2023-02-02 12:10:07
ርዕስ
=========
አንድ ህግ ነበረ እኔም ዘንድ ፈገግታ አንተም ዘንድ ደስታ፤
በልጅነት ልሳን ሚያግባባን አንድ ቃል ፌሽታና ጨዋታ።
ዱሩና ገደሉ ሸለቆና ሜዳው ለአንተም ለኔም እኩል፤
ለአባትህ ለአባቴ ለእርሻ ኑሮአቸው ተግቶ እሚያገለግል።
ለእናቴ ችግር ለማጀቷ ሽፋን የአንተ እናት ተጋርዳ፤
የአባቴ ጥንድ በሬ በደስታ ሲሸጡ ለአባትህ መሬት እዳ።
ወንድምህ ሲያገባ ሲሞሸር ለሰርጉ አጀብ ሲል አድባሩ፤
የእናቴ ማጀት ገበና ሊሸፍን ክፍት ነበር በሩ።
እህቴ በምጥ ተይዛ በፅኑ አያትክ ሲጠሩ፤
ቶሎ እንዲያዋልዱ ከላይ ታች ሲሉ ጎረቤት ሰፈሩ፤
ጭንቋን አታብዥቢያት በቶሎ ገላግሊያት እያሉ ማርያምን ሲጠሩ፤
ለሰማይ ከዋክብት አንጋጠን ለእግዜሩ።
ማርያም! ማርያም ስንል በአቧራና በእንባ ፊታችን ር'ሶ፤
ድንገት ብንሰማ የጨቅላ ህፃን ለቅሶ፤
የደስታ ማብሰሪያ የጥይት ድምፅ ያሰማው ተኩሶ፤
አባትህ ነበረ ከኔ አባት ደስታ የሱ ሐሴት ብሶ።
ደሞ አንድ ቀን ለታ "አንፍር" ጥጃችን ከገደል ላይ ወድቆ፤
እኩል ተቀጥተናል በእናቴ ልምጭ በአያትክ ሸምበቆ።
ሐዘን ቢጎበኘን የእህቴ ህይወት አልፎ ጎረቤት ሲያነባ፤
"ልጄ ልጄ" እያለች ገመድ አገልድማ ከጉድጓድ ልትገባ።
ከአፉ የተመለሰች በሐዘኗ ብዛት በምሬት አልቅሳ፤
እናትህ ነበረች ከእናቴ ጋራ ጥቁር ማቅ ለብሳ።
ያ ሁሉ መከራ ያ ሁሉ ደስታ ለአፍታ እየታወሰኝ፤
ዘመን ባሰመረው የብሔር ድንበር ላይ መቆምክ አመመኝ፤
አንተ ከዚያ ማዶ ቆመክ ከድንበሩ እኔን ስታየኝ፤
ከአባቴ አስክሬን ላይ እናቴን ስጣራ ምነው አላገዝከኝ።
ከባለጊዜ ጋር ስምህ ተደምሮ ዛሬ ባይጠራ፤
እጣ ተጥሎበት የኔ ስም ቢሰነድ ከመከራ ጋራ።
ምነው ዝም አለከኝ
ላግዝሽ ሳትለኝ
ከባለተረኞች ከባለጊዜ ጋር ባልላፋ እኩል፤
ቀን ጥሎኝ አልጠፋም አንስቶኝ አልበድል።
ዛሬ ከጎኔ ባትቆምም አይዞሾ ባትለኝ፤
ለአፍታ እንዳዘነጋው መቼም እንደማልወድቅ የጎጥ ገመድ ጥሎኝ
እናም
ቀን አልፎ ሲቀየር ሲፈርደን እግዜሩ፤
እንዳንተዛዘብ ይብቃኝ መሠደዱ ይብቃህ ማባረሩ።
110 viewsAki Man, 09:10