2023-03-24 20:24:30
ዓርብ ምሽት! መጋቢት 15/2015 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች
1፤ የዓለም ገንዘብ ድርጅት (አይ ኤም ኤፍ) ኢትዮጵያ ላቀረበችው የገንዘብ ድጋፍ በጎ ምላሽ ለመስጠትየቴክኒክ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን የድርጅቱ ቃል አቀባይ ጆሊ ኮዛክ ዛሬ ዋሽንግተን ውስጥ ለውጭ ዜና ምንጮች ጋዜጠኞች መናገራቸውን ቪኦኤ ዘግቧል። ድርጅቱ የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት ያስቆመው የሰላም ስምምነት መፈረሙን ተከትሎ፣ በአገሪቱ መንግሥት የኢኮኖሚ ተሃድሶ ዕቅድ ዙሪያ ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ውይይት እየተደረገ ስለመሆኑ ቃል አቀባይዋ መናገራቸውን ዘገባው ጠቅሷል። የሰላም ስምምነቱ ከአገሪቱ መንግሥት ጋር በቅርበት እንዲሰራ መልካም ዕድሎችን እንደፈጠረለት ድርጅቱ ጨምሮ ገልጧል ተብሏል።
2፥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ በትግራይ የሚገኙ ጳጳሳት መጋቢት 13 ቀን "መንበረ ሰላማ የትግራይ ጠቅላይ ቤተክህነት" የተባለ "ሕገወጥ ክልላዊ መዋቅር" መፍጠራቸው፣ የቤተክርስቲያኗን "ተቋማዊ አንድነትና ነባር መዋቅራዊ አደረጃጀት" የሚንድ መሆኑን ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ለአሕጉረ ስብከቶች ሊቀ ጳጳስ መሾም የሚችለው የሲኖዶሱ ምልዓተ ጉባኤ መሆኑን የጠቀሰው መግለጫው፣ አዲስ የትግራይ ሊቃነ ጳጳሳት በውጭ አገራት የቤተክርስቲያኗ አሕጉረ ስብከቶች ራሳቸውን በራሳቸው መመደባቸው የቤተክርስቲያኗን "ቀኖናዊና አስተዳደራዊ አሠራር" ይጥሳል ብሏል። ቤተክርስቲያኗ የጦርነቱ ደጋፊ እንደነበረች የሚያስመስሉ መግለጫዎች ተቀባይነት እንደሌላቸው የገለጸው ሲኖዶሱ፣ በትግራይ የሚገኙ የአሕጉረ ስብከቶችን በጀት ከቆመበት ጀምሮ እንደሚልክ ገልጧል። ሲኖዶሱ፣ ሁሉንም ችግሮች ለመፍታት ለመጋቢት 21 ለጠራሁት ምልዓተ ጉባኤ በክልሉ ያሉ አባቶች ይገኙ ሲል ጥሪ አድርጓል።
3፤ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ የክልሉን "ሕገመንታዊ ግዛቶች ማስመለስ" የአስተዳደራቸው ተቀዳሚ ተግባር እንደሚሆን ዛሬ በሰጡት የመጀመሪያ መግለጫቸው መናገራቸውን የክልሉ ቴሌቪዥን ዘግቧል። ጌታቸው ምዕራብ ትግራይ፣ ደቡባዊ ትግራይ እና ጸለምት አካባቢዎች በኃይል ተይዘው እንደሚገኙና አሁንም የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደሚፈጸሙባቸው መግለጻቸውን ዘገባው ጠቅሷል። ጊዜያዊ አስተዳደሩ የክልሉን የጦርነት ተፈናቃዮች ወደቀያቸው ለመመለስ በትኩረት እንደሚሠራም ጌታቸው ተናግረዋል ተብሏል። ጌታቸው የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር የሆኑት፣ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ሕወሃት ባቀረበው ጥቆማ መሠረት የጌታቸውን ሹመት ትናንት ካጸደቁ በኋላ ነበር።
4፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ነገ ከጉራጌ ዞን ተወካዮች ጋር ወልቂጤ ከተማ ውስጥ ሊወያዩ መሆኑን ከምንጮቼ ሰምቻለሁ በማለት "ኢትዮጵያ ኢንሳይደር" ዘግቧል። ዐቢይ ከዞንና ከወረዳ ተወካዮች እንዲሁም ከአዲስ አበባ ከሚውጣጠ የጉራጌ ብሄር ተወካዮች ጋር የሚወያዩት፣ በጉራጌ ዞን የክልልነት አደረጃጀት ጥያቄ ዙሪያ ሳይሆን እንደማይቀር ምንጮች መናገራቸውን ዘገባው ጠቅሷል። ዐቢይ ትናንት በአዲስ አበባ ከጉራጌ ባለሃብቶች ጋር በዞኑ የክልልነት አደረጃጀት ጥያቄ ላይ መወያየታታቸውና የጠቀሰው ዘገባው፣ ዐቢይ በዚሁ ስብሰባ ላይ የጉራጌ ሕዝብ ከሌሎች አጎራባች ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ጋር ባንድ ክልል ቢዋቀር እንደሚሻል መናገራቸውን አመልክቷል። ጉራጌ ዞን የራሱን ክልል ለማቋቋም ቢወስንም፣ ፌደሬሽን ምክር ቤት ግን ከደቡብ ክልል ቀሪ ዞኖች ጋር ወደፊት በሚዋቀረው "ማዕከላዊ ኢትዮጵያ" ክልል ስር እንዲዋቀር ወስኖበታል።
5፤ ኦሮሚያ እና ሱማሌ ክልሎች በተከሰተው ድርቅ ሳቢያ በርካታ ሰዎች በኮሌራ በሽታ መምታቸውን የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መናገሩን ቢቢሲ አማርኛ ዘግቧል። ኮሌራ ወረርሽኙ ባለፈው ነሐሴ ከተከሰተ ወዲህ 48 ሰዎች እንደሞቱና፣ ድርቁ ወረርሽኙን እንዳባባሰው ተቋሙ መናገሩን ዘገባው ጠቅሷል። ወረርሽኙ በኦሮሚያ ክልል በ15 ወረዳዎች እንዲሁም በሱማሌ ክልል በሦስት ወረዳዎች መከሰቱን ተቋሙ መግለጡን የጠቀሰው ዘገባው፣ በኦሮሚያ ክልል ከ1 ሺህ 800 በላይ ሰዎች በበሽታው ተይዘዋል ማለቱን አውስቷል። በበሽታው ሕይወታቸው ካለፉት መካከል፣ 31 ያህሉ ከኦሮሚያ ክልል ናቸው ተብሏል።
6፤ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 53 ብር ከ8704 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 54 ብር ከ9478 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 63 ብር ከ2737 ሳንቲም እና መሸጫው 64 ብር ከ5392 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ58 ብር ከ5841 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ59 ብር ከ7558 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። አንድ የቻይና ዩዋን ደሞ በ7 ብር ከ1385 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ7 ብር ከ2813 ሳንቲም እንደተሸጠ ባንኩ ገልጧል። #ሼርርር ይደረግ
ወሳኝ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ቻናሉን ይቀላቀሉ
@emsmereja
195 views17:24