Get Mystery Box with random crypto!

Zemedkun Bekele (ዘመዴ)

የቴሌግራም ቻናል አርማ zemedkun_zemede — Zemedkun Bekele (ዘመዴ) Z
የቴሌግራም ቻናል አርማ zemedkun_zemede — Zemedkun Bekele (ዘመዴ)
የሰርጥ አድራሻ: @zemedkun_zemede
ምድቦች: ብሎጎች
ቋንቋ: አማርኛ
ተመዝጋቢዎች: 1.26K

Ratings & Reviews

3.67

3 reviews

Reviews can be left only by registered users. All reviews are moderated by admins.

5 stars

1

4 stars

0

3 stars

2

2 stars

0

1 stars

0


የቅርብ ጊዜ መልዕክቶች 13

2023-04-04 12:11:56 ልዩ መረጃ
የአማራ ልዩ ሀይል ትጥቅ እንዲፈታ የክልሉ መንግሥት መስማማቱ ታወቀ።
ሰሞኑን በባህርዳር በተደረገው ስብሰባም የአማራ ልዩ ሀይል ትጥቁን እንዲፈታ ተወስኗል።
በአንዳንድ ቦታም መሳሪያ ጥርነፋውም ተጀምሯል። ይሄን ለማስፈፀም በጄኔራል አበባው ታደሰ የሚመራ ግብረሀይል መቋቋሙም ታውቋል። በዚህም የአማራ ልዩ ሀይል ትጥቁን በአንድ ወር ውስጥ ለመከላከያ ሰራዊት አስረክቦ እንዲጨርስ እየተሰራ ነው።
በአንፃሩ ደግሞ በየከተሞች የሚገኙ የአድማ ብተና አባላት የተሻለ ስልጠና ወስደው ከተሞችን የሚጠብቁ ይሆናል ሲሉ፣ምንጮቻችን ገልፀዋል። #ሼር በማድረግ ተባበሩኝ


ወሳኝ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ቻናሉን ይቀላቀሉ

                                   @emsmereja
198 views09:11
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-04-04 07:42:05 ማክሰኞ ማለዳ! መጋቢት 26/2015 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች

1፤ መንግሥት ባቋቋመው ብሄራዊ አስመላሽ ኮሚቴ አማካኝነት በሳዑዲ ዓረቢያ በችግር ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ኢትዮጵያዊያን ፍልሰተኞችን ወደ አገራቸው የመመለሱን መርሃ ግብር ማጠናቀቁን ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር አስታውቋል። ብሄራዊ ኮሚቴው በአንድ ዓመት ውስጥ 131 ሺህ ፍልሰተኞችን ወደ አገራቸው መመለስ መቻሉን ሚንስቴሩ ገልጧል። ፍልሰተኞቹ ወደ አገራቸው የተመለሱት፣ ብሄራዊ ኮሚቴው ከባለፈው ዓመት መጋቢት ጀምሮ በየሳምንቱ ባስተባበራቸው የአውሮፕላን በረራዎች አማካኝነት ነው።

2፤ የቀድሞው የጋምቤላ ክልል ምክትል ፖሊስ ኮሚሽነር ቱት ኮር በወንጀል ተጠርጥረው ፍርድ ቤት መቅረባቸውን ፋና ብሮድካስት ዘግቧል። ቱር ኮር ችሎት የቀረቡት፣ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እና የጋምቤላ ነጻነት ግንባር ታጣቂዎች ባለፈው ዓመት ሰኔ በጋምቤላ ከተማ ላይ ለፈጸሙት የተቀናጀ ጥቃት ለቡድኖቹ መረጃ በመስጠት ንጹሃን ዜጎችን አስገድለዋል ተብለው መኾኑን ዘገባው ጠቅሷል። በተያያዘ፣ የክልሉ መንግሥት ከአማጺው የጋምቤላ ነጻነት ግንባር ጋር የሰላም ስምምነት መጀመሩን "ኢትዮጵያ ኢንሳይደር" ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል። የክልሉ መንግሥት ከአማጺው ቡድን ጋር በደቡብ ሱዳን ጁባ እና አዲስ አበባ ሁለት ጊዜ የሰላም ንግግር አካሂዷል መባሉን ዘገባው ጠቅሷል።

3፤ የአማራ ክልል መንግሥት በተያዘው ዓመት ከቅማንት ብሄረሰብ ታጣቂዎች ጋር ባደረገው የሰላም ስምምነት ከ1 ሺህ በላይ ታጣቂዎች ወደ ሰላማዊ ሕይወት መመለሳቸውን ዴይቸቨለ ዘግቧል። በተለያየ የጎንደር ዞኖች ሲንቀሳቀሱ የቆዩት ታጣቂዎች ወደ መደበኛ ሕይወት የተመለሱት፣ በአገር ሽማግሌዎች አማካኝነት በተቋቋሙ የሰላም ኮሚቴዎችና የሐይማኖት አባቶች ጥረት መኾኑን የክልሉ ሰላምና ደኅንነት ቢሮ መናገሩን ዜና ምንጩ ዘግቧል። ኾኖም የክልሉ መንግሥት በሕግ መጠየቅ ያለባቸውን የቀድሞ ታጣቂዎች በሕግ እንደሚዳኛቸው ቢሮው ማስታወቁን ዘገባው አመልክቷል።

4፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፋደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት እና ምክትል ፕሬዝዳንትን ሹመት ለማጽደቅ ዛሬ ጧት ከሦስት ሰዓት ጀምሮ እንደሚሰበሰብ ትናንት አስታውቋል። ምክር ቤቱ የፌደራል ፍርድ ቤቱን አመራሮች ሹመት የሚያጸድቀው፣ የመልቀቂያ ጥያቄ ያቀረቡትን የፍርድ ቤቱን ፕሬዝዳንት ብርሃነ መስቀል ዋጋሪንና የምክትል ፕሬዝዳንት ተናኘ ጥላሁንን የመልቀቂያ ጥያቄ ከተቀበለ በኋላ እንደሚኾን ይጠበቃል። ምክር ቤቱ በዚሁ ስብሰባው፣ የአንድ አባሉን ያለመከሰስ መብት ለማንሳት ይወስናል። ያለመከሰስ መብታቸው እንዲነሳባቸው የውሳኔ ሃሳብ የሚቀርብባቸው የምክር ቤቱ አባል ማንነት ግን፣ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ እልተገለጠም።

5፤ የሱዳን ወታደራዊ አመራሮች እና ሲቪል የፖለቲካ ኃይሎች ከመጋቢት 23 የተራዘመውን የሲቪል ሽግግር መንግሥት መመስረቻ የስምምነት ሰነድ ፊርማ መጋቢት 28 ለመፈረም እዲስ ቀነ ቀጠሮ መቁረጣቸውን የአገሪቱ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። የአገሪቱ ጦር ሠራዊት እና የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሠራዊት መሪዎች ሁለቱን ጦር ሠራዊቶች ማዋሃድ በሚቻልበት ሁኔታ ዙሪያ እስካሁን ከስምምነት አልደረሱም። በሉዓላዊ ምክር ቤቱ ሊቀመንበርና የሱዳን ብሄራዊ ጦር ዋና አዛዥ ጀኔራል አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን እና በምክትላቸው በፈጥኖ ደራሹ ሠራዊት አዛዥ ጀኔራል ሞሐመድ ደጋሎ መካከል የተፈጠረው ዋናው ልዩነት፣ ፈጥኖ ደራሹ ሠራዊት ከብሄራዊው ጦር ሠራዊት ጋር በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ይዋሃድ? የሚለው እንደኾነ ተገልጧል። #ሼር በማድረግ ተባበሩኝ


ወሳኝ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ቻናሉን ይቀላቀሉ

                                   @emsmereja
204 views04:42
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-04-03 20:26:07 ሰኞ ምሽት! መጋቢት 25/2015 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች

1፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነገ በሚያካሂደው ስብሰባ የአንድ አባሉን ያለመከሰስ መብት እንደሚያነሳ ምክር ቤቱ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባሰራጨው መረጃ አስታውቋል። ምክር ቤቱ ያለመከሰስ መብታቸው እንደሚነሳባቸው የሚጠበቁትን አባሉን ማንነት በስም አልጠቀሰም። ምክር ቤቱ፣ አዲስ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንትና ምክትል ፕሬዝዳንትም እንደሚሾም ገልጧል። የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ብርሃን መስቀል ዋጋሪ እና ምክትላቸው ተናኘ ጥላሁን በቅርቡ ከሃላፊነት ለመልቀቅ ጥያቄ ማቅረባቸውን ሪፖርተር ዘግቦ ነበር።

2፤ መንግሥት ለተያዘው በጀት ዓመት የተጨማሪ በጀት ጥያቄ እስካሁን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አለማቅረቡን ዋዜማ ሰምታለች። አንድ የመንግሥት ባለሥልጣን በተያዘው ዓመት መንግሥት ተጨማሪ በጀት ላያስፈልገው እንደሚችል ለዋዜማ ተናግረዋል። ሌላ ምንጭ ደሞ፣ መንግሥት ተጨማሪ በጀት ያላቀረበው ተጨማሪ በጀት ስላላስፈለገው ሳይሆን ለተጨማሪ የብር ህትመት ላለመጋለጥ ሲል መኾኑን ገልጸዋል። እስካሁን በተለመደው አሠራር፣ ገንዘብ ሚንስቴር በዓመቱ አጋማሽ ላይ የተጨማሪ በጀት ጥያቄ ለምክር ቤቱ ያቀርብ ነበር። ምክር ቤቱ ለተያዘው ዓመት ያጸደቀው የመንግሥት በጀት 786 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ነው። መንግሥት ባለፈው ዓመት አጋማሽ ላይ 122 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት ማጸደቁ ይታወሳል።

3፤ የኢጋድ ዋና ጸሃፊ ወርቅነህ ገበየሁ በጅቡቲ ለኢጋድ ሴክሬታሪያት አዲስ ሕንጻ ግንባታ ትናንት ከጅቡቲ መንግሥት እና ከአንድ የቻይና መንግሥታዊ የኮንስትራክሽን ኩባንያ ጋር የግንባታ ስምምነት መፈራረማቸውን በትዊተር ገጻቸው ባሠፈሩት መልዕክት ገልጸዋል። የኢጋድ አዲሱ ሕንጻ የሚገነባው፣ የጅቡቲ መንግሥት በነጻ በሰጠው 10 ሺህ ስኩዌር ሜትር ቦታ ላይ እንደኾነ ድርጅቱ ገልጧል። በግንባታው የስምምነት ፊርማ ላይ፣ የኢትዮጵያ፣ የጅቡቲ፣ የኬንያ፣ ሱማሊያና ሱዳን አምባሳደሮች መገኘታቸው ተገልጧል።

4፤ ላለፉት 10 ቀናት ሰኞ እና ሐሙስ በጸረ-መንግሥት ተቃውሞ ስትናጥ የሰነበተችው ኬንያ የተቃዋሚ መሪው ራይላ ኦዲንጋ የዚህ ሳምንትን የተቃውሞ ሰልፎች በመሰረዛቸውን ሰላም አግኝታ ውላለች። ኦዲንጋ የተቃውሞ ሰልፉን የሰረዙት፣ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ከኦዲንጋ ጋር ልዩነቶቻቸውን በንግግር ለመፍታት ዝግጁ መኾናቸውን ገልጸው፣ ኦዲንጋ የተቃውሞ ሰልፎቹን እንዲሰርዙ በመጠየቃቸው ነው። ሩቶ ይህንኑ ቃላቸውን በማክበር፣ ኦዱንጋ ያነሷቸውን ጥያቄዎች በፓርላማው አሠራር ለማስተናገድ ይቻል ዘንድ ዛሬ ከፓርላማው አመራሮች ጋር መነጋገራቸውን የአገሪቱ ጋዜጦች ዘግበዋል።

5. አፍሪካ ኅብረት በሱማሊያ ነውጠኛውን አልሸባብ ለመዋጋት የተሠማራው አሚሶም በአፍሪካ ኅብረት የሰላም ሽግግር ተልዕኮ ከተተካ አንደኛ ዓመቱን ደፍኗል። የኅብረቱ ተልዕኮ ሃላፊ ሞሐመድ አል-አሚን ሱፍ የአዲሱን ተልዕኮ አንደኛ ዓመት አስመልክተው ባደረጉት ንግግር፣ ባለፉት ጥቂት ወራት የአልሸባብ እንቅስቃሴ በከፍተኛ ደረጃ ቀንሷል ማለታቸውን የሱማሊያ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። በአዲስ ሃላፊነት የተደራጀው የኅብረቱ የሰላም ሽግግር ተልዕኮ፣ የአገሪቱን ጸጥታ ጥበቃ በቀጣዩ የአውሮፓዊያን ዓመት መጨረሻ ለሱማሊያ ጦር ሠራዊት የማስረከብ እቅድ አለው። የሱማሊያ ጦር ከነሐሴ ጀምሮ በአልሸባብ ላይ መጠነ-ሰፊ ጸረ-ማጥቃት መክፈቱን ተከትሎ፣ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ጅቡቲ ከኅብረቱ ሰላም አስከባሪ ተልዕኮ ማዕቀፍ ውጭ በሱማሊያ ጦር ዕዝ ስር ተጨማሪ ወታደሮችን በቅርቡ ማሠማራታቸው እንደተዘገበ ይታወሳል።

6፤ ዛሬ የአንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ በዓለም ገበያ ወደ 84 ዶላር ከ52 ሳንቲም ማሻቅቡን ሮይተርስ ዘግቧል። "ብሬንት" የተባለው ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋው ባንድ ቀን በ5 ነጥብ 7 በመቶ መጨመሩን ዘገባው ጠቅሷል። የነዳጅ ዋጋ ዛሬ ጭማሪ ያሳየው፣ ሳዑዲ ዓረቢያና ሩሲያን ጨምሮ የተወሰኑ ነዳጅ አምራች አገራት በድንገት ለዓለም ገበያ የሚያቀርቡትን የነዳጅ ምርት በቀን በ1 ሚሊዮን በርሜል ለመቀነስ መወሰናቸውን ተከትሎ ነው። የነዳጅ ዋጋ ጭማሪው፣ በዓለም ዙሪያ የመሠረታዊ ፍጆታ ሸቀጦች ዋጋ ጭማሪ ሊያስከትል ይችላል ተብሎ ተሰግቷል።

7፤ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 53 ብር ከ9189 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 54 ብር ከ9973 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 63 ብር ከ7118 ሳንቲም እና መሸጫው 64 ብር ከ9860 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ58 ብር ከ6260 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ59 ብር ከ7985 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። #ሼር በማድረግ ተባበሩኝ


ወሳኝ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ቻናሉን ይቀላቀሉ

                                   @emsmereja
217 views17:26
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-04-03 07:40:13 ሰኞ ማለዳ! መጋቢት 25/2015 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች

1፤ ከአማራና ደቡብ ክልሎች የተወከሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት አንዳንድ የሁለቱ ክልሎች መንግሥታዊ ተቋማት ሠራተኞች ደመወዝ መክፈል እንደተሳናቸው መናገራቸውን ሪፖርተር ዘግቧል። በደቡብ ክልል አንዳንድ መንግሥታዊ ተቋማት ከሦስት እስከ አራት ወራት ድረስ የሠራተኛ ደመወዝ እንዳልከፈሉ በምክር ቤቱ የክልሉ ተወካዮች መግለጣቸውን ዘገባው ጠቅሷል። በአማራ ክልልም፣ በርካታ ወረዳዎች በበጀት እጥረት በወረዳ መዋቅርነት መቀጠል በማይችሉበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውን ከክልሉ የተወከሉ የምክር ቤት አባላት ተናግረዋል ተብሏል። የምክር ቤቱ አባላት ይህን የተናገሩት፣ ከፌደራል ሥራ አስፈጻሚና ሕግ ተርጓሚ ባለሥልጣናት ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ እንደኾነ ዘገባው ጠቅሷል።

2፤ ጤና ሚንስቴር በኦሮሚያ እና ሱማሌ ክልሎች በ18 ወረዳዎች የኮሌራ ወረርሽኝን እስካሁን ማጥፋት እንዳልተቻለ ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። በሁለቱ ክልሎች በአምስት ወረዳዎች የተከሰተው ወረርሽኝ ግን፣ በቁጥጥር ስር መዋሉን ሚንስቴሩ ገልጧል። ወረርሽኙ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የኮሌራ ክትባት መሰጠቱን የገለጠው ሚንስቴሩ፣ ወረርሽኙን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠርና ወደ አጎራባች አካባቢዎች እንዳይሰራጭ ለመከላከል ከዓለም ጤና ድርጅት 1.2 ሚሊዮን ዶዝ ክትባት ጠይቄያለሁ ብሏል። ከድርቅ ጋር በተያያዘ፣ በአንዳንድ ክልሎች የኩፍኝ ወረርሽኝ እና የወባ በሽታዎች መከሰታቸውን ሚንስቴሩ ገልጧል።

3፤ አንጋፋው የኬንያ ተቃዋሚ መሪ ራይላ ኦዱንጋ በዚህ ሳምንት የጠሯቸውን ሁለት አገር ዓቀፍ ጸረ-መንግሥት የተቃውሞ ሰልፎች መሰረዛቸውን አስታውቀዋል። ኦዲንጋ የተቃውሞ ሰልፎቹን የሰረዙት፣ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ልዩነቶችን በንግግር ለመፍታት ዝግጁ መኾናቸውን ገልጸው፣ የተቃውሞ ሰልፎቹ እንዲቆሙ ትናንት ምሽት ጥሪ ማድረጋቸውን ተከትሎ ነው። ፕሬዝዳንቱ ጥሪውን ያቀረቡት፣ በፓርላማው ውስጥ የመንግሥትና ተቃዋሚው ፓርቲ በልዩነቶቻቸው ዙሪያ ንግግር እንዲጀምሩ ነው። ኾኖም ኦዲንጋ በጥያቄዎቻቸው ዙሪያ አዎንታዊ ውጤት ካላዩ፣ በቀጣዩ ሳምንት የተቃውሞ ሰልፎችን እንቀጥላለን በማለት አስጠንቅቀዋል።

4፤ ደቡብ ሱዳን በምሥራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ቀጠና ጥላ ስር ወታደሮቿን ወደ ምሥራቃዊ ኮንጎ ዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ልካለች። በቀጠናዊው ድርጅት ውሳኔ መሠረት፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ እና ቡሩንዲ ቀደም ሲል ወታደሮቻቸውን የጦርነት ቀጠና በኾነው ምሥራቃዊ ኮንጎ አሠማርተዋል። የቀጠናው ወታደሮች በአገሪቱ ምሥራቃዊ አውራጃዎች የተሠማሩት፣ የኮንጎ መንግሥትን በመውጋት ላይ ያለውን የኤም-23 አማጺ ቡድን ግስጋሴ ለመግታት፣ ለሰላማዊ ሰዎች ጥበቃ ለማድረግና በርካታ አማጺዎችን ትጥቅ ለማስፈታት ነው።

5፤ የሱማሌላንድ መንግሥት አሜሪካና አፍሪካ ኅብረት የግጭት ቀጠና በኾነችው ላስ አኖድ ሰላም እንዲሰፍን ብርቱ ጥረት እንዲያደርጉና የሱማሌላንድን ሉዓላዊነት ለሚያከብር ዘላቂ መፍትሄ ድጋፍ እንዲሰጡ ትናንት ባወጣው መግለጫ ተማጽኗል። ሱማሌላንድ በዚሁ መግለጫዋ፣ ጎረቤት አገራት ያደረጓቸውን ጨምሮ ሁሉም የሰላም ጥረቶች በተዋጊ ሚሊሻዎች እምቢተኝነት ሳቢያ ከሽፈዋል ብላለች። የአልሸባብ ታጣቂዎች፣ የሱማሊያ ጦር ሠራዊትና የፑንትላንድ ራስ ገዝ ታጣቂዎች እየወጓት መኾኑን የጠቀሰችው ሱማሌላንድ፣ ፑንትላንድ ታጣቂዎችን ማስገባቷን እንድታቆም አሜሪካ ግፊት እንድታደርግ መጠየቋን ገልጣለች። #ሼር በማድረግ ተባበሩኝ


ወሳኝ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ቻናሉን ይቀላቀሉ

                                   @emsmereja
239 views04:40
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-04-01 20:58:24
ከጋብቻ በኋላ የጫጉላ ሽርሽር የተለመደ ነው።




#ሼር በማድረግ ተባበሩኝ


ወሳኝ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ቻናሉን ይቀላቀሉ

                                   @emsmereja
277 views17:58
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-03-31 21:00:49
ክሪስ ስማኝማ ልንገርህ
የአፍሪካ መሪዎች ከስልጣን ከወረዱ በኋላ፣ ህዝባቸው ምንም ጥቃት ፈፅሞባቸው አያውቅም። ምክንያቱም፦ ስልጣን የሚለቁት ሲሞቱ ብቻ ነው።

#ሼር በማድረግ ተባበሩኝ


ወሳኝ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ቻናሉን ይቀላቀሉ

                                   @emsmereja
331 views18:00
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-03-31 20:37:02 ዓርብ ምሽት! መጋቢት 22/2015 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች

1፤ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ልዑካን ቡድን አዲስ አበባ ውስጥ ከፌደራል መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር እየተወያየ እንደኾነ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕስ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ መናገራቸውን የክልሉ ቴሌቪዥን ዘግቧል። የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው የመሩት የክልሉ ልዑካን ቡድንና የፌደራል መንግሥቱ ባለሥልጣናት እየተወያዩባቸው ከሚገኙባቸው አጀንዳዎች መካከል ዋነኛው፣ በትግራይ ክልል የመልሶ ማቋቋም እንቅስቃሴ ዙሪያ እንደኾነ ጣቢያው ገልጧል።

2፤ የብሄራዊ መልሶ ማቋቋሚያና ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ተሾመ ቶጋ በትግራይ ክልል የነፍስ ወከፍና የቡድን ጦር መሳሪያዎችን የማስፈታቱ ሂደት መዘግየቱን መናገራቸውን ዴይቸቨለ ዘግቧል። ኮሚሽነር ተሾመ ዛሬ ባሕርዳር ላይ በጉዳዩ ዙሪያ በተካሄደ የምክክር መድረክ ላይ፣ ለሂደቱ መዘግየት ምክንያቶቹ፣ አዲሱ ኮሚሽን በቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መጠመዱና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምስረታ መዘግየቱ መማኾናቸውን መጥቀሳቸውን ዘገባው አመልክቷል። ኾኖም ኮሚሽነር ተሾመ፣ ከአሁን ጀምሮ የነፍስ ወከፍና ቀላል የጦር መሳሪያዎችን ትጥቅ የማስፈታቱ ሥራ በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሠረት ተግባራዊ መኾን ይጀምራል ማለታቸውን ዘገባው ጠቅሷል። በምክክር መድረኩ ላይ የአማራ ክልል ከፍተኛ ባለሥልጣናትና የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ መኮንኖች ተገኝተዋል ተብሏል።

3፤ የመንግሥታዊው የኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎትን በዋና ሥራ አስፈጻሚነት ለስድስት ዓመታት የመሩት ሮባ መገርሳ ከሃላፊነታቸው መነሳታቸውን ካፒታል ጋዜጣ ዘግቧል። በሮባ ምትክ፣ በሪሶ አመሎ የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኾነው እንደተሾሙ ዘገባው አመልክቷል። ተሰናባቹ ሮባ የኩባንያውን ዋና ሥራ አስፈጻሚነት ሃላፊነት ከመረከባቸው በፊት፣ በኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን በምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚነት ለዓመታት ያገለገሉና በዘርፉ የካበተ ልምድ ያላቸው እንደነበሩ ዘገባው ጠቅሷል። በተመሳሳይ፣ የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር የኋላሸት ጀመረ ከሃላፊነት ተነስተው፣ በምትካቸው አብዱልበር ሸምሱ እንደተሾሙ ዜና ምንጩ ዘግቧል።

4፤ በደቡብ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን የኛንጋቶም ወረዳ አስተዳደር የአንድ እምነት ተከታይ ኡጋንዳዊያን ወደ ወረዳው የገቡት "የምጽዓት ቀንን በመሸሽ ነው" መባሉን እንዳስተባበለ ቢቢሲ አማርኛ ዘግቧል። የወረዳው አስተዳደር፣ 277 ኡጋንዳዊያን ወደ ወረዳው ባለፈው ታኅሳስ መግባታቸውን አረጋግጦ፣ ኾኖም ግን ኡጋንዳዊያኑ "በኡጋንዳ ይጀምራል ብለው ያመኑትን የምጽዓት ቀን ሽሽተው የተሰደዱ ናቸው" ተብሎ የተነገረው "የተሳሳተ መረጃ ነው" ማለቱን ዘገባው ጠቅሷል። ኡጋንዳዊኑ ለኛንጋቶም ብሄረሰብ "የቤተክርስቲያን መልዕክት ለማድረስና አካባቢውን ለመጎብኘት" የገቡ የሐይማኖት ተጓዦች እንደኾኑ የጠቀሱት የወረዳው ባለሥልጣናት፣ ኛንጋቶም ብሄረሰብ ከኡጋንዳ የፈለሰ ነው የሚል አፈ ታሪክ መኖሩንም ተናግረዋል ተብሏል። ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር፣ ኡጋንዳዊያኑ "የምጽዓት ቀንን የሸሹ" መኾናቸውን ማረጋገጡን ትናንት ተናግሮ ነበር።

5፤ አሜሪካ የሱማሌላንድ ራስ ገዝ መንግሥት ወታደሮቹን የግጭት ቀጠና ከሆነችው ላስ አኖድ ከተማ እንዲያስወጣ ጠይቃለች። መንግሥትን የሚፋለሙ የላስ አኖድ የጎሳ ሚሊሻዎችም፣ በመንግሥት ኃይሎች ላይ ጥቃት ከማድረስ እንዲቆጠቡ አሜሪካ አሳስባለች። ሁለቱ ወገኖች ግጭቱን አብርደው ቀደም ሲል የተደረሰውን ተኩስ አቁም እንዲያከብሩ የጠየቀችው አሜሪካ፣ ሰብዓዊ ቀውሱ እንዳይባባስ ተፋላሚ ወገኖች በንግግር ግጭቱን መፍታት አለባቸው ብላለች። ባለፈው ኅዳር መካሄድ የነበረበት የሱማሌላንድ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ መዘግየቱ እንዳሳሰባትም አሜሪካ የገለጠች ሲሆን፣ የፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ መንግሥት ምርጫው የሚካሄድበትን የጊዜ መርሃ ግብር እንዲያሳውቅ ጥሪ አድርጋለች።

6፤ የዓለማቀፉ ወንጀል ፍርድ ቤት መመስረቻ ስምምነት ፈራሚዋ ደቡብ አፍሪካ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቱን ለ"ብሪክስ" አገራት የመሪዎች ጉባኤ ሲሄዱ እንደምታስተናግዳቸው ዛሬ በውጭ ጉዳይ ሚንስትሯ ናለዲ ፓንዶር በኩል አስታውቃለች። የዓለማቀፉ ወንጀል ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ፑቲን በዩክሬን "የጦር ወንጀል ፈጽመዋል" በማለት የእስር ማዘዣ ማውጣቱን ተከትሎ፣ በቀጣዩ ነሐሴ የ"ብሪክስ" አገራት የመሪዎች ጉባኤ አዘጋጇ ደቡብ አፍሪካ አቋሟ ምን እንደሚኾን በጉጉት ሲጠበቅ ነበር። ደቡብ አፍሪካና ሩሲያ በሌሎች አገራት ግፊት በድንገት ጠላት ሊኾኑ አይችሉም ያሉት ፓንዶር፣ ፑቲንን በጉባኤው እንዲገኙ እንደተጋበዙ ተናግረዋል። በዓለማቀፉ ፍርድ ቤት ስምምነት መሠረት፣ ደቡብ አፍሪካ ፑቲን ግዛቷን ከተረገጡ አስራ ለፍርድ ቤቱ የማስረከብ ግዴታ አለባት። "ብሪክስ" በፍጥነት በማደግ ላይ ያሉት ኃያላኑ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሩሲያ፣ ቻይና፣ ሕንድና ብራዚል የመሠረቱተ ቡድን ነው።

7፤ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 53 ብር ከ9017 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 54 ብር ከ9808 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 63 ብር ከ5330 ሳንቲም እና መሸጫው 64 ብር ከ8037 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ58 ብር ከ5545 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ59 ብር ከ7256 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። አንድ የቻይና ዩዋን ደሞ በ7 ብር ከ0868 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ7 ብር ከ2285 ሳንቲም ተሽጧል ተብሏል። #ሼር በማድረግ ተባበሩኝ


ወሳኝ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ቻናሉን ይቀላቀሉ

                                   @emsmereja
319 views17:37
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-03-31 07:58:14 ዓርብ ማለዳ! መጋቢት 22/2015 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች

1፤ መንግሥት ክስ የመሠረተባቸውን የሕወሃት ሲቪልና ወታደራዊ አመራሮች ከእስር መፍታቱን ከተከሳሾቹ ጠበቃና ቤተሰቦች ሰምታለች ። ትናንት ከእስር ከተፈቱት መካከል፣ የቀድሞው የትግራይ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳድር አብርሃም ተከስተ፣ አዲስዓለም ባሌማ እና የቀድሞዋ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ኬሪያ ኢብራሂም ይገኙበታል። ከእስር የተፈቱት ተከሳሾች፣ በደብረጺዮን ገ/ሚካዔልና በጀኔራል ታደሠ ወረደ መዝገብ ስር ክስ ተመስርቶባቸው የነበሩ 16 ሲቪልና 20 ወታደራዊ መኮንኖች ናቸው። ተከሳሾቹ የተፈቱት፣ ፍትህ ሚንስቴር በፓርቲው ሲቪልና ወታደራዊ አመራሮች ላይ የከፈተውን ክስ ማቋረጡን ተከትሎ ነው።

2፤ የኤርትራ ወታደሮች ከተቆጣጠራቸው የኢሮብ ወረዳ አካባቢዎች እንዳልወጡ የወረዳዋ ነዋሪዎች መናገራቸውን ጠቅሶ ዶይቸቨለ ዘግቧል። ነዋሪዎቹ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦትና መሠረታዊ አገልግሎቶች እያገኙ እንዳልኾነ መግለጣቸውን ዘገባው ጠቅሷል። በሌላ ዜና፣ መከላከያ ሠራዊት በአማራ ክልል ዋግኽምራ ብሄረሰብ ዞን በሕወሃት ታጣቂዎች ቁጥጥር ስር የቆየችውን አበርገሌ ከተማን መቆጣጠሩ ተገልጧል። የዞኑ ጸግብጂ ወረዳ ግን እስካሁንም በሕወሃት ታጣቂዎች ስር እንደምትገኝ የወረዳው አስተዳደር ኮምንኬሽን ቢሮ መናገሩን ቪኦኤ ዘግቧል።

3፤ በጎረቤት ኬንያ የተቀሰቀሰው ጸረ-መንግሥት የቃውሞ ትናንትም ተባብሶ ቀጥሏል። የተቃዋሚው መሪ ራይላ ኦዲንጋ ለቀጣዩ ሰኞ አራተኛውን አገር ዓቀፍ የተቃውሞ ሰልፍ ጠርተዋል። የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ልዩ ልዑክ ሴናተር ክሪስ ኩንስ ወደ ናይሮቢ አቅንተው ውጥረቱን ለማብረድ ያደረጉት ሙከራ አለመሳካቱን የኬንያ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ኩንስ ተልዕኳቸው የሽምግልና ጥረት ስለመኾኑ በይፋ ባይገልጡም፣ ከአገሪቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ሪጋቲ ጋሻጉዋ እና ከራይላ ኦዲንጋ ጋር መነጋገራቸውን ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ይህንኑ ውይይት ተከትሎ፣ ምክትል ፕሬዝዳንቱ መንግሥት የተቃውሞ ሰልፉን ከሚያስተባብሩት ኦዲንጋ ጋር "በሥልጣን መጋራት" ዙሪያ ንግግር እንደማይኖረው ተናግረዋል ተብሏል።

4፤ አሜሪካ ለሱማሊያ አዲስ አምባሳደር መሾሟን አስታውቃለች። አሜሪካ በአምባሳደር ላሪ አንድሬ ምትክ አዲስ የሾመቻቸው፣ አምባሳደር ሪቻርድ ሪሌይ ናቸው። አሜሪካ አዲስ አምባሳደር የሾመችው፣ የሱማሊያ መንግሥት በአልሸባብ ላይ ሁለተኛውን ዙር አጠቃላይ ጦርነት ለመጀመር እየተዘጋጀ ባለበት ወቅት ላይ ነው። ተሰናባቹ አምባሳደር አንድሬ በሱማሊያ አምባሳደር ኾነው የተሾሙት ባለፈው ዓመት ጥር ወር ሲሆን፣ አምባሳደር አንድሬ በሱማሊያ መንግሥት እና በሱማሊያ ዓለማቀፍ አጋሮች መካከል የሠመረ ግንኙነት እንዲፈጠር ስለማድረጋቸው ይነገርላቸዋል።

5፤ የተመድ ጸጥታው ምክር ቤት በዲሞክራሲያዊት ኮንጎ የሚገኙ ሁሉም አማጺ ኃይሎችባስቸኳይና ለዘለቄታው ትጥቅ እንዲፈቱ አሳስቧል። ምክር ቤቱ፣ በተለይ ኤም-23 የተሰኘው አማጺ ቡድንተጨማሪ አካባቢዎችን እንዳይቆጣጠርና እስካሁን በኃይል የተቆጣጠራቸውን አካባቢዎችም በሙሉ እንዲለቅ ምክር ቤቱ አዟል። ምክር ቤቱ፣ ታጣቂ አማጺዎች ሴቶችን አስገድዶ መድፈርንና ሕጻናትን ለውጊያ መመልመልን ጨምሮ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ይፈጽማሉ በማለት ከሷል። ምክር ቤቱ ይህን ውሳኔ ያሳለፈው፣ የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ አገራት በቀጠናው ማዕቀፍ ስር የአገሪቱን መንግሥት የሚያግዙ ወታደሮችን ወደ ምሥራቅ ኮንጎ መላክ በቀጠሉበት ወቅት ላይ ነው። ኡጋንዳ በቀጠናው ማዕቅፕፍ ስር፣ ከትናንት በስቲያ 5 ሺህ ወታደሮችን ወደ ምሥራቅ ኮንጎ ልካለች። #ሼር በማድረግ ተባበሩኝ


ወሳኝ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ቻናሉን ይቀላቀሉ

                                   @emsmereja
295 views04:58
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-03-30 21:16:15 ሐሙስ ምሽት!መጋቢት 21/2015 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች

1፤ ፍትህ ሚንስቴር በሕወሃት ከፍተኛ የሲቪልና የወታደራዊ መኮንኖች ላይ የመሠረተውን የወንጀል ክስ ማቋረጡን ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ሚንስቴሩ፣ ከሰሜኑ ጦርነት ጋር በተያያዙ ወንጀሎች ዙሪያ ያለው ተጠያቂነት "ዓለማቀፍ ተሞክሮን ታሳቢ ባደረገ መልኩ በሽግግር ፍትህ ማዕቀፍ ሊታይ እንደሚገባ ስምምነት ላይ ተደርሷል" ብሏል። ሚንስቴሩ፣ በሕወሃት ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖችና የሕወሃት ሊቀመንበር ደብረጺዮን ገ/ሚካዔልንና የአሁኑን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳን ጨምሮ በሲቪል የፖለቲካ አመራሮች ላይ የመሠረታቸውን ክሶች ያቋረጠው፣ ፌደራል መንግሥቱና ሕወሃት ፕሪቶሪያ ላይ በደረሱበት ሰላም ስምምነት መሠረት እንደኾነ ጠቅሷል። ሚንስቴሩ ክሶቹን ያቋረጠው፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕወሃትን ከአሸባሪነት መዝገብ በሰረዘ ማግስት ነው።

2፤ የብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን 250 ሺህ የሚደርሱ ተዋጊዎችን ትጥቅ አስፈትቶ መልሶ ለማቋቋም 29 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ወይም 555 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገው መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የውጭ ዲፕሎማቶች ባቀረበው የገንዘብ ልገሳ ጥያቄ መግለጡን ዋዜማ ሰምታለች። ኮሚሽኑ በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ተዋጊዎችንና ታጣቂዎችን ትጥቅ ለማስፈታት፣ ለመበተንና ወደ ኅብረተሰቡ ለመቀላቀል ባዘጋጀው ዝርዝር ሰነድ ዙሪያ፣ ከዲፕሎማቶች ጋር ሰሞኑን መወያየቱን ዋዜማ ተረድታለች። መንግሥት ከ20 እስከ 25 በመቶ የሚሆነውን ወጪ እንደሚሸፍንና፣ ላንድ የቀድሞ ተዋጊ መቋቋሚያ ከ36 ሺህ እስከ 60 ሺህ ብር እንደሚሰጥ በሰነዱ ተገልጧል። በመልሶ ማቋቋሙ፣ የትግራይ፣ አማራ፣ አፋር፣ ኦሮሚያ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላና ደቡብ ክልሎች ታጣቂዎችን ለማካተት የታቀደ ሲሆን፣ በመጀመሪያው ዙር ግን የትግራይ፣ አማራና አፋር ተዋጊዎች ብቻ ይካተታሉ ተብሏል።

3፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው ስብሰባ የብሄራዊ ዲጂታል መታወቂያ ረቂቅ አዋጅን ባንድ ድምጸ ተዓቅቦ አጽድቋል። አዋጁን ለምክር ቤቱ ያቀረበው የሕግና ፍትህ ቋሚ ኮሚቴ፣ ዲጂታል መታወቂያ ሁሉን ዓቀፍ፣ ወጥ እና አስተማማኝ በሆነ ሥርዓት የዜጎችን መረጃ ለመያዝ የሚረዳና በመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ግልጽነትንና ተጠያቂነት ያለበትን አሠራር ለመዘርጋት የሚያስችል መኾኑን ገልጧል። መንግሥት በጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤት ስር የተቋቋመው የዲጂታል መታወቂያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ለወራት የሙከራ ሥራዎችን ሲተገብር መቆየቱ ይታወቃል።

4፤ ኢዜማ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ባለፈው ዓመት መጋቢት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበው ያስሾሟቸው የመገናኛ ብዙኀን ባለሥልጣን ቦርድ አባላት ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ጠይቋል። ኢዜማ፣ የገዥው ፓርቲ አባላት የሆኑ የቦርድ አመራሮች የተሾሙት ከመገናኛ ብዙኀን አዋጅ በተቃራኒ ነው በማለት ተችቷል። ዐቢይ፣ መንግሥታቸው ነጻ መገናኛ ብዙኀንና ነጻ ሃሳብ እንዲኖር ጥረት እያደረገ መኾኑን ሰሞኑን ለምክር ቤቱ መናገራቸውን የጠቀሰው ኢዜማ፣ የሃሳብ የበላይነት ሊሰፍን የሚችለው ግን መንግሥት መገናኛ ብዙኀንን ነጻና ገለልተኛ ማድረግ ሲችል ብቻ ነው ብሏል። ኢዜማ፣ ገዥው ፓርቲ መገናኛ ብዙኀንን በተጽዕኖው ስር በማስገባቱ፣ ሃሳቦቼ የመደመጥ ዕድል ተነፍጓዋል በማለትም አማሯል።

5፤ ኢሰመኮ በፖለቲካ ፓርቲዎች "የመሰብሰብ መብት ላይ የሚጥሏቸው ገደቦች" እና በአባሎቻቸው ላይ የሚደርሱ እንግልቶች" ለዘለቄታው መቆም አለባቸው ሲል ዛሬ ባወጣው መግለጫ አሳስቧል። ኢሰመኮ፣ በእናት ፓርቲ እና በባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የመሰብሰብ መብታቸው እንደተገደበ አረጋግጫለሁ ብሏል። የጎጎት የጉራጌ አንድነትና ፍትህ ፓርቲ ምስረታ አስተባባሪዎችም "እንግልትና እስራት" እንደደረሰባቸው ኢሰመኮ ገልጧል። በፓርቲዎች ላይ የሚፈጸሙባቸው ክልከላዎችና እገዳዎች፣ "የመሰብሰብ፣ የመደራጀትና የመሳተፍ መብቶች ጥሰቶች" እንደኾኑ ኢሰመኮ ጠቅሷል። መንግሥት በፓርቲዎች ላይ "ድንገተኛና ከታሰበላቸው ዓላማ በላይ የኾኑ ርምጃዎችን ከመውሰድ እንዲቆጠብ" እና ይልቁንም ለስብሰባ ተሳታፊዎች ጥበቃና ከለላ የመስጠት ግዴታ እንዳለበት ኢሰመኮ ገልጧል።

6፤ በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን ነቀምቴ ከተማ የገዥው ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ደሳለኝ ቦኮንጆ ማንነታቸው ባያልታወቁ ታጣቂዎች ዛሬ መገደላቸውን የከተማ አስተዳደሩ በፌስቡክ ገጹ አስታውቋል። የከተማ አስተዳደሩ፣ የፓርቲው ሃላፊ ለሥራ ከቤታቸው ሲወጡ በተተኮሰባቸው ጥይት እንደተገደሉ ገልጧል። የኦሮሚያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤትም፣ ግድያውን የፈጸመው "የታጠቀ ኃይል" ነው በማለት በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል። በነቀምቴ ከተማ በመንግሥትና የፓርቲ ሃላፊዎች ላይ ግድያ ሲፈጸም የአሁኑ የመጀመሪያው አይደለም።

7፤ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ከኡጋንዳ የተነሱ ኡጋንዳዊያን የአንድ እምነት ተከታዮች የኢትዮጵያን ድንበር አቋርጠው ደቡብ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን ንያንጋቶም ወረዳ ውስጥ መስፈራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ መለስ ዓለም ዛሬ በሰጡት መግለጫ ማረጋገጣቸውን መግለጫውን የተከታተሉ የአገር ውስጥ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። በመቶዎች የሚቆጠሩ የአንድ እምነት ተከታዮች "የመጨረሻው ምጽዓት" ኡጋንዳ ውስጥ ሊጀምር ተቃርቧል በሚል እምነት ወደ ኢትዮጵያ እንደተሰደዱ ከሳምንታት በፊት የኡጋንዳ ዜና ምንጮች ዘግበው ነበር። መለስ፣ ኡጋንዳዊያኑ ስደተኞች የገቡበትን መንገድ ወይም ብዛታቸውን ይግለጡ አይግለጡ ግን ዜና ምንጮቹ አልጠቀሱም።

8፤ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 53 ብር ከ8978 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 54 ብር ከ9758 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 63 ብር ከ5273 ሳንቲም እና መሸጫው 64 ብር ከ7978 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ58 ብር ከ5007 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ59 ብር ከ6707 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። #ሼር በማድረግ ተባበሩኝ


ወሳኝ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ቻናሉን ይቀላቀሉ

                                   @emsmereja
264 views18:16
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-03-30 21:09:24
ኬሪያ ኢብራሂም፣ ዶ/ር አብርሃም ተከስተ እና ዶ/ር አዲስዓለም ባሌማ ከእስር ተፈቱ!
በዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል እና በጄነራል ታደሰ ወረደ መዝገብ ተከስሰው በእስር ላይ የነበሩ የህወሓት ሲቪል እና ወታደራዊ አመራሮች ዛሬ ሐሙስ መጋቢት 21፤ 2015 አመሻሽ ላይ ከእስር መፈታታቸውን የተከሳሾቹ ጠበቆች አስተባባሪ የሆኑት አቶ አቶ ሃፍቶም ከሰተ ተናገሩ።

በዛሬው ዕለት ከእስር ተለቅቀው ወደ ቤታቸው መግባታቸው ከተረጋገጡ ተከሳሾች ውስጥ፤ የህወሓት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም፣ ዶ/ር አብርሃም ተከስተ እና ዶ/ር አዲስዓለም ባሌማ እንደሚገኙበት ጠበቃው አስታውቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

#ሼር በማድረግ ተባበሩኝ


ወሳኝ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ቻናሉን ይቀላቀሉ

                                   @emsmereja
251 views18:09
ክፈት / አስተያየት ይስጡ