Get Mystery Box with random crypto!

ዓርብ ምሽት! መጋቢት 22/2015 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች 1፤ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር | Zemedkun Bekele (ዘመዴ)

ዓርብ ምሽት! መጋቢት 22/2015 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች

1፤ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ልዑካን ቡድን አዲስ አበባ ውስጥ ከፌደራል መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር እየተወያየ እንደኾነ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕስ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ መናገራቸውን የክልሉ ቴሌቪዥን ዘግቧል። የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው የመሩት የክልሉ ልዑካን ቡድንና የፌደራል መንግሥቱ ባለሥልጣናት እየተወያዩባቸው ከሚገኙባቸው አጀንዳዎች መካከል ዋነኛው፣ በትግራይ ክልል የመልሶ ማቋቋም እንቅስቃሴ ዙሪያ እንደኾነ ጣቢያው ገልጧል።

2፤ የብሄራዊ መልሶ ማቋቋሚያና ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ተሾመ ቶጋ በትግራይ ክልል የነፍስ ወከፍና የቡድን ጦር መሳሪያዎችን የማስፈታቱ ሂደት መዘግየቱን መናገራቸውን ዴይቸቨለ ዘግቧል። ኮሚሽነር ተሾመ ዛሬ ባሕርዳር ላይ በጉዳዩ ዙሪያ በተካሄደ የምክክር መድረክ ላይ፣ ለሂደቱ መዘግየት ምክንያቶቹ፣ አዲሱ ኮሚሽን በቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መጠመዱና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምስረታ መዘግየቱ መማኾናቸውን መጥቀሳቸውን ዘገባው አመልክቷል። ኾኖም ኮሚሽነር ተሾመ፣ ከአሁን ጀምሮ የነፍስ ወከፍና ቀላል የጦር መሳሪያዎችን ትጥቅ የማስፈታቱ ሥራ በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሠረት ተግባራዊ መኾን ይጀምራል ማለታቸውን ዘገባው ጠቅሷል። በምክክር መድረኩ ላይ የአማራ ክልል ከፍተኛ ባለሥልጣናትና የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ መኮንኖች ተገኝተዋል ተብሏል።

3፤ የመንግሥታዊው የኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎትን በዋና ሥራ አስፈጻሚነት ለስድስት ዓመታት የመሩት ሮባ መገርሳ ከሃላፊነታቸው መነሳታቸውን ካፒታል ጋዜጣ ዘግቧል። በሮባ ምትክ፣ በሪሶ አመሎ የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኾነው እንደተሾሙ ዘገባው አመልክቷል። ተሰናባቹ ሮባ የኩባንያውን ዋና ሥራ አስፈጻሚነት ሃላፊነት ከመረከባቸው በፊት፣ በኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን በምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚነት ለዓመታት ያገለገሉና በዘርፉ የካበተ ልምድ ያላቸው እንደነበሩ ዘገባው ጠቅሷል። በተመሳሳይ፣ የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር የኋላሸት ጀመረ ከሃላፊነት ተነስተው፣ በምትካቸው አብዱልበር ሸምሱ እንደተሾሙ ዜና ምንጩ ዘግቧል።

4፤ በደቡብ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን የኛንጋቶም ወረዳ አስተዳደር የአንድ እምነት ተከታይ ኡጋንዳዊያን ወደ ወረዳው የገቡት "የምጽዓት ቀንን በመሸሽ ነው" መባሉን እንዳስተባበለ ቢቢሲ አማርኛ ዘግቧል። የወረዳው አስተዳደር፣ 277 ኡጋንዳዊያን ወደ ወረዳው ባለፈው ታኅሳስ መግባታቸውን አረጋግጦ፣ ኾኖም ግን ኡጋንዳዊያኑ "በኡጋንዳ ይጀምራል ብለው ያመኑትን የምጽዓት ቀን ሽሽተው የተሰደዱ ናቸው" ተብሎ የተነገረው "የተሳሳተ መረጃ ነው" ማለቱን ዘገባው ጠቅሷል። ኡጋንዳዊኑ ለኛንጋቶም ብሄረሰብ "የቤተክርስቲያን መልዕክት ለማድረስና አካባቢውን ለመጎብኘት" የገቡ የሐይማኖት ተጓዦች እንደኾኑ የጠቀሱት የወረዳው ባለሥልጣናት፣ ኛንጋቶም ብሄረሰብ ከኡጋንዳ የፈለሰ ነው የሚል አፈ ታሪክ መኖሩንም ተናግረዋል ተብሏል። ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር፣ ኡጋንዳዊያኑ "የምጽዓት ቀንን የሸሹ" መኾናቸውን ማረጋገጡን ትናንት ተናግሮ ነበር።

5፤ አሜሪካ የሱማሌላንድ ራስ ገዝ መንግሥት ወታደሮቹን የግጭት ቀጠና ከሆነችው ላስ አኖድ ከተማ እንዲያስወጣ ጠይቃለች። መንግሥትን የሚፋለሙ የላስ አኖድ የጎሳ ሚሊሻዎችም፣ በመንግሥት ኃይሎች ላይ ጥቃት ከማድረስ እንዲቆጠቡ አሜሪካ አሳስባለች። ሁለቱ ወገኖች ግጭቱን አብርደው ቀደም ሲል የተደረሰውን ተኩስ አቁም እንዲያከብሩ የጠየቀችው አሜሪካ፣ ሰብዓዊ ቀውሱ እንዳይባባስ ተፋላሚ ወገኖች በንግግር ግጭቱን መፍታት አለባቸው ብላለች። ባለፈው ኅዳር መካሄድ የነበረበት የሱማሌላንድ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ መዘግየቱ እንዳሳሰባትም አሜሪካ የገለጠች ሲሆን፣ የፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ መንግሥት ምርጫው የሚካሄድበትን የጊዜ መርሃ ግብር እንዲያሳውቅ ጥሪ አድርጋለች።

6፤ የዓለማቀፉ ወንጀል ፍርድ ቤት መመስረቻ ስምምነት ፈራሚዋ ደቡብ አፍሪካ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቱን ለ"ብሪክስ" አገራት የመሪዎች ጉባኤ ሲሄዱ እንደምታስተናግዳቸው ዛሬ በውጭ ጉዳይ ሚንስትሯ ናለዲ ፓንዶር በኩል አስታውቃለች። የዓለማቀፉ ወንጀል ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ፑቲን በዩክሬን "የጦር ወንጀል ፈጽመዋል" በማለት የእስር ማዘዣ ማውጣቱን ተከትሎ፣ በቀጣዩ ነሐሴ የ"ብሪክስ" አገራት የመሪዎች ጉባኤ አዘጋጇ ደቡብ አፍሪካ አቋሟ ምን እንደሚኾን በጉጉት ሲጠበቅ ነበር። ደቡብ አፍሪካና ሩሲያ በሌሎች አገራት ግፊት በድንገት ጠላት ሊኾኑ አይችሉም ያሉት ፓንዶር፣ ፑቲንን በጉባኤው እንዲገኙ እንደተጋበዙ ተናግረዋል። በዓለማቀፉ ፍርድ ቤት ስምምነት መሠረት፣ ደቡብ አፍሪካ ፑቲን ግዛቷን ከተረገጡ አስራ ለፍርድ ቤቱ የማስረከብ ግዴታ አለባት። "ብሪክስ" በፍጥነት በማደግ ላይ ያሉት ኃያላኑ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሩሲያ፣ ቻይና፣ ሕንድና ብራዚል የመሠረቱተ ቡድን ነው።

7፤ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 53 ብር ከ9017 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 54 ብር ከ9808 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 63 ብር ከ5330 ሳንቲም እና መሸጫው 64 ብር ከ8037 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ58 ብር ከ5545 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ59 ብር ከ7256 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። አንድ የቻይና ዩዋን ደሞ በ7 ብር ከ0868 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ7 ብር ከ2285 ሳንቲም ተሽጧል ተብሏል። #ሼር በማድረግ ተባበሩኝ


ወሳኝ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ቻናሉን ይቀላቀሉ

                                   @emsmereja