2024-03-25 19:48:50
ጥያቄ፡-ሴት ልጃችን ጥፋት ስትሰራና ስትገረፍ ብዙም የመታረም ሁኔታ ስለማታሳይ ከምንገርፋት ይልቅ ከስህተቷ እንድትታረም ሌላ መንገድ መጠቀም ጀመርንና ለውጥ ያየን ይመስለናል፡፡ በምታጠፋ ጊዜ “አልወድሽም” ስትባል ለማስተካከል ትሞክራለች፡፡ ከዚያም እንደምንወዳት ለማረጋገጥ ትጠይቀናለች፡፡ ስትታረም ደግሞ እንደምትወደድ እንነግራታለን፡፡ ይህ ሁኔታ ችግር ይኖረው ይሆን?
መልስ፡-የልጆችን ዲሲፕሊን አስመልክቶ የተለያየ አቋምና ግንዛቤ ያላቸው ቤተሰቦች አሉ፡፡ አንዳንድ ቤተሰቦች ልጆቻቸውን ፈጽመው ዲሲፕሊን ስለማያደርጉ ብልሹ ባህሪ ያላቸውን ልጆች ያሳድጋሉ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ልጆችን ዲሲፕሊን በማድረግ ቢያምኑም የሚያደርጉበት መንገድ ግን ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡
የእናንተ መንገድ ከሁለተኛው የሚመደብ ነው፡፡ ልጃችሁ ስትሳሳት እንደማትወደድ፣ ትክክለኛ ስትሆን ደግሞ እንደምትወደድ ስትነገግሯት ህሊናዋን ለአደገኛ ቀውስ እያሰለጠናችሁት መሆኑን አትዘንጉ፡፡ ይህቺ ልጅ ቀስ በቀስ የመደነቅና ተቀባይነት የማግኘት ሱሰኛ ሆና ነው የምታድገው፡፡ ይህም ማለት ሰዎች እንዲወዷትና እንዲቀበሏት የግድ ሰዎቹን ማስደሰት እንዳለባት የማሰብ ዝንባሌን ይዛ ስለምታድግ የወደፊት ሕይወቷ ሰዎችን በማስደሰት ዙሪያ ይሆናል፡፡
የዚህ ውጤቱ፡-
• ካለማቋረጥ ሰዎች እንደሚወዷትና እንደማይወዷት ለማወቅ የመሞከር ዝንባሌ፣
• ሰዎች እንደማይወዷት ካሰበች ድብርት ውስጥ የመግባት ሁኔታ፣
• ስህተት ስትሰራ ሰዎች እንደሚጠሏት በማሰብ ስህተትን በመፍራት ከእንቅስቃሴ መገታት፣
• ሰዎች እንዲወዷት የመጦዝና ሰዎች እንደልባቸው የሚያደርጓት አይነት ሰው መሆን . . . እና የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡
ልጆችን መቅጣት (ዲሲፐልን ማድረግ) ተገቢ የሆነ ልምምድ ቢሆንም “ቅጣት” እና “ጥቃት” የተለያዩ መሆናቸው ማወቅ አስፈላጊ ነው፡፡ ማንኛውም አካላዊ ጥቃት፣ የስሜት ጥቃት፣ የስነ-ልቦና ጥቃት . . . ከትክክለኛ ዲሲፕሊን ጋር ሊምታታ አይባውም፡፡ ይህ የእናንተ ልምምድ ከስትና ከስነ-ልቦና ጥቃት ዘርፍ የሚመደብ ነው፡፡
ልጃችሁ ብታጠፋም ሆነ ባታጠፋ የእናንተ ፍቅር የማይለዋወጥ መሆኑን ወደማሳወቅ ልምምድ ውስጥ መግባት አስፈላጊ ነው፡፡ ሆኖም ግን ለስህተቷ እርማት፣ ሆን ብላ ለምታጠፋቸው ሁኔታዎች ደግሞ ትክክለኛውን ቅጣት መስጠት አስፈላጊ ነው፡፡ የተለያዩ ልጆች ለተለያየ የቅታት መንገድ ምላሽ ይሰጣሉ፡፡
ለምሳሌ፣ አልታዘዝ ሲሉ፣ ለተወሰነ ጊዜ የሚወዱትን መጫወቻ መከልከል፣ ማየት የሚፈልጉትን የቴሌቭዢን ወይም የድህረ-ገጽ ፕሮግራም ለተወሰነ ጊዜ መከልከል፣ ማግኘት የሚፈልጉትን ጓደኛ ለተወሰነ ጊዜ እንዳየገኙ ማገድና የመሳሰሉት መንገዶች ከጥቃት በመቆጠብ ህሊናን ለማሰልጠን ይረዳሉ፡፡
https://t.me/Dreyob
https://m.youtube.com/user/naeleyob623
https://www.facebook.com/Dr-Eyob-Mamo-1050816404958639/
13.1K viewsedited 16:48