2023-03-13 07:43:05
""""የጠዋት ዜናዎች ሰኞ መጋቢት 4/2015 ዓ.ም
1፤ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ትናንት በአዲስ አበባ ጠቅላላ ጉባኤ እንዳላካሂድ ተከልክያለሁ ሲል ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ አስታውቋል። ፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤውን ማካሄድ ያልቻለው፣ ጠቅላላ ጉባኤው የተጠራበት ጋምቤላ ሆቴል ጉባኤውን እንዳናስተናግድ የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ አዞናል በማለቱ እንደሆነ ፓርቲው ገልጧል። ሆኖም ፓርቲው ለጉባኤው ከአዲስ አበባ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ የተጻፈ የፍቃድ ወረቀት ይዞ እንደነበር ተናግሯል።
2፤ መንግሥት ቅዳሜ'ለት በአዲስ አበባ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በሽግግር ፍትህ ፖሊሲ አማራጮች ረቂቅ ሰነድ ላይ ለመወያየት ከጠራው ስብሰባ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሰነዱን ወቅታዊነት መተቸታቸውን ሪፖርተር ዘግቧል። የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዮች ከሽግግር ፍትህ በፊት አገራዊ መግባባትና የግጭቶች መቆም ይቅደም በማለት ተመሳሳይ አቋም ማንጸባረቃቸውን ዘገባው ጠቅሷል። ፓርቲዎቹ የአገሪቱ ሰላምና ጸጥታ የሽግግር ፍትህ ለማስፈን አመቺ አለመሆኑን የጠቀሱ መሆኑን ያመለከተው ዘገባው፣ ፍትህ ሚንስቴር ግን ለፓርቲዎቹ ስጋት ምላሽ የሚሰጡ ተወካዮቹን እንዳልላከ አውስቷል። በስብሰባው ከተሳተፉት ፓርቲዎች መካከል፣ ኢዜማ፣ አብን፣ መኢአድ፣ እናት ፓርቲ እና ኢሕአፓ ይገኙበታል ተብሏል።
3፤ አዲስ አበባ የሚገኘው የአፍሪካ ኅብረት ዋና መስሪያ ቤት በሳይበር ጥቃት እንደተመታ ፎርቹን ዘግቧል። በሳይበር ጥቃቱ ሳቢያ፣ የድርጅቱ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች የድርጅቱን የኮምፒውተር ቴክኖሎጂ ሥርዓት ወዲያውኑ እንደዘጉትና በዚህም ሳቢያ በርካታ ሥራዎች ላንድ ሳምንት እንደተስተጓጎሉ መረዳቱን ዘገባው ጠቅሷል። የሳይበር ጥቃቱ በበርካታ ኮምፒውተሮች ላይ ጉዳት ማድረሱን የጠቀሰው ዜና ምንጩ፣ ድርጅቱ ጥቃቱን ያደረሰውን አካል ለመለየት፣ ምርመራ መጀመሩን አመልክቷል።
4፤ የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ሊቀመንበር ጀኔራል ቡርሃንና ምክትላቸው ጀኔራል ደጋሎ ላንድ ወር የዘለቀውን ቅራኔያቸውን በመፍታት የአገሪቱን ብሄራዊ ጸጥታ በበላይነት የሚቆጣጠር ኮሚቴ ማቋቋማቸውን የአገሪቱ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ኮሚቴው ከመደበኛ ሠራዊቶች፣ ከመንግሥት ተቋማትና የሽግግር ሰነዱን ከፈረሙ ታጣቂ ቡድኖች እንደሚውጣጣ ዘገባዎች አመልክተዋል። ጀኔራል ቡርሃንና ጀኔራል ደጋሎ ቅራኔ ውስጥ የገቡት፣ ጀኔራል ቡርሃን በቅርቡ በተፈረመው የሽግግር የፖለቲካ ሰነድ ውስጥ ተጨማሪ የፖለቲካ ኃይሎች ካልተካተቱ ሥልጣን አላስረክብም በማለታቸውና ጀኔራል ደጋሎ ደሞ የቡርሃንን አቋም በመቃወማቸው ነበር።
5፤ የሱማሊያ መንግሥት ከበድ ያሉ አንቀጾችን የያዘ የጸረ-ሽብር ሕግ አርቅቋል። የጸረ-ሽብር ሕጉ፣ መንግሥት በሕግ የተፈረደባቸው የአሸባሪ ቡድን አባላት ንብረቶችን እንዲሁም ለሌላ ሰው ያስተላለፏቸውን ንብረቶች ጭምር እንዲወርስ ሥልጣን እንደሚሰጥ የአገሪቱ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ረቂቅ ሕጉ የሽብር ክሶች በወታድራዊ ፍርድ ቤት ብቻ እንዲታዩ እንደሚደነግግ ዘገባዎቹ አመልክተዋል። ረቂቅ ሕጉ በፓርላማው የጸደቀ ሲሆን፣ የላይኛው እንደራሴዎች ምክር ቤት እና ፕሬዝዳንቱ ሲያጸድቁት ተግባራዊ ይሆናል ተብሏል።
6፤ የደቡብ አፍሪካ የሙስና ተቆጣጣሪ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ሴሪል ራማፎዛ ከተጠረጠሩበት የሙስና ቅሌት ነጻ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ ማለቱን የአገሪቱ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ራማፎዛ፣ ከገጠር ባድማቸው በዘራፊዎች ከ500 ሺህ ዶላር በላይ ሲዘረፉ ለፖሊስ ያላሳወቁት፣ ገንዘቡን በሙስና ስሏገኙት ሊሆን ይችላል የሚል ክስ ቀርቦባቸው ነበር። ጸረ ሙስና ኮሚሽኑ ግን፣ ፕሬዝዳንት በክስተቱ ሥልጣናቸውን ያላግባብ እንዳልተጠቀሙ ወይም የስነ ምግባር መርሆዎችን እንዳልጣሱ እና ዝርፊያውን በሦስት ሳምንት ውስጥ ለፖሊስ እንዳሳወቁ ገልጧል። የአገሪቱ ፓርላማ ያቋቋመው መርማሪ ኮሚሽን፣ የፕሬዚዳንቱ ድርጊት መልስ ሊሰጡበት የሚገባቸው ነው የሚል ሪፖርት ማውጣቱ ይታወሳል። #ሼርርር
@emsmereja
@emsmereja
10 views04:43