2024-03-29 05:01:40
የመገፋት መዘዞች(“የመገፋት ሕመም” ከተሰኘው የዶ/ር ኢዮብ ማሞ መጽሐፍ የተቀነጨበ)፡፡
የመገፋት ስሜት ሰለባ መሆን በሰዎች ሕይወት ውስጥ ይህ ነው የማይባል መዘዝ ያስከትላል፡፡ በማንኛውም ማሕበራዊ ግንኙነትህ ውስጥ ለአንተና ለሌላው ሰው ግር የሚል ባህሪይን የምታንጸባርቅ ከሆነና ከሰዎች ጋር ያለህ ግንኙነት ጎርበጥባጣ ከሆነ ሌሎች የራስ-በራስ ምርመራ ከማድረግህ በፊት ከመገፋት አንጻር ያለህበትን ወቅታዊ ሁኔታ መመልከት ይበጃል፡፡
የመገፋት ስሜት በርካታ አሉታዊ ውጤቶች የሚኖሩት ሲሆን፣ ከሚያስከትላቸው መዘዞች መካከል ፈጥኖና ጎልቶ የሚታየው፣ የመነጠልና የብቸኝነት ስሜት ነው፡፡ ሰዎች እንደተገፉ ሲሰማቸው የመገለልና የብቸኝነት ጫና በስሜታቸው ላይ ይከመራል፡፡ የመገፋት መዘዝ ግን በብቸኝነት ስሜት ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ ከዚህ በታች በተጠቀሱት ነጥቦች እንደምንመለከተው መፍትሄ ያልተገኘለት የመገፋት ስሜት በርካታ ጣጣዎችን ይዞ ነው የሚመጣው፡፡
1. መገፋት ተመላላሽ ሕመምን ይሰጠናልቀደም ብለን እንደተመለከትነው አንጎላችን ለአጥንት ስብራት የሚመጣን የሕመም ስሜትና በመገፋት የሚመጣን የሕመም ስሜት እኩል ነው የሚያስተናግደው፡፡ ሆኖም፣ የመገፋት ስቃይ ከአካል ሕመም ስቃይ የሚለየው ወይም የሚብሰው በማንኛውም ጊዜ ትውስታው እንደገና የሕመሙን ስሜት ስለሚቀሰቅሰው ነው፡፡ ለምሳሌ፣ የዛሬ አስር አመት አጥንትን ሰብሮ የነበረ ሰው ያንን ደርሶበት የነበረውን ሁኔታ መለስ ብሎ ሲያስበው የአጥንት ሕመሙ ተመልሶ አያሰቃየውም፡፡ በተቃራኒው ግን የዛሬ አስር አመት የከባድ መገፋትና መገለል ሰለባ የነበረ ሰው እንደገና ሁኔታውን ሲያስታውሰው ይህ ነው የማይባል ስቃይ ሊመለስበት ይችላል፡፡
2. መገፋት ማሕበራዊ ቀውስ ውስጥ ይጨምረናል አንድ ሰው በሚገፋበት ወይም በሚገለልበት ጊዜ ቀድሞ የነበረውን ማሕበራዊ ትስስር ያጣል፡፡ ይህ ከመገፋት የሚመጣ የመነጠል ስሜት ቀድሞ የነበረንን የመደላደል ስሜት ስለሚነጥቀን ያለን ማሕበራዊ ሕይወት ይናጋል፡፡ ከተደላለደ ማሕበራዊ ሕይወትና ግንኙነት ውጪ ሙሉ ሊሆን የማይችለው ማንነታችን ያንን ፍለጋ የሚያሳልፈው ጊዜና የሚያቃጥለው የስሜት ኃይል ይህ ነው አይባልም፡፡ በነበረን መገፋት የተሰማንን ሕመም ለማካካስና ሁኔታውን “ለመበቀል” በሌላ በሚገባ ወዳልታሰበበት ማሕበራዊ ሁኔታ ውስጥ ራሳችንን እናገኘዋለን፡፡ ከዚያም፣ ሌላ የመገፋት ዑደቱ ይቀጥላል፡፡
3. መገፋት የስሜት መዛባት ያስከትላል መገፋት ቁጣ፣ ጠብ-ጫሪነትና የመሳሰሉት አይነት ለማሕበራዊ ግንኙነት ጸር የሆኑ ስሜቶችን እንድናዳብር ያጋልጠናል፡፡ በአንዳንድ ጥናቶች እንደተጠቆመው የእጽ ሱሰኝነት፣ ድህነት፣ እንዲሁም የወንበዴዎች ቡድን (Gang) አባልነት ከሚያስከትለው መዘዝ ይልቅ የመገፋት ቀውስ የሚያስከትለው መዘዝ ይልቃል፡፡ የተገፉ ወይም እንደተገፉ የተሰማቸው ሰዎች ሁኔታው ሲብስባቸው የጸበኝነትና የወንጀለኛነት ባህሪይ ይታይባቸዋል፡፡
4. መገፋት በራስ መተማመናችንን ይነካዋልየመገፋትና የመገለል ሰለባ የሆኑ ሰዎች በራሳቸው ላይ ያላቸውን አመለካከት የመጣል ዝንባሌ ውስጥ ይገባሉ፡፡ አንድ አንድ ጊዜ የመገፋቱ ሁኔታ የተከሰተው ከእነሱ ስህተት ውጪ ሆኖ እንኳን ሁኔታውን ግን የሚያገናኙት ከራሳቸው ጋር ነው፡፡ ስለዚህም፣ “ሰዎች የገፉኝ እንደዚህ ስለሆንኩኝ ነው” ወደሚል ድምዳሜ ውስጥ ይገባሉ፡፡ ራስን መውቀስ፣ መገፋት በተሰማቸው መስክ አንጻር ለወደፊቱ ድፍረትን ማጣት፣ ራስን ማግለልና የመሳሰሉት የወረደ በራስ የመተማመን መገለጫዎች የዚህ ምልክቶች ናቸው፡፡
5. መገፋት የእውቀት ማእከላችንን ይነካዋልበአንዳንድ ጥናቶች እንደታየው ሰዎች የቅርብ ጊዜ የመገፋት ልምምዳቸውን እንዲያስታውሱ ሲደረጉና የአእምሮ ብልህነት (IQ) ፈተና ሲሰጣቸው ውጤታቸው ዝቅተኛ ይሆናል፡፡ የመገፋትና የመገለል ሰሜትን የቅርብ ርቀት የማስታወስ ብቃትቸውና የውሳኔ አሰጣጥ ብቃታቸው ላይ ይህ ነው የማይባል ተጽእኖ እንዳለው ይታመናል፡፡
በልጅነትህ በቤተሰብ፣ በወጣትነትህ በአቻዎችህ፣ በጎልማሳነት እድሜህ በፍቅረኛ፣ በአዋቂነት እድሜህ በትዳር አጋር፣ በስራ አለም ውስጥ በአለቃ ወይም በባልደረባዎችህ፣ በሕብረተሰብ ውስጥ በዘርህ ወይም በኢኮኖሚ ደረጃህ . . . የመገፋት ልምምድ ከነበረህ፣ “የመገፋት ህመም” የተሰኘውን መጽሐፍ በማንበብ ከተጽእኖው ነጻ የመውጣት ጉዞን መጀመር ትችላለህ፡፡
https://t.me/Dreyob
https://m.youtube.com/user/naeleyob623
14.6K views02:01