2023-05-26 13:09:19
#መንበረ_ሰላማን_ለምን_እቃወማለሁ?
1) የምእመናኑ መንፈሳዊና ሥጋዊ ጉዳት ማእከል ያደረገ ሳይሆን "የፖለቲካ ክንፍ ሚዛን ማስጠበቅያ ነው" ብየ ስለማምን፡፡
የትግራይ ህዝብ ከደረሰበት ዘርፈ ብዙ ጉዳት የተነሳ መንፈሳዊና ማሕበራዊ ሕይወቱ ተመሰቃቅሏል። የዕለት ጉርስ ያጣና በዚህም ለሞት የሚዳረግ ብዙ ነው። ይህ ህዝብ ከዚህ ሁሉ መከራ ለመታደግ በትግራይ ያሉ የሃይማኖት መሪዎች (በተለይ ክህዝብ ብዛት አንፃር የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን) ሚና የጎላ መሆን ነበረበት። ይሁንና ግን ፖለቲከኞችንና አክቲቪስቶችን እየተከተለ መግለጫ ከማውጣት የዘለለ ለተጎዳው ህዝብ አንዳች ነገር ሲያደርግ አይታይም። ለህዝቡ መንፈሳዊ መረጋጋት ጉባኤያትንና ልዩ ልዩ ስልጠናዎች መዛጋጀት ግን ይህን ያክል እሩቅ ባልሆነበት ነበር።
አንድ አሁናዊ ጉዳይ ብቻ ላንሳ፦
የትግራይ ገበሬዎች መዳበርያ እንደ ሰማይ ርቋቸው እያለ፣ ተፈናቃዮች ለዕለት ጉርስ የለጋሾች እጅ እየጠበቁ "ከዚህ ህዝብ ተገኝተናል፣ ለህዝብ ቁመናል" በሚሉ ሌቦች በልገሳ የተገኘን መዳበርያና ስንዴ በግለሰቦች እጅ ገብቶ ለገበያ ሲቀርብ ብዙ ሰው ሲያስቆጣ፣ ለጋሾች "ተጣርቶ ሌቦች ለሕግ ካልቀረቡና የክትትል መንገዳችን ሳናዘምን እርዳታ አንልክም" የሚል መርዶ ሲያሰሙ፣ የዓለም አጀንዳ ሲሆን፣ ጊዜአዊ አስተዳደሩ አጣሪ ኮሚቴ ሲያዋቅር "መንበረ ሰላማ" በአሁኑ መግለጫው ይህችን መንካት ሳይፈልግ የግለሰቦች "ለሰርግና ለተስካር የሚታወጡት ወጪ ያሳስበኛል" ብሏል። ለምን? ከህዝብ ይልቅ ለፖለቲካ ይጠነቀቃልላ! እንዲያ ብሎ መግለጫ ቢያወጣ የፖለቲካ ነጥብ ይጥላል ብሎ የሚሳሳለት አካል አለ ማለት ነው።
2) እቅበተ እምነት የረሳ በመሆኑ።
አሁን በትግራይ ብዙ ወጣት ከኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እየወጣ ወደ ሌሎች እምነቶች እየፈለሰና ኢ-አማኝ እየሆነ ነው። ምክንያቶቹ ብዙዎች ሊሆኑ ቢችሉም በትግራይ ያሉ አባቶች ግን ከሃይማኖት ስለሚወጡት ወጣቶች ሲገዳቸው አይታይም። እነሱ ይቅር ከመባባል እንዴት እንደሚሸሹ ሲያስቡ መሽቶ ይነጋባቸዋል። በተለያዩ ሚድያዎች የቤተ ክርስቲያ አስተምህሮ የሚያንቋሽሹ ዝግጅቶች በስፋት ሲቀርቡ "ከቤተ ክርስቲያን የወጡ ናቸው" ከሚል እውር መግለጫ የዘለለ ስለ ተነገረው አስተምህሮና ስለሚድያዎቹ ምንም ላለማለት ቃል የገቡ ይመስላሉ። "አቡነ ሰላማና ፱ቱ ቅዱሳን የድህነታችንና የድንቁርናችን ምክንያት ናቸው" የሚሉ አካላት እየተንከባከቡ በየቀኑ "መንበረ ሰላማ ወደፊት" ይሉናል።
3) አብዝተው የሚጮኹለት ትግራይን ለመገንጠል በሙሉ ኃይላቸው በሚሠሩ ሃይማኖት የለሽ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች በመሆኑ።
መንበረ ሰላማን ወደዚህ ጫፍ እንዲደርስ ከኋላ ሆነው አለንልህ የሚሉት በብዛት ሃይማኖት የሌላቸው ለትግራይ መገንጠል አብዝተው የሚሠሩ ፖለቲከኛችና አክቲቪስቶች ናቸው። በርግጥ በደረሰው ከፍተኛ ጉዳት ተበሳጭቶና አከሃሄዱ ልክ መስሎት የሚደግፍ ምእመን የለም ማለት ግን አይደለም። ከእነዚህ በተጨማሪ ተሃድሶ ፕሮቴስታንትና ፕሮቴስታንቶች ጮቤ ይረግጣሉ። ለምን?
4) የምእመናን ልብ የሚከፋፍል ስለሆነ።
አከሃሄዱ የብዙ ምእመናንን ልቡና የሚከፋፍልና ከመንፈሳዊነት ይልቅ የ"የእኔነት" ስሜት የምያጎላ ነው። ይቅርና አገለግለዋለሁ የሚትለው ምእመንና በሌላ ቦታ (ክልልና ሀገር) ያለ በእንቅስቃሴህ የሚረበሽ አማኝ ካለ ስለ ምእመኑ ተብሎ ከችኮለና ከእልኸኝነት ወጥቶ ስክነትና እርጋታ ይጠይቅ ነበር። የመንበረ ሰላማ ችኩልነትና ግብታዊነት ግን ልቡናው የተከፋፈለብት ምእመን ይበልጥ የሚጎዳና ሃይማኖታዊ ረቡ ከዜሮ በታች የሆነ ነው።
5) መንበረ ሰላማ ራሱ ገፊ ምክንያቶቼ ከሚላቸው ንጹሕ ባለመሆኑ።
መንበረ ሰላማ ለመመስራት ገፊ ምክንያቶች ሆኖውብና ከሚባሉት መካከል
የኢ/ኦ/ተ ቤተ ክርስቲያን ጦርነቱ ደግፋለች
በትግራይ ለደረሰው የካህናት፣ የምእመናን፣ የአብያተ ክርስቲያናትና ንዋየ ቅድሳት ሞት፣ ስደት፣ ውድመት፣ ስርቆት ወዘተ ሲኖዶሱ አላወገዘም
ከቅዱስ ሲኖዶስ አባላት መካከል ብዙዎች መልካም ያልሆኑ ንግግሮችና ድርጊቶች ሲፈፅሙ ሲኖዶሱ ምንም አላላቸውም ወዘተ የሚሉ ናቸው።
እነዚህ ሁሉ ልክ ናቸውኳ ብንል በመንበረ ሰላማ ያሉ ብፁአን አባቶችና ሊቃውንት "ቤተ ክህነት መሰረትን" ከማለታቸው በፊት እንደ ግል፤ ቤተ ክህነት ከመሰረቱ በኋላ ደግሞ እንደ ተቋም እላይ ከተዘረዘሩት ክሶች ራሳቸውን ንጹሐን ማድረግ አይችሉም - በፍፁም (መዘርዘሩ አሰልች ስለሆነና ጥቅሙ እምብዛም ስለሆነ ልተወው - ለሚጠይቀኝ ግን እቀጥላለሁ)።
በብጹእ አቡነ መርሐና በሌሎች አካላት ተደጋግሞ የሚነሳ አንድ ጉዳይ ብቻ አንስቸ ልለፍ። አንድ ሊቀ ጳጳስ "ከህወሓት ይልቅ ሠይጣን ቢገዛን ይሻለናል" ማለታቸው ይታወሳል። ንጽጽራዊ ንግግሩ አይደለም ከሊቀ ጳጳስ ከሌላ ሰውም ባንሰማው ደስ ይለናል። ይህ ንግግር ግን ከዓውዱ አውጥቶ ከሃይማኖትና አምልኮ ጋር ማያያዝ ነገሩን "ከፍየልዋ በላይ . . ." ያደርገዋል። አቡነ መርሐ በዚህ ንግግር ይህን ያህል የተከፉት ህወሓት በአንድ ሊቀ ጳጳስ በዚህ ልክ በመጠላቷ ነው ወይስ በህወሓት ውስጥ አምልኮ አለ? "ከህወሓት ይልቅ የሠይጣን አገዛዝ ይሻለናል" ማለት ነው የሚከፋው ወይስ "ህወሓት ተነካች" ብሎ ለያዥ ለገናዥ ማስቸገር? በሁለቱ መሃል የፖለቲካ ዝንባሌ ልዩነት የለም - ያውና አንድ ናቸው። ሌላውም እንዲሁ ነው።
6) የሐዋርያት አሠረ ክህነት (Apostolic succession) የሚበጥስ ኢ-ቀኖናዊ በመሆኑ።
በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሥልጣነ ክህነት በቅብብሎሽ የሚወርድ እንጂ እንደፈለግክ እየጀመርክና እየቀጠልክ የሚትሄድበት አይደለም። ለዚህም አሁን ያለን ሲኖዶሳዊ አስተዳደር ከመንበረ ማርቆስ ለማምጣት የተከፈለው ዋጋና ዋጋ የከፈሉት እነ አቡነ ዮሐንስ ቀዳማዊ ምስክሮቻችን ናቸው። በፖለቲካዊ ጉዳዮች ተኮራርፈህ "የራስህ ጉዳይ" የሚባል ቢሆን ከእኛ ይልቅ ለእነ አቡነ ዮሐንስ "ብዙ ገፊ ምክንያቶች ነበሯቸው" ብየ አምናለሁ። የመንበረ ሰላማ አከሃሄድ ግን ይህን ሁሉ ታሳቢ ያላደረገ ግብታዊ ሆና ተሰምቶኛል።
"ፓትርያሪክነ አቡነ ማቲያስ" እያሉ የአቡነ ማቲያስ ይሁንታ ያልተገኘበት ሹመት እንፈፅማለን ማለት ራሱ "የዕቃ ዕቃ" ጨዋታ ይመስላል እንጂ ሃይማኖታዊ ይዘት እንደሌለው ግልፅ ማሳያ ነው። ወይ "አቡነ ማትያስ ፓትርያሪካችን አይደሉም" ማለት አልያም ኤጲስ ቆጶሳት ለመሾም ይሁንታቸው መጠበቅ ግድ ነው። "ለምን እንዲህ ሆነ?" ቢባል የመንበረ ሰላማ መንገድ ጠራጊዎቹ ሃይማኖታዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸው መረዳት እንደ ፖለቲካው ስለሆነ።
Gebreab Hagos
11.5K views10:09