Get Mystery Box with random crypto!

ሰኞ ማለዳ! ሚያዝያ 2/2015 ዓ.ም የEMS Mereja ዕለታዊ ዜናዎች 1፤ በአማራ ክልል ፌደራ | Zemedkun Bekele (ዘመዴ)

ሰኞ ማለዳ! ሚያዝያ 2/2015 ዓ.ም የEMS Mereja ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ በአማራ ክልል ፌደራል መንግሥቱ የክልል ልዩ ኃይሎችን መልሶ የማደራጀት ርምጃ መጀመሩን ተከትሎ ትናንት በተለያዩ የክልሉ ከተሞች የተቃውሞ ሰልፎች እንደተካሄዱ EMS ሰምታለች። በቆቦ ከተማ አቅራቢያ ደሞ፣ በጸጥታ ኃይሎች መካከል የተኩስ ልውውጥ እንደተደረገ ከአካባቢው ነዋሪዎች መረዳት ተችሏል። ባንዳንድ አካባቢዎች የክልሉ ልዩ ኃይሎች ከካምፕ እንደወጡና፣ የክልሉ መንግሥትም የልዩ ኃይሉ አባላት በካምፓቸው እንዲቆዩ ከልዩ ኃይሉ አመራሮች ጋር መወያየቱ ታውቋል። በተያያዘ፣ በክልሉ ምክር ቤት የአብን ተወካዮች የክልሉ ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ አስቸኳይ ጉባኤ እንዲቀመጥ በደብዳቤ ጠይቀዋል።

2፤ በአማራ ክልል ጎንደር እና ቆቦ ከተሞች ፌደራል መንግሥት የክልሉን ልዩ ኃይል መልሶ ለማደራጀት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በመቃወም የጥይት ተኩሶችና ተቃውሞዎች እንደነበሩ መስማቱን ጠቅሶ ሮይተርስ ዘግቧል። በጎንደር ከተማ የመንግሥትን ውሳኔ በመቃወም የልዩ ኃይል አባላት ጥይት ወደ ሰማይ ይተኩሱ እንደነበር ምንጮች መናገራቸውን የጠቀሰው ዘገባው፣ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ቢያንስ በስድስት ከተሞች ተቃውሞ እንደተቀሰቀሰ መስማቱን ገልጧል። ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ትናንት ባወጡት መግለጫ፣ የክልል ልዩ ኃይሎችን መልሶ የማደራጀቱን ተልዕኮ "የሚከፍለውን ዋጋ ከፍለንም ቢኾን" እናሳካዋለን ያሉ ሲሆን፣ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለም የፌደራል መንግሥቱ ያሳለፈው ውሳኔ በተዛባ መንገድ ተተርጉሟል ሲሉ የውሳኔውን አስፈላጊነት ለክልሉ ብዙኀን መገናኛ ተናግረዋል።

3፤ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌት በቀጣዩ ክረምት የሚይዘው የውሃ መጠን ከ22 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ወደ 42 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ከፍ እንደሚል ከምንጮች ሰምቻለሁ ሲል ሪፖርተር አስነብቧል። የግድቡ መካከለኛ ክፍል ከፍታ ባለፈው ዓመት ከነበረበት 600 ሜትር ዘንድሮ ወደ 620 ሜትር እንዲኹም የግራ እና ቀኙ ክፍል ከፍታ 633 ሜትር ይደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ ምንጮች መናገራቸውንም ዘገባው ጠቅሷል። የግድቡን ግንባታ ቀሪ ሥራዎች ለማጠናቀቅ፣ 60 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ገንዘብ ያስፈልጋል ተብሏል።

4፤ እናት ፓርቲ ቅዳሜ የምርጫ ቦርድ ታዛቢዎች በተገኙበት ባካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ ከፍተኛ አመራሮቹን መምረጡን በማኀበራዊ ትስስር ገጹ ባሰራጨው መረጃ አስታውቋል። የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ፣ ዶ/ር ሰይፈሥላሴ አያሌውን የፓርቲው ሊቀመንበር እንዲኹም ጥሩማር አባተን ምክትል ሊቀመንበር አድርጎ መምረጡን ፓርቲው ገልጧል። ፓርቲው፣ የላዕላይ ምክር ቤትና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትንም መርጫለሁ ብሏል።

5፤ የማኅበረሰብ አንቂና የ"ኢትዮ ንቃት" ዩትዩብ ጣቢያ ባለቤት መስከረም አበራ
ትናንት በፌደራል ፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሏን "ኢትዮጵያ ኢንሳይደር" ዘግቧል። ፌደራል ፖሊሶች መስከረምን ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ሦስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ከመሄዳቸው በፊት፣ በመኖሪያ ቤቷ ብርበራ ማካሄዳቸውን ከቤተሰቧ ማረጋገጡን ዘገባው ጠቅሷል። መስከረም ባለፈው ታኅሳስ ለሁለተኛ ጊዜ ታስራ ሁከት በመቀስቀስ ወንጀል ክስ ከተመሠረተባት በኋላ፣ በ50 ሺህ ብር ዋስትና መፈታቷ ይታወሳል። መስከረም በዩትዩብ ጣቢያዋ ካደረገችው ንግግር ጋር በተያያዘ ስትታሠር የትናንቱ ለሦስተኛ ጊዜ ነው። #ሼር በማድረግ ተባበሩን


ወሳኝ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ቻናሉን ይቀላቀሉ

                                   @emsmereja