2023-03-27 21:05:01
ሰኞ ምሽት መጋቢት 18/2015 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች
1፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ነገ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሪፖርት እንደሚያቀርቡና ሪፖርቱን ተከትሎ የምክር ቤቱ አባላት ለሚያቀርቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ እንደሚሰጡ ምክር ቤቱ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል። ለጠቅላይ ሚንስትሩ ጥያቄና ማብራሪያ የሚቀርብላቸው፣ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ እንደሆነ ምክር ቤቱ ገልጧል። ዐቢይ፣ በተያዘው ዓመት ባለፈው ኅዳር ወር በምክር ቤቱ ተገኝተው ለጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ መስጠታቸው ይታወሳል። ዐቢይ፣ ነገ ለምክር ቤቱ አባላት ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጡት፣ ምክር ቤት በ61 ተቃውሞ ሕወሃትን ከአሸባሪነት ፍረጃ በሰረዘ ማግስት ነው።
2፤ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን በብሄራዊ ምክክሩ ለመሳተፍ ፍቃደኛ ያልሆኑ 13 የፖለቲካ ኃይሎችን ለማግባባት ላለፉት 6 ወራት ያደረጋቸው ሙከራዎች እንዳልተሳኩ ዋዜማ ከምንጮቿ ሰምታለች። "ቡድን 13" ተብለው የሚጠሩት እነዚሁ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በአገራዊ ምክክሩ አንሳተፍም ያሉት፣ በምክክር ኮሚሽኑ የፖለቲካ ገለልተኛነት እና በኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች አሿሿም ሂደት ላይ ጥያቄ በማንሳት ነው። ከአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ጋር ለመስራት ፍቃደኛ ካልሆኑ ፓርቲዎች መካከል፣ ኦፌኮ፣ ኦነግ፣ የአፋር ሕዝብ ፓርቲ፣ የሲዳማ ፌደራሊስት ፓርቲ እና ኦብነግ ይገኙበታል። የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትም፣ ፓርቲዎቹ ወደ አገራዊው የምክክሩ ማዕቀፍ እንዲገቡ ጥረት እያደረገ መኾኑን የምክር ቤቱ ሊቀመንበር መብራቱ ዓለሙ ለዋዜማ ተናግረዋል።
3፤ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚንቀሳቀሱ ስምንት ፓርቲዎች ከግንቦት 30 በፊት በክልሉ ምርጫ እንዲካሄድ ለምርጫ ቦርድ ደብዳቤ ማስገባታቸውን የዋዜማ ሪፖርተር ዘግቧል። ጥያቄውን ለቦርዱ ካስገቡት ፓርቲዎች መካከል፣ ገዥው ብልጽግና ፓርቲ ይገኝበታል። ፓርቲዎቹ በክልሉ በ2013ቱ አገር ዓቀፍ ምርጫ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ለክልል ምክር ቤቶች ከተያዙ አብዛኞቹ ምርጫ ክልሎች ሳይካሄድ የቀረው ምርጫ ከዘንድሮው ክረምት መግባት በፊት እንዲካሄድ የጠየቁት፣ የክልሉ የጸጥታ ሁኔታ ተሻሽሏል በማለት ነው። ምርጫ ቦርድ ምርጫ ማድረግ የሚጠበቅበት፣ በ71 የክልል ምክር ቤትና በ6 የየሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ክልሎች ነው።
4፤ የከፍተኛ ትምህርት ምዘናና የፈተናዎች አገልግሎት የዘንድሮው የ12ኛ ክፍል አገር ዓቀፍ መልቀቂያ ፈተና ልክ እንደ ባለፈው ዓመት ሁሉ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ቅጥር ግቢ ውስጥ እንደሚሰጥ ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ማስታወቁን የአገር ውስጥ ዜና አውታሮች ዘግበዋል። ተቋሙ ለዘንድሮው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ምዝገባ ከቀጣዩ ረቡዕ ጀምሮ እስከ ሚያዝያ 15 ድረስ እንደሚካሄድና፣ በጠቅላላው 1 ሚሊዮን ተፈታኞች ይመዘገባሉ የሚል ቅድመ ግምት እንደተያዘ መግለጡን ዘገባዎቹ አመልክተዋል። የዘንድሮው የ12ኛ ክፍል አገር ዓቀፍ ፈተና የሚሰጥበት ጊዜ ግን፣ የተፈታኞች ትክክለኛ ብዛት ከታወቀ በኋላ እንደሚወሰን ተቋሙ ገልጧል ተብሏል።
5፤ ጎረቤት ኬንያ ዛሬ በከፍተኛ ሁከት የታጀቡ ጸረ-መንግሥት የተቃውሞ ሰልፎችን አስተናግዳለች። የተቃውሞ ሰልፉ በተለይ በዋና ከተማዋ ናይሮቢ እና የኦዲንጋ የድጋፍ መሠረት በሆነችው ኪሱሙ ከተሞች በርትቷል። የተወሰኑ ሰልፈኞች ናይሮቢ ውስጥ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው ራይላ ኦዲንጋ ቤተሰብ ንብረት በሆነ አንድ ኩባንያ ላይ ጥቃት የፈጸሙ ሲሆን፣ ሌሎች የተደራጁ ቡድኖች ደሞ በቀድሞው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ቤተሰብ ንብረት በሆነ ኩባንያ ላይ ዝርፊያ እንደፈጸሙ የአገሪቱ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ፖሊስ የሰልፉ መሪ ኦዲንጋ የተሳፈሩባቸውን መኪኖች ጨምሮ፣ በሰልፈኞቹ ላይ አስለቃሽ ጭስ እንደተኮሰ ተገልጧል። ኦዲንጋ በሳምንት ሁለት ጊዜ አገር ዓቀፍ የተቃውሞ ሰልፍ የጠሩት፣ ለአገሪቱ የኑሮ ውድነት መንግሥትን ተጠያቂ በማድረግና የባለፈው ነሐሴ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ተጭበርብሯል በማለት ነው።
6፤ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 53 ብር ከ8752 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 54 ብር ከ9527 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 62 ብር ከ7288 ሳንቲም እና መሸጫው 63 ብር ከ9834 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ57 ብር ከ7542 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ58 ብር ከ9093 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። #ሼርርር በማድረግ ተባበሩን
ወሳኝ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ቻናሉን ይቀላቀሉ
@emsmereja
194 views18:05