2023-03-28 20:47:10
ማክሰኞ ምሽት! መጋቢት 19/2015 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች
1፤ የዓለም ገንዘብ ድርጅት (አይ ኤም ኤፍ) አንድ የባለሥልጣናት ቡድን ድርጅቱ ለኢትዮጵያ ሊሰጥ ለሚችለው የገንዘብ ድጋፍ የቴክኒክ ዝግጅቶችን ለማድረግ አገሪቱ ውስጥ እንደሚገኝ ሮይተርስ ዘግቧል። መንግሥት ለአገር በቀል የኢኮኖሚ መርሃ ግብሩ ማስፈጸሚያ ድርጅቱ የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርግለት በይፋ ጥያቄ ማቅረቡን የድርጅቱ ቃል አቀባይ መናገራቸውን ዘገባው ጠቅሷል። ድርጅቱ የድጋፍ ጥያቄውን ካጸደቀ፣ ድጋፉ የመንግሥትን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ዕቅድ ለመተግበርና የአገሪቱን ኢኮኖሚ በማረጋጋት ሥራ ለመፍጠር፣ ለሰብዓዊ ዕርዳታና ድህነትን ለመቀነስ ይውላል ሲሉ ቃል አቀባዩ መግለጻቸውን ዜና ምንጩ አመልክቷል። መንግሥት በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍሎች ሰላም ለማስፈን እያደረገ ያለውን ጥረትና ከትግራይ ኃይሎች ጋር የደረሰበት የሰላም ስምምነት አተገባበርን አይ ኤም ኤፍ በአዎንታ ይመለከተዋል መባሉን በዘገባው ላይ ተመልክቷል።
2፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ዛሬ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል። ስለ ሰላም፣ ስለ ክልልነት ጥያቄ፣ ስለ ምጣኔ ሃብት፣ ስለ መፈናቀል እና በሌሎች በርካታ ጉዳዮች ዙሪያ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል። ዐቢይ፣ ከሥልጣን የመልቀቅ ዕቅድ ይኖራቸው እንደኾነ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ሥልጣን መልቀቅ አለመልቀቅ በምርጫ ብቻ የሚወሰን እንደኾነ ምላሽ ሰጥተዋል። ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ መንገደኞች እንዳይገቡ ኦሮሚያ ክልል ላይ ስለሚገጥማቸው ክልከላ ደሞ፣ በከተማዋ ሁከት የመቀስቀስና መንግሥትን በኃይል የመገልበጥ ተልዕኮ ተሰጥቷቸው የሚገቡ አካላት እንዳሉ ዐቢይ ተናግረዋል። ከክልሎች ወደ አዲስ አበባ የሚደረገው ፍልሰት፣ በተያዘው ዓመት ከፍተኛ መሆኑንም ዐቢይ ጠቁመዋል። መንግሥታቸው አገር ለማፍረስ እየሠራ ነው ተብሎ ለበቀረበላቸው ጥያቄም፣ ጉዳዩን እንደ ቀልድ እንደሚወስዱትና የአገር መፍረስና መገነጣጠል አደጋ መቆሙን ገልጸዋል።
3፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ መንግሥታቸው ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ሰላም ለማውረድ እንቅስቃሴ መጀመሩን ዛሬ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ ላይ ተናግረዋል። መንግሥት ለበርካታ ዜጎች ሞትና መፈናቀል ምክንያት የሆነው በክልሉ የሚካሄደው ግጭት እንዲቆም ፍላጎት ያለው መኾኑን ዐቢይ ገልጸዋል። መንግሥት ለግጭቱ ሰላማዊ መፍትሄ ለማፈላለግ ሲል የገዥው ብልጽግና ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር የሚመሩት ኮሚቴ ማቋቋሙን የጠቀሱት ዐቢይ፣ እስካሁን 10 ያህል የሰላም ጥረቶችን እንደተሞከሩ ጠቁመዋል። ኾኖም ቡድኑ ማዕከላዊ አመራር ስለሌለው የሰላም ፍለጋ ሂደቱ መጓተቱን ጠቅላይ ሚንስትሩ ጨምረው ገልጸዋል።
4፤ የቤንሻንጉል ጉሙዝ መንግሥት ወደ ሰላማዊ ኑሮ ለተመለሱ የቀድሞ ታጣቂዎች በኢኮኖሚ ተጠቃሚ የሚያደርጉ አንዳንድ ጥቅማጥቅሞችን ለመስጠት መወሰኑን የክልሉ ብዙኀን መገናኛ ዘግቧል። የክልሉ መንግሥት ያሳለፈው ውሳኔ፣ ትጥቃቸውን የፈቱ የቀድሞ አማጺያን በማዕድን፣ ግብርና እና ንግድ እንዲሠማሩ የሚያስችሉ እንደኾኑ ዜና ምንጩ ጠቅሷል። ይህንኑ ውሳኔ ተግባራዊ ለማድረግም፣ የክልሉ መንግሥት የእርሻ ትራክተሮችን፣ የማዕድን ማውጫ መሳሪያዎችን እና የልማት ሥራ ማስጀመሪያ መነሻ ካፒታል እሰጣለሁ ማለቱን ዘገባው ጨምሮ ገልጧል። ክልሉ ለዚሁ ሥራ ምን ያህል በጀት እንደመደበ ግን ዘገባው አልገለጠም።
5፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በኦሮሚያ ክልል ወሊሶ ከተማ አካባቢ በተካሄደው "በሕገወጥ የቀኖና ቤተክርስቲያን ጥሰት" ተግባር ውስጥ የተሳተፉና "በሕገወጥ ሲመት ኤጲስ ጳጳስነት" የተፈጸመላቸው 17 ግለሰቦች ለቤተክርስቲያኗ ቅዱስ ሲኖዶስ የይቅርታ ደብዳቤ ማስገባታቸውን የቤተክርስቲያኗ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። 17ቱ ግለሰቦች የይቅርታ ደብዳቤያቸውን ያቀረቡት፣ ዛሬ በጠቅላይ ቤተክህነት ጽሕፈት ቤት ከሲኖዶሱ ከፍተኛ ኃላፊዎች ከአቡነ አብርሃም እና ከአቡነ ጴጥሮስ ጋር ከተነጋገሩ በኋላ መኾኑን ዜና ምንጮቹ ጠቅሰዋል። አቡነ አብርሃም እና አቡነ ጴጥሮስም፣ የይቅርታ ደብዳቤውን ለቅዱስ ሲኖዶሱ ለማቅረብ ቃል መግባታቸው ተገልጧል። ቀሪዎቹ ግለሰቦች በቅርብ ቀናት ተመሳሳይ የይቅርታ ደብዳቤ ያስገባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ዜና ምንጮቹ ጨምረው ጠቅሰዋል።
6፤ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ሰሞኑን በኬንያ የተቀሰቀሰእ ጸረ-መንግሥት ሁከት እንዳሳሰባቸው ዛሬ ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል። ፋኪ፣ ሁሉም ወገኖች ሁከትን አስወግደው የአገር አንድነትን መሠረት ባደረገ መልኩ ልዩነቶቻቸውን በንግግር እንዲፈቱ ጥሪ አድርገዋል። ፋኪ በዚሁ መግለጫቸው፣ ባለፈው ነሐሴ በአገሪቱ በተደረገው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ዊሊያም ሩቶ ማሸነፋቸውን የአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያረጋገጠው ሃቅ መሆኑን ጠቅሰዋል። ታዋቂው የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ራይላ ኦዲንጋ ትናንት በጠሩት የተቃውሞ ሰልፍ፣ በተቃዋሚዎች እና ፖሊስ መካከል ግጭትና ከፍተኛ የንብረት ውድመት መድረሱን የአገሪቱ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ከተቃውሞ ሰልፉ ዓላማዎች መካከል፣ መንግሥት የኑሮ ውድነቱን እንዲፈታና ተቃዋሚዎች "ተጭበርብሯል" ለሚሉት ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ፍትህ መጠየቅ ይገኙበታል።
7፤ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 53 ብር ከ8833 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 54 ብር ከ9610 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 63 ብር ከ0933 ሳንቲም እና መሸጫው 64 ብር ከ3552 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ58 ብር ከ0269 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ59 ብር ከ1874 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። #ሼር በማድረግ ተባበሩኝ
ወሳኝ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ቻናሉን ይቀላቀሉ
@emsmereja
121 views17:47