Get Mystery Box with random crypto!

ሰኞ ማለዳ! መጋቢት 18/2015 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች 1. የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከናይጀሪያ | Zemedkun Bekele (ዘመዴ)

ሰኞ ማለዳ! መጋቢት 18/2015 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች

1. የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከናይጀሪያ አየር መንገድ ጋር በፈጠረው ስምምነት መሠረት ከበረራ ውጭ የሆነውን የናይጀሪያ አየር መንገድ መልሶ በማቋቋም በመጭው ግንቦት በረራ ሊያስጀምር መሆኑን የአገሪቱ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። አዲስ በሚቋቋመው የናይጀሪያ አየር መንገድ ውስጥ፣ የኢትዮጵያ አዩር መንገድ 49 በመቶ፣ ናይጀሪያዊያን ባለሃብቶች 46 በመቶ እንዲሁም የናይጀሪያ መንግሥት ቀሪውን 5 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ እንዲይዙ ስምምነት ላይ እንደተደረሰ ዘገባዎቹ ጠቅሰዋል። አየር መንገዱን እንደገና በረራ ለማስጀመር የታቀደው፣ በ23 አውሮፕላኖች እንደሆነ ተገልጧል። የናይጀሪያ አየር መንገድ ከባድ ሙስና ባደረሰበት ኪሳራ ሳቦያ፣ ከበረራ ውጭ የሆነው ከ20 ዓመት በፊት ነበር።

2፤ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባ አገረ ስብከት የካቲት 23 ቀን በፒያሳው ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ላይ አስለቃሽ ጭስ የተኮሱ አካላት አጣርቶ ለሕዝብ ይፋ የሚያደርግ የሕግ ባለሙያዎች ቡድን ማቋቋሙን አስታውቋል። አገረ ስብከቱ፣ በአዲሱ ሸገር ከተማ ስር ከተካለሉ ቤተክርስቲያናት መካከል መንግሥት በግብረ ኃይሉ ያስፈረሰውን አንድ የጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን በራሱ ወጭ መልሶ እንዲያስገነባም አሳስቧል። አገረ ስብከቱ ጨምሮም፣ በቤተክርስቲያናት ላይ የሚፈጸመው "አድሏዊ" እና "ኢ-ሕገመንግሥታዊ" ድርጊት እንዲቆም ጠይቋል።

3፤ ብሄራዊ ባንክ ሦስት አዳዲስ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን መንደፉን ሪፖርተር አስነብቧል። ማሻሻያዎቹ የባንኩን ተቋማዊ ነጻነትና የቁጥጥር ሥልጣን በማጠናከር፣ የሰው ኃይልና ዲጂታል አቅሙን በማሳደግና የገንዘብ ፖሊሲውን በማሻሻል ላይ ያተኮሩ እንደሆኑ ዘገባው ጠቅሷል። የባንኩ ገዥ ማሞ ምኅረቱ፣ በሦስት ዓመታት ውስጥ 70 በመቶ ኢትዮጵያዊያን ለባንኩ የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽ እንዲኾኑ ግብ እንደተያዘ መጋቢት 14 ቀን በተካሄደ አንድ መድረክ ላይ መናገራቸውን ዘገባው ጠቅሷል። ብሄራዊ ባንክ ለሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ኩባንያ የሞባይል ገንዘብ ዝውውር ፍቃድ በቅርቡ እንደሚሰጥም ማሞ ተናግረዋል ተብሏል።

4፤ በሜጀር ጀኔራል ተስፋዬ አያሌው የተመራ የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት የከፍተኛ መኮንኖች ልዑክ ቅዳሜ'ለት በማዕከላዊ ሱማሊያ የሒራን ግዛት ከተማ በለደወይን መግባቱን የሱማሊያ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት ልዑክ ወደ ሱማሊያ ያቀናው፣ የሱማሊያ መንግሥት በአልሸባብ ላይ ሁለተኛውን ዙር የማጥቃት ዘመቻ በሚያውጅበት ዋዜማ ላይ ነው። ልዑኩ ከሱማሊያ ጦር ሠራዊት አቻዎቹ ጋር እንደሚወያይና፣ ኢትዮጵያ በቅርቡ ወደ ሱማሊያ ያዘመተቻቸው ቁጥራቸው ያልተገለጹ ወታደሮች ከአልሸባብ ጋር ለመዋጋት ያላቸውን ዝግጁነት እንደሚገመግም ዘገባዎቹ አመልክተዋል። ከልዑካን ቡድኑ ጋር የተወሰኑ የሱማሌ ክልል ባለሥልጣናት አብረው ተጉዘዋል ተብሏል።

5፤ የሱዳን ወታደራዊ መሪዎችና ሲቪል ተቃዋሚ የፖለቲካ ኃይሎች ትናንት ምሽት በዓለማቀፍ አደራዳሪዎች አማካኝነት ባደረጉት ስብሰባ ላይ የመጨረሻው የሲቪል ሽግግር መንግሥት ማቋቋሚያ ረቂቅ ሰነድ ተጠናቆ መቅረቡን የሱዳን ዜና ወኪል ዘግቧል። በስምምነት ረቂቅ ሰነዱ ላይ ገና በድርድር ላይ ያለው የጸጥታ መዋቅር ማሻሻያ ከታከለበት በኋላ፣ መጋቢት 23 እንደሚፈረም ዘገባው ጠቅሷል። ተሰብሳቢዎቹ፣ የመጀመሪያውን የፖለቲካ ማዕቀፍ ስምምነት ያልፈረሙ ኃይሎች የፖለቲካ ንግግር ሂደቱን ተቀላቅለው የመጨረሻውን ስምምነት እንዲፈርሙ ጥሪ ማድረጋቸው ተገልጧል። የስምምነት ማዕቀፉ አካል ያልሆኑት ቡድኖች ግን፣ ለፊርማ የተቃረበውን የሲቪል መንግሥት ማቋቋሚያ ሰነድ እንደማይቀበሉት በመግለጽ ላይ ናቸው። #ሼርርር በማድረግ ተባበሩን


ወሳኝ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ቻናሉን ይቀላቀሉ

                                   @emsmereja