2023-04-11 21:55:15
ማክሰኞ ምሽት! ሚያዝያ 3/2015 ዓ.ም የEMS ዕለታዊ ዜናዎች
1፤ በትግራይ ክልል ሽራሮ ከተማ ከሚገኝ የዓለም ምግብ ድርጅት የዕርዳታ መጋዘን ውስጥ ለ100 ሺህ ተረጅዎች የሚበቃ ሰብዓዊ ዕርዳታ መዘረፉን ድርጅቱ በቅርቡ እንደደረሰበት ከሁለት የረድዔት ድርጅት ሠራተኞች ሰምቻለሁ ሲል አሶሴትድ ፕሬስ ዘግቧል። ዕርዳታውን የለገሰው የአሜሪካው ዓለማቀፍ የተራድዖ ድርጅት መኾኑንና ዕርዳታውን ማን እንደዘረፈው ግን እስካሁን እንዳልታወቀ ምንጮቹ መናገራቸውን ዘገባው አመልክቷል።
ድርጅቱ በትክክል ከየትኛው መጋዘኑ ዕርዳታ እንደተዘረፈ ባይጠቅስም፣ በኢትዮጵያ የድርጅቱ ኃላፊ ክላውድ ጂቢዳር ግን ለድርጅቱ አጋሮች በጻፉት ደብዳቤ በአገር ውስጥ ገበያዎች ከፍተኛ መጠን ያለው ምግብ ለሽያጭ መቅረቡ ድርጅቱን እንዳሳሰበው መግለጣቸውን ዘገባው ጠቅሷል። ኹኔታው በድርጅቱ ስምና ወደፊት የምግብ ዕርዳታ ልገሳ ለማግኘት በሚያደርገው ጥረት ላይ ስጋት እንደሚደቅን ኃላፊው መግለጣቸውንና፣ "ዕርዳታ እንዳይዘረፍና ላልታለመለት ዓላማ እንዳይውል አስቸኳይ ርምጃዎችን መውሰድ መውሰድ እንደሚያስፈልግ" በደብዳቤያቸው መጠቆማቸው በዘገባው ተጠቅሷል። ድርጅቱ በጉዳዩ ላይ ምርመራ እያደረገ ስለመኾኑም በደብዳቤው ላይ ጠቅሷል ተብሏል።
2፤ አብን የአማራ ክልልን ጨምሮ የየትኛውም ክልል ካቢኔ ወይም ምክር ቤት የክልል ልዩ ኃይሎችን መልሶ በማደራጀት ዙሪያ ያደረገው "ውይይትም ኾነ ያሳለፈው ሕጋዊ ውሳኔ" የለም ሲል ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። የፌደራል መንግሥት ባለሥልጣናት የክልል ልዩ ኃይሎች የመልሶ ማደራጀት ማስፈጸሚያ በተባለው ዕቅድ ላይ የተወያዩት መጋቢት 30 ላይ መኾኑን ፓርቲው በአስረጅነት ጠቅሷል። ገዥው ፓርቲ የክልል ልዩ ኃይሎችን መልሶ የማደራጀቱ ውሳኔው በሁሉም ክልሎች በተመሳሳይ ጊዜ የሚተገበር ስለመኾኑ ትናንት ያወጣው መግለጫ "እወነታን የካደ" መኾኑን የገለጠው አብን፣ ከአማራ ክልል ውጪ "በየትኛውም ክልል የልዩ ኃይል አባላትን ትጥቅ የማስፈታት ወይም መልሶ የማደራጀት እንቅስቃሴ አልተደረገም" ብሏል። የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አዛዦችን በድንገት ከሥራ ውጭ በማድረግ፣ የልዩ ኃይሉ "የዕዝ ሰንሰለት እንዲፈርስ" ተደርጓል በማለትም አብን ከሷል። አብን አያይዞም፣ የክልሉና የፌደራል መንግሥታት "የክልሉ ሕዝብ አደባባይ ወጥቶ ያቀረበውን ጥያቄ እንዲያከብሩ" ጠይቋል።
3፤ በአማራ ክልል በባሕርዳር እና ደብረብርሃን ከተሞች በተለያዩ የጸጥታ ኃይሎች መካከል ዛሬ የተኩስ ልውውጥ መደረጉን ከነዋሪዎችና የረድዔት ድርጅት ሠራተኞች መስማቱን ጠቅሶ አሶሴትድ ፕሬስ ዘግቧል። ትናንት ሌሊት ደሞ፣ በደሴ እና ሰቆጣ ከተሞች የጥይት ተኩስ ሲሰማ ማደሩን ከምንጮች መስማቱን ዘገባው አመልክቷል። በክልሉ በርካታ በአካባቢዎች መንገዶች፣ የንግድ መደብሮችና ባንኮችም መዘጋታቸውን ዜና ምንጩ ጨምሮ አመልክቷል።
4፤ ኢሰመጉ መንግሥት የክልል ልዩ ኃይሎችን መልሶ ለማደራጀት ጀመርኩት ያለው እንቅስቃሴ የክልሎችን ነባራዊና ተጨባጭ ኹኔታ ግምት ውስጥ ያስገባና የዜጎችን ደኅንነት አደጋ ላይ የማይጥል መኾኑን እንዲያረጋግጥ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ጠይቋል። መንግሥት የክልሎች ልዩ ኃይሎችን መልሶ የማደራጀት ውሳኔውንና የውሳኔውን አፈጻጸም ለተለያዩ ባለድርሻ አካላትና ባጠቃላይ ለሕዝቡ ግልጽ እንዲያደርግ የጠየቀው ኢሰመጉ፣ የፌደራሉና ክልል መንግሥታት ውሳኔውን በሰላማዊ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በማያስከትልና ዘለቄታዊ መፍትሄ ሊያመጣ በሚችል መንገድ እንዲፈጽሙት ጥሪ አድርጓል። ኢሰመጉ፣ ክልሎች በአንዳንድ አጋጣሚዎች ልዩ ኃይሎቻቸውን በማንቀሳቀስ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሲፈጽሙ እንደተስተዋሉ ኢሰመጉ በመግለጫው አስታውሷል። ኢሰመጉ፣ ሰሞኑን ከመንግሥት ውሳኔ ጋር በተያያዘ በአማራ ክልል በተቀሰቀሱ ተቃውሞዎች መንገዶች እንደተዘጉና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችም እንደተፈጸሙ ጨምሮ አመልክቷል።
5፤ የዓለማቀፉ ቀይ መስቀል ማኅበር የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ቢሮ በአማራ ክልል ለሕይወት አስጊ በኾነ ሕመም ላይ የሚገኙ ታማሚዎችን ከቦታ ቦታ በሚያጓጉዙ አምቡላንሶች እና የጤና ባለሙያዎች ላይ በቅርብ ጊዜያት የተፈጸሙ ጥቃቶች አሳስበውኛል ሲል ዛሬ ከቀትር በኋላ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። የጤና ሠራተኞች፣ አምቡላንሶችና ሆስፒታሎች ዒላማ መኾን እንደሌለባቸው የገለጠው ማኅበሩ፣ የጤና ሠራተኞች፣ አምቡላንሶችና ሆስፒታሎች በማናቸውም ጊዜ ሊከበሩ እና ጥበቃ ሊደረግላቸው የሚገባቸው ናቸው ብሏል።
6፤ በትግራይ ክልል ሽራሮ ከተማ ከሚገኝ የዓለም ምግብ ድርጅት የዕርዳታ መጋዘን ውስጥ ለ100 ሺህ ተረጅዎች የሚበቃ ሰብዓዊ ዕርዳታ መዘረፉን ድርጅቱ በቅርቡ እንደደረሰበት ከሁለት የረድዔት ድርጅት ሠራተኞች ሰምቻለሁ ሲል አሶሴትድ ፕሬስ ዘግቧል። ዕርዳታውን የለገሰው የአሜሪካው ዓለማቀፍ የተራድዖ ድርጅት መኾኑንና ዕርዳታውን ማን እንደዘረፈው ግን እስካሁን እንዳልታወቀ ምንጮቹ መናገራቸውን ዘገባው አመልክቷል።
ድርጅቱ በትክክል ከየትኛው መጋዘኑ ዕርዳታ እንደተዘረፈ ባይጠቅስም፣ በኢትዮጵያ የድርጅቱ ኃላፊ ክላውድ ጂቢዳር ግን ለድርጅቱ አጋሮች በጻፉት ደብዳቤ በአገር ውስጥ ገበያዎች ከፍተኛ መጠን ያለው ምግብ ለሽያጭ መቅረቡ ድርጅቱን እንዳሳሰበው መግለጣቸውን ዘገባው ጠቅሷል። ኹኔታው በድርጅቱ ስምና ወደፊት የምግብ ዕርዳታ ልገሳ ለማግኘት በሚያደርገው ጥረት ላይ ስጋት እንደሚደቅን ኃላፊው መግለጣቸውንና፣ "ዕርዳታ እንዳይዘረፍና ላልታለመለት ዓላማ እንዳይውል አስቸኳይ ርምጃዎችን መውሰድ መውሰድ እንደሚያስፈልግ" በደብዳቤያቸው መጠቆማቸው በዘገባው ተጠቅሷል።
7፤ የጤና ሚንስትር ዶ/ር ሊያ ታደሠ የመሩት የሚንስቴሩ ከፍተኛ ልዐካን ቡድን ዛሬ በመቀሌ ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ባለሥልጣናት ጋር ውይይት ማድረጉን የክልሉ ቴሌቪዥን ዘግቧል። ልዑካን ቡድኑ በትግራዩ ጦርነት በጤና ተቋማት ላይ የደረሰውን ውድመት በማዕከላዊ እና ምሥራቃዊ የክልሉ አካባቢዎች ተዘዋውሮ እንደሚጎበኝ ዘገባው አመልክቷል።
8፤ የተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ዛሬ በጎረቤት ሱማሊያ ጉብኝት በማድረግ ላይ ናቸው። ጉተሬዝ ሞቃዲሾ ውስጥ ከሱማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሞሐመድ ጋር የተወያዩ ሲሆን፣ በውይይቱ ላይም ፕሬዝዳንት ሞሐመድ የተመድ ጸጥታው ምክር ቤት በሱማሊያ ላይ የጣለውን የጦር መሳሪያ ማዕቀብ እንዲያነሳ መጠየቃቸውን የፕሬዝዳንቱ ቤተመንግሥት አስታውቋል። ጉተሬዝ፣ ወደ ደቡባዊ ምዕራብ ፌደራል ግዛት ዋና ከተማ ባይድዋ አቅንተው በአገሪቱ ለ5 ተከታታይ የዝናብ ወቅቶች የተከሰተው ከባድ ድርቅ ያስከተለውን ሰብዓዊ ቀውስና በምግብ እጥረት የተጎዱ ሰዎች የተጠለሉበትን ጣቢያ መመልከታቸውን የሱማሊያ ዜና ምንጮች ዘግበዋል።
9፤ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 54 ብር ከ0019 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 55 ብር ከ0819 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 64 ብር ከ0471 ሳንቲም እና መሸጫው 65 ብር ከ3280 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ58 ብር ከ8459 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ60 ብር ከ0228 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። #ሼር በማድረግ ተባበሩን
ወሳኝ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ቻናሉን ይቀላቀሉ
@emsmereja
285 views18:55