2023-03-18 20:08:40
የቅዳሜ ምሽት መጋቢት 9/2015 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች
1፤ የሕወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ የፓርቲውን ቃል አቀባይና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ጌታቸው ረዳ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት እንዲሆኑ ትናንት በአብላጫ ድምጽ መምረጡን የትግራይ ክልል ቴሌቪዥን ዛሬ ዘግቧል። የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደር የሚያዋቅረው፣ ለዚሁ ዓላማ የተቋቋመውና ጀኔራል ታደሠ ወረደ የሚመሩት ክልል ዓቀፍ ኮሚቴ ነው። ኮሚቴው፣ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ ሁሉን አካታች እንደሚሆን ሲገልጽ የቆየ ሲሆን፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩን ፕሬዝዳንት የሚያቀርበው ግን ሕወሃት እንዲሆን እንደተወሰነ ቀደም ሲል ተገልጧል።
2፤ አዲሱ ጎጎት የጉራጌ አንድነትና ፍትህ ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ ዛሬ በአዲስ አበባ ባደረገው ስብሰባ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላቱን፣ ሊቀመንበሩንና ምክትል ሊቀመንበሩን መምረጡን በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባሰራጨው መረጃ አስታውቋል። የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ 11 የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትን የመረጠ ሲሆን፣ መሐመድ አብራርን የፓርቲው ሊቀመንበር እንዲሁም እስር ላይ የሚገኙትን እንዳለ ንዳን ደሞ ምክትል ሊቀመንበር አድርጎ መምረጡን ገልጧል። ፓርቲው ከሳምንት በፊት ባካሄደው መስራች ጉባኤ፣ 29 ቋሚ አባላት ያሉት ማዕከላዊ ኮሚቴ አቋቁሟል። ፓርቲው፣ ጉራጌ ዞን ራሱን የቻለ ክልል እንዲሆን እንደሚታገል ቀደም ሲል መግለጡ ይታወሳል።
3፤ በሰሜኑ ጦርነት ሳቢያ ከሁለት ዓመት በላይ የተዘጉ የትግራይ ክልል ትምህርት ቤቶችን እንደገና ለማስከፈት ዕቅድ መውጣቱን የተመድ ሕጻናት ድርጅት- ዩኒሴፍ ለቢቢሲ ሬዲዮ ተናግሯል። ድርጅቱ፣ ከክልሉ አስተዳደር ጋር የተያዘው ዕቅድ ትምህርት ቤቶችን በመጭው ሚያዝያ ወር ለመክፈት መሆኑን ገልጧል። በክልሉ በጦርነቱ ሳቢያ 2.3 ሚሊዮን ሕጻናት ከትምህርት ገበታ ውጭ ሆነው እንደሚገኙ ድርጅቱ ጨምሮ ጠቅሷል።
4፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ "የመደመር ትውልድ" የተሰኘውን አዲሱን መጽሃፋቸውን ዛሬ በታላቁ ቤተ መንግሥት በተካሄደ ስነ ሥርዓት ማስመረቃቸውን የመንግሥት ዜና አውታሮች ዘግበዋል። መጽሃፉ በአማርኛ፣ በአፋን ኦሮሞ እና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች እንደተዘጋጀና፣ ክልሎች ከመጽሃፉ ሽያጭ የሚያገኙትን ገቢ ለትውልድ ግንባታና ታሪካዊ ቦታዎችን ለማደስ ያውሉታል መባሉን ዘገባዎቹ ጠቅሰዋል። በመጽሃፉ ምረቃ ስነ ሥርዓት ላይ፣ ዐቢይ፣ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ የክልሎች ርዕሰ መስተዳድሮች፣ የገዥው ብልጽግና ፓርቲ አመራሮችና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል ተብሏል።
5፤ የደቡብ አፍሪካ መንግሥት የአገሪቱን ጦር ሠራዊት ቁልፍ መሠረተ ልማቶችን እንዲጠብቅ በዋና ዋና ከተሞች ሊያሠማራ መሆኑን የአገሪቱ ዜና አውታሮች ዘግበዋል። መንግሥት ሠራዊቱን በከተሞች የሚያሠማራው፣ ተቃዋሚው "የኢኮኖሚ ነጻነት ተፋላሚዎች" ፓርቲ የመንግሥትና የግል ተቋማትን የሚያዘጋ አገር ዓቀፍ የተቃውሞ ሰልፍ በቀጣዩ ሳምንት መጥራቱን ተከትሎ ነው። ፓርቲው የተቃውሞ ሰልፉን የጠራው፣ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎዛ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለውድቀት ዳርገውታል በማለት ፕሬዝዳንቱ ሥልጣን እንዲለቁ ግፊት ለማድረግ ነው። ወጣቱ ጁሌስ ማሌማ የሚመራው የኢኮኖሚ ነጻነት ተፋላሚዎች ፓርቲ፣ በአገሪቱ ፓርላማ በመቀመጫ ብዛት ሦስተኛው ትልቅ ፓርቲ ነው።
6፤ አወዛጋቢውን በብሪታኒያ ጥገኝነት ጠያቂዎችን በሩዋንዳ የማስፈር ፖሊሲን የነደፉት የብሪታንያ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚንስትር ስቴላ ብሬቨርማን ዛሬ ኪጋሊ መግባታቸውን የብሪታንያ ጋዜጦች ዘግበዋል። ብሬቨርማን በሩዋንዳ በሚኖራቸው የሁለት ቀናት ቆይታ፣ ብሪታኒያ "ሕገወጥ" የምትላቸውን ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች በሩዋንዳ ለማስፈር በተደረሰው ስምምነት አተገባበር ዙሪያ ከአገሪቱ ባለሥልጣናት ጋር እንደሚነጋገሩ ተገልጧል። የብሪታንያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ የአገሪቱ መንግሥት በ"ሕገወጥ" መንገድ የሚገቡ ጥገኝነት ጠያቂዎችንና ስደተኞችን በሩዋንዳ ማስፈር ይችላል ሲል በቅርቡ መወሰኑ ይታወሳል።
7፤ የዩክሬን የምግብ እህል ምርት በጥቁር ባሕር ወደቦች በኩል ለዓለም ገበያ እንዲቀርብ ባለፈው ዓመት ሐምሌ ላይ ከሩሲያ ጋር የተደረሰው ስምምነት ዛሬ በድጋሚ ለአራት ወራት መታደሱን የፈረንሳዩ ዜና ወኪል ዘግቧል። ሩሲያና ዩክሬን ስምምነቱን ያደሱት፣ በተመድና በቱርክ አደራዳሪነት ለበርካታ ቀናት ድርድር ከተደረገ በኋላ ነው። ሩሲያ ስምምነቱ ለሁለት ወራት ብቻ እንዲታደስ ከቀናት በፊት ሃሳብ አቅርባ ነበር። ባለፈው ኅዳር ለአራት ወራት የታደሰው ይኼው ስምምነት፣ የቆይታ ጊዜው በዛሬው ዕለት ይጠናቀቅ ነበር። #share
ወሳኝ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ቻናሉን ይቀላቀሉ
@emsmereja
252 views17:08