2024-03-08 04:59:59
ችቦው እንዳይጠፋ!(“ጀምሮ መጨረስ” ከተሰኘው የዶ/ር ኢዮብ መጽሐፍ የተወሰደ)
“በፍጥነት የሚጀምሩ ብዙዎች፣ በብቃት የሚጨርሱ ግን ጥቂቶች ናቸው” - Gary Ryan Blair
የጥንት ግሪክ የኦሎምፒክ ሯጮች “ላምፓዲድሮሚያ” (lampadedromia) በመባል በሚታወቅ የቅብብሎሽ ሩጫ ይወዳደሩ ነበር፡፡ በዚህ ውድድር ላይ ሯጮቹ አንድን የበራ ችቦ (ፋና) በእጃቸው ይዘው በመሮጥና ከሚቀጥሉት ተረካቢ ሯጮች ጋር በማቀበል የመጨረሻው ተቀባይ የድል መስመሩ ጋር እስከሚደርስ ድረስ ይሮጣል፡፡ በዚህ የችቦ-ቅብብል ሩጫ ላይ ሽልማቱ የሚሰጠው ቀድሞ ለገባው ቡድን አይደለም፡፡ ሽልማቱ የሚሰጠው ችቦው ሳይጠፋበት ቀድሞ ለገባው ቡድን ነው፡፡
የሽልማቱ ዋና መልእክት፡- አንድን ሩጫ መጀመር ብቻ ሳይሆን መቀጠልም አስፈላጊ ነው፣ መቀጠልም ብቻ ሳይሆን መጨረስም አስፈላጊ ነው፣ መጨረስ ብቻ ሳይሆን ችቦው ሳይጠፋ መጨረስ አስፈላጊ ነው፡፡ ስለሆነም፣ አንድ ቡድን ሩጫውን በብቃት ጨረሰ የሚባለው ችቦው ሳይጠፋ ከደረሰ ነው፡፡ አንዳንድ ነገር ጀምረን በብቃት የመጨረሰን ሂደት ከስራውና ከእኛ አንጻር መመልከት ስንጀምር ብቻ የችቦው እውነታ ይገባናል፡
1. ስራው ጀምሮ የመጨረስ ጉዳይ ሲነሳ በመጀመሪያ ወደሃሳባችን የሚመጣው መጠናቀቅ የሚገባው ስራ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በዙሪያችን እንደምናስተውለው አንዳንድ ስራዎች በጥሩ ውይይትና እቅድ ይጀምሩና ሲጠናቀቁ ግን ተዝረክርከው፣ ከታሰበለት ገጽታ ውጪ ሆነውና ዋጋ ቢስ እስከሚሆኑ ድረስ ጊዜያቸው ተራዝሞ ይጠናቀቃሉ፡፡ ይህ ሁኔታ በምንሰራበት መስሪያ ቤት፣ ሰዎችን ቀጥረን በምናሰራው ስራና በሌሎች ዘርፎችም በየጊዜው የምንጋፈጠው ጉዳይ ነው፡፡
ከራሱ ከስራው አንጻር ስንመለከተው፣ አንድን ስራ ጠንክሮ መጨረስ ማለት ስራው ከመጀመሩ በፊት በታቀደለት የጊዜ ገደብና በወጣለት የጥራትና የብቃት ደረጃ ማጠናቀቅ ማለት ነው፡፡ አንድን ስራ ጨረስን ለማለት ያህል መጨረስ ብቻውን በቂ አይደለም፣ ከላይ በተጠቀሰው አውድ አንጻር ስራውን በብቃትና ጠንክሮ መጨረስም ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ይህንን እውነታ አለመገንዘብ ወይም ደግሞ አውቀነው አስፈላጊውን መስዋእትነት ላለመክፈል በማለት የምንሰራቸው ስራዎች ናቸው እንግዲህ
2. እኛ አንዳንድ ሰዎች አንድን ስራ ለመጨረስ ካላቸው ትጋትና ፍላጎት የተነሳ ስለራሳቸው ህልውና ማሰብ እስከሚያቆሙ ድረስ ይደርሳሉ፡፡ ይሰራሉ፣ ይሰራሉ፣ አሁንም ይሰራሉ! በስራ ስለባከነው፣ ስለደከመውና የእረፍትና የጥገና ጊዜ ስለሚያስፈልገው ማንነታቸው ግን ፈጽሞ ትዝ አይላቸውም፡፡ ስለሆነም ስራውን ሲጨርሱ እነሱም አብረው ያልቃሉ፡፡ እንደዚህ አይነት ሰዎች የሚታያቸው ስራቸውና ስራቸው ብቻ ስለሆነ በሂደቱ ውስጥ ስለሚያጡት የግላቸው አስፈላጊ ነገር ትዝም አይላቸው፡፡
አንድን ስራ ጠንክሮ የመጨረስ ሂደት የግልን ጤንነት የሚያጠቃልል ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ጤንነት የአካል፣ የስነ-ልቦና፣ የስሜትና የአእምሮ ገጽታዎች አሉት፡፡ ምንም እንኳን ስራውን በተሳካለት ሁኔታ ጥጉ ድረስ ብንወስደውና ብናጠናቅቀውም በሂደቱ ግን ከተጠቀሱት የማንነት ዘርፎች አንጻር ደክመንና ከጥቅም ውጪ ሆነን ከጨረስነው ይህ ሁኔታ ጠንክሮ የመጨረስን ሃሳብ አይወክልም፡፡ አንድ ስራ በመጠናቀቁ ምክንያት የሚሰጠንን መልካም ፍሬ የምንበላው እኮ በመጀመሪያ እኛ ጤና ስንሆን ነው፡፡
የተጀመረውን የፍቅር ግንኙነት ጥጉ ለማድረስ ያለን ትግል፣ የትምህርቱ ውጤት በስኬታማ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ያለን ጭንቀት የንግዱን አትራፊነት ለማረጋገጥ ያለን እንቅልፍ ማጣት፣ ያሰብነው ስኬት ላይ ለመድረስ ያለን ሩጫ … በሂደቱ ውስጥ እኛነታችንንና ጤንነታችንን ካሳጣን (ችቦውን ካጠፋው) የጀመርነውን ነገር የመጨረሳችን ትርጉሙ በዜሮ ይባዛል፡፡
https://t.me/Dreyob
https://m.youtube.com/user/naeleyob623
https://www.facebook.com/Dr-Eyob-Mamo-1050816404958639/
13.0K views01:59