ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የነበረ )
4ኛ. መብራቱ ኪ/ማርያም በርሄ (በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቴክኒክ ሙያ ስልጠናና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ የሶፍትዌር ሲስተም ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የነበረ)
5ኛ. ስጦታው ግዛቸው ደገፋ (በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቴክኒክ ሙያ ስልጠናና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ የሶፍትዌር ፕሮግራመር የነበረ)
6ኛ. ባዩልኝ ረታ ጸጋ (በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቴክኒክ ሙያ ስልጠናና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ የሶፍትዌር ፕሮግራመር የነበረ)
7ኛ. ሚኪያስ ቶሌራ ወ/እየሱስ (በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን የሲስተምና ዳታ ቤዝ ባለሙያ የነበረ)
8ኛ. አሚ አምባዬ ማሞ (በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቴክኒክ ሙያ ስልጠናና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ የሶፍትዌር ፕሮግራመር የነበረ)
9ኛ. ዮናስ ወ/ጊዮርጊስ ነዳሳ (በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን የመረጃ ባለሙያ የነበረ)
10ኛ. ዘካርያስ አያለ ገቢ (በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን የሲሰተም ዳታ ቤዝ አድሚንስትሬተር)
11ኛ. ኤደን ካሳሁን ተሰማ ሲሆኑ፤ ዐቃቤ ህግ 3 ክሶችን የኢፌደሪ ፍትህ ሚኒስትር የጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀኔራል ዐቃቤ ህግ በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት በትላንተናው ዕለት ክስ መስርቶባቸዋል፡፡
የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀኔራል ዐቃቤ ህግ በ1ኛ የክስ ዝርዝር በ1ኛ፣ 2ኛ እና በ3ኛ ተከሳሾች ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊነት ላይ ተመድበው ሲሰሩ የማይገባ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለማስገኘት በማሰብ ስልጣናቸውን ወይም ሃላፊነታቸውን ተጠቅመው በሀምሌ 01 ቀን 2014 በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጋራ መኖሪያ ቤቶች እድለኞችን በፍትሃዊ የሎተሪ እጣ በሲስተም ለመለየት ተብሎ ከወጣው የ14ኛ ዙር የ20/80 እና የ3ኛ ዙር የ40/60 የወጣበትን ሲስተምን የማልማት፣ እጣ የማውጣት እና የኮንደሚኒየም ቤት የቁጠባ ተመዝጋቢዎችን የዳታ ቅብብሎሽ ሂደትን በተሰጣቸው ኃላፊነት መሰረት ሊከላከሉት፣ ሊጠብቁት እና የጥራት ደረጃውን በጠበቀ መንገድ ለውጤት ማብቃት ሲገባቸው፤ 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች በሥራ ሃላፊነታቸዉ ሊጠብቁትና ሊከላከሉት የሚገባዉን የመንግስትና የህዝብ ጥቅም ወደጎን በመተዉ እድለኞችን መርጦ የሚያወጣ ሲስተምን የማልማት፤ የፕሮጀክት ሥራ የጥራት ደረጃውን ጠብቆ እንዲለማ ማድረግ ሲገባቸው ሲስተሙ በትክክለኛ መንገድ ባለማበት እና ደህንነቱ ባልተጠበቀበት ሁኔታ፣ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ለሲስተሙ የደህንነት ማረጋገጫ ሳይሰጠው ለእጣ ማውጣት እንዲወል በማድረግ፣ እጣው ዝቅተኛውን የቁጠባ መስፈርት የሚያሟሉ፣ ከአዲስ ተመዝጋቢነት ወደ ነባር ተመዝጋቢት የተቀየሩ፣ ቁጠባቸውን ያቋረጡ ግለሰቦች የእጣው ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያስችል ክፍተት እንዲፈጠር በማድረጋቸው 3ኛ ተከሳሽ የተመዝጋቢዎች ዳታ እንዳይቀየር መጠበቅ እና መከላከል ሲገባው ዳታው ተጋላጭ እንዲሆን በማድረግ ህገ-ወጥ ጥቅሞችና ጉዳት እንዲደርስና እጣዉን ለመሰረዝ የሚያበቃ ከፍተኛ ክፍተት እንዲፈጠር በማድረጋቸዉ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈጸሙት የመንግስት ስራን በማያመች አኳኋን በመምራት ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡
2ኛ ክስ ከ4ኛ እስከ 10ኛ በተጠቀሱት ተከሳሾች ላይ ብቻ የቀረበ ሲሆን፤ 4ኛ ተከሳሽ የእጣ ማዉጫ ሶፍትዌሩን በበላይነት የሚመራዉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቴክኒክ ሙያ ሥልጠናና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ የሶፍትዌር ሲስተም ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በመሆኑ ህገወጥ ድርጊቱን ማስቆም ሲገባዉ በድርጊቱ ተባባሪ በመሆንና የራሱንም ሥም በማስገባት እጣ እንዲወጣለት በማድረጉ፤ 5ኛና 6ኛና ሶፍተዌሩን እንዲያለሙ፣ 7ኛ ተከሳሽ ደግሞ ከቤቶች የተዘጋጀዉን ዳታ እንዲያስተዳድር የተሰጣቸዉን ሃላፊነት ወደጎን በመተዉ እርስ በዕርሳቸዉና ከ8ኛ፣ 9ኛ እና 10ኛ ተከሳሾች ጋር በጥቅም በመመሳጠር ለእጣ ብቁ ያልሆኑ ሰዎችን ብቁ እንደሆኑ በማስመሰልና በእጣዉ ዉስጥ በማካተት አብዛኛዎቹ እጣ እንዲወጣላቸዉ በማድረግ በህዝብና በመንግስት ጥቅም ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስ ያደረጉ በመሆኑ በዋና ወንጀል አድራጊነት በፈፀሙት በስልጣን አለአግባብ መገልገል የሙስና ወንጀል ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡
3ኛ ክስ 5ኛ እና ከ7ኛ እስከ 11ኛ የተጠቀሱት ተከሳሾች ላይ የቀረበ ሲሆን ተከሳሾች ገንዘቡ የወንጀል ፍሬ መሆኑን እያወቁ ወይም ማወቅ ሲገባቸው በስማቸዉ በከፈቱት የባንክ ሂሳባቸዉ ላይ እንዲገባ በማድረግና እርስ በርሳቸዉ በማስተላለፍ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈፀሙት በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብን ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀል ክስ እንደተመሰረተባቸው ከፍትሕ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡
ከ10 ኛ እና 11ኛ ተከሳሽ ውጪ ያሉት ኹሉም (9ኙ) ተከሳሾች ፍ/ቤት ቀርበው ክሱ እንዲደርሳቸው መደረጉም ታውቋል፡፡
አዲስ ማለዳ
15.0K views08:06