2023-04-13 22:03:29
ሐሙስ ምሽት! ሚያዝያ 5/2015 ዓ.ም የEMS Mereja ዐበይት ዜናዎች
1፤ በኢትዮጵያ የሕጻናት አድን ድርጅት በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ሳቢያ 2.5 ሚሊዮን ሕጻናት እስካሁንም ከትምህርት ገበታ ውጭ እንደኾኑ ትናንት ባወጣው መግለጫ ገልጣል። ድርጅቱ፣ በትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች በጦርነቱ ውድመት በደረሰባቸው አካባቢዎች ትምህርት ቤቶችን እንደገና አገልግሎት ለማስጀመር የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ጠቅሷል። በተለይ በትግራይ 85 በመቶዎቹ ትምህርት ቤቶች በጦርነቱ "ከባድ" ወይም "ከፊል ጉዳት" እንደደረሰባቸው በጥናት መረጋገጡን የጠቀሰው ድርጅቱ፣ በክልሉ ኹሉም ትምህርት ቤቶች ዛሬም ዝግ ናቸው ብሏል። ባጠቃላይ በመላ አገሪቱ ባሁኑ ወቅት 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሕጻናት ከትምህርት ገበታ ውጭ እንደኾኑ ድርጅቱ ጨምሮ ገልጧል።
2፤ "አቫንቲ ኮምንኬሽን" የተሰኘው የብሪታኒያ የሳተላይት የቴሌኮም ኩባንያ በኢትዮጵያ የቴሌኮም ገበያ ለመሠማራት አቅጃለሁ በማለት መናገሩን እፍሪካ ሪፖርት መጽሄት አስነብቧል። "አቫንቲ" ኢትዮጵያ ውስጥ የቴሌኮም አገልግሎት ፍቃድ እንዲሰጠው ለአገሪቱ መንግሥት ጥያቄ ማቅረቡን የገለጠው ዘገባው፣ የኢንቨስትመንት አጋርነት ለመፍጠር ከኢትዮ ቴሌኮምና ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ኩባንያዎች ጋር ንግግር መጀመሩን የኩባንያው ሥራ አስኪያጅ እንደነገሩት ጠቅሷል። "አቫንቲ" በኢትዮጵያ ውስጥ መሠማራት የፈለገው፣ የአገሪቱን የኢንተርኔት ሽፋን በማስፋፋት መስክ እንደኾነ ዘገባው ገልጧል።
3፤ የኢትዮጵያ ብዙኀን መገናኛ ባለሥልጣን ለኢሳት ቴሌቪዥን "የመጨረሻ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ" መስጠቱን ፋና ብሮድካስት ዘግቧል። ባለሥልጣኑ ማስጠንቀቂያውን የሰጠው፣ ኢሳት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ "ሚዛናዊነት የጎደላቸው፣ በተጨባጭ መረጃ ያልተደገፉ፣ የሕዝቦችን መተማመንና አንድነት ሊሸረሽሩ የሚችሉ" ዘገባዎችን በተደጋጋሚ አቅርቧል በማለት መኾኑን ዘገባው አመልክቷል። ባለሥልጣኑ፣ ኢሳት መጋቢት 6 ቀን የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ወደ ዋና ከተማዋ በብዛት ስለሚገቡ ሰዎች ያደረጉት ንግግር "ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጭና የሰዎችን የመንቀሳቀስ መብት የሚጥስ መኾኑን የፖለቲካ ፓርቲዎች አስታወቁ" የሚል ዜና መስራቱን ለአብነት መጥቀሱን ዘገባው አብራርቷል።
4፤ የግብጽ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ኢትዮጵያ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ውዝግብ ግድቡን ውሃ ለመሙላት "ለጊዜ መግዣነት እየተጠቀመችበት" ትገኛለች በማለት መክሰሷን የግብጹ አሕራም ዘግቧል። ሚንስቴሩ፣ ትናንት በሰጠው መግለጫ፣ ግብጽ የግድቡን ውዝግብ ፖለቲካዊ አድረገዋለች በማለት ኢትዮጵያ የምታሰማውን ወቀሳም ነቅፏል። ኢትዮጵያ ግድቡን በተናጥል መሙላቷን አቁማ፣ በቅድሚያ በግድቡ አስተዳደርና ውሃ አሞላል ዙሪያ አስገዳጅ የሦስትዮሽ ስምምነት ይፈረም የሚለውን የሱዳንና ግብጽ አቋም ኢትዮጵያ እስካሁን አልተቀበለችውም። የኢትዮጵያ መንግሥት የግድቡ አጠቃላይ ግንባታ 90 በመቶ ላይ መድረሱን በቅርቡ የገለጠ ሲሆን፣ በተያዘው ዓመት ክረምት ለአራተኛ ጊዜ የግድቡን ውሃ ሙሌት እንደሚከናወን ይጠበቃል።
5፤ ጋና "አር21" የተሰኘውን አዲስ የወባ በሽታ መከላከያ ክትባት ጥቅም ላይ እንዲውል በማጽደቅ የመጀመሪያዋ አገር መኾኗን ዓለማቀፍ የዜና ምንጮች ዘግበዋል። ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ከ30 ዓመታት እልህ አስጨራሽ ምርምር በኋላ ያገኘው ይኼው ክትባት፣ በወባ በሽታ ለመሞት ከፍተኛ ተጋላጭነት ያላቸውን ከ5 ወር እስከ 3 ዓመት የሚኾኑ ሕጽናትን 77 በመቶ ከበሽታው የመከላከል አቅም እንዳለው ቡርኪናፋሶ ላይ በተደረጉ ሙከራዎች መረጋገጡን ዘገባዎቹ ጠቅሷል። ጋና ክትባቱን ጥቅም ላይ ለማዋል የወሰነችው፣ የዓለም ጤና ድርጅት ክትባቱ ገና ሳያጸድቀው ነው። ድርጅቱ የብሪታኒያ የመድኃኒት ኩባንያ ያመረተው "ጂኤስኬ" የተሰኘ ሌላ የወባ ክትባት ጥቅም ላይ እንዲውል ባለፈው ዓመትያጸደቀ ሲሆን፣ የክትባቱ የመከላከል አቅም ግን 60 በመቶ ብቻ ነው።
6፤ የሱዳን ጦር ሠራዊትና ፈጥኖ ደራሽ ሠራዊት አዲስ ፍጥጫ ውስጥ መግባታቸውን የውጭ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ፍጥጫው የተከሰተው፣ ጀኔራል ሞሐመድ ደጋሎ የሚመሩት ፈጥኖ ደራሽ ሠራዊት በካርቱም ሰሜናዊ አካባቢዎችና ግዛቶች በድንገት መሠማራቱን ተከትሎ ነው። የሱዳን ጦር ሠራዊት፣ የፈጥኖ ደራሽ ሠራዊቱ አዲስ ሥምሪት ከእውቅናውና ከፈጥኖ ደራሹ ሠራዊት የድንበር ጠባቂነት ሃላፊነት ውጭ መኾኑን ገልጦ፣ ድርጊቱ በኹለቱ ሠራዊቶች መካከል ግጭት ሊቀሰቅስ ይችላል ሲል ማስጠንቀቁን ዘገባዎቹ ጠቅሰዋል። ይህንኑ ተከትሎ፣ ብሄራዊው ጦር ሠራዊት በካርቱም ዙሪያ ወታደሮች ማስፈር መጀመሩ ተሰምቷል። ፈጥኖ ደራሽ ሠራዊቱ ሲቪል የሽግግር መንግሥት ከተመሠረተ በኋላ ከአገሪቱ ጦር ሠራዊት ጋር በሚቀላቀልበት ጊዜ ላይ እስካሁን ስምምነት ላይ አልተደረሰም።
7፤ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 54 ብር ከ0117 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 55 ብር ከ0919 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 64 ብር ከ1360 ሳንቲም እና መሸጫው 65 ብር ከ4187 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ58 ብር ከ9106 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ60 ብር ከ0888 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። #ሼር በማድረግ ተባበሩን
ወሳኝ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ቻናሉን ይቀላቀሉ
@emsmereja
254 views19:03