Get Mystery Box with random crypto!

ማለዳ! ቅዳሜ መጋቢት 9/2015 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች 1፤ የሕወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ የፓርቲው ቃ | Zemedkun Bekele (ዘመዴ)

ማለዳ! ቅዳሜ መጋቢት 9/2015 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች

1፤ የሕወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ የፓርቲው ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት እንዲሆኑ ማጨቱን ቪኦኤ ዘግቧል። ሕወሃት የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ ካዋቀረ በኋላ፣ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር በሚያደርጋቸው ድርድር መዋቅሩ መጽደቅ ይጠበቅበታል። የትግራይ ዓለማቀፍ ምሁራን ማኅበር ለጊዜያዊ አስተዳደሩ ምክትል ፕሬዝዳንት ዕጩ እንድጠቁም በቀረበልኝ ጥያቄ መሠረት፣ ጡረተኛውን ጀኔራል ጻድቃን ገ/ተንሳይን እጩ አድርጌ አቅርቤያለሁ ማለቱ ይታወሳል። በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የሚቋቋመው፣ ፕሪቶሪያ ላይ በፌደራል መንግሥቱና ሕወሃት መካከል በተደረሰው የሰላም ስምምነት መሠረት ነው።

2፤ የገዥው ብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሰሞኑን ያካሄደውን ስብሰባ አስመልክቶ ትናንት ማምሻውን ባወጣው መግለጫ፣ የፓርቲው ባለሥልጣናት ከጥላቻና ከግጭት ቀስቃሽ ንግግሮችና ድርጊቶች እንዲቆጠቡ አሳስቧል። ምሁራን፣ የሐይማኖት አባቶች፣ መገናኛ ብዙኀን፣ የማኅበረሰብ አንቂዎችም፣ ከጥላቻና ግጭት አባባሽ እንዲሁም የአገርን ሰላምና ደኅንነት ለአደጋ ከሚያጋልጡ ንግግሮች እንዲቆጠቡ ያሳሰበው ፓርቲው፣ የፍትህና ጸጥታ አካላትም እንዲህ ዓይነት ድርጊቶችን በቸልተኝነት እንዳይመለከቱ ጠይቋል። ፓርቲው አገሪቱ የገጠሟትን ችግሮች በዝርዝር መመርመሩን ገልጦ፣ ከዋና ዋና ችግሮች መካከል የታሪክ እዳዎች፣ የነጻነት አያያዝ ችግሮችና የኑሮ ውድነት ተጠቃሽ እንደሆኑ አብራርቷል።

3፤ የጉሙዝ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ የታሠሩ 46 አባላቱ መፈታታቸውን መናገሩን ዶይቸቨለ ዘግቧል። ሆኖም በመተከልና ካማሺ ዞኖች ከተከሰተው ግጭት ጋር በተያያዘ የታሠሩ አባላቱ በሙሉ አለመፈታታቸውን ፓርቲው መግለጡን ዘገባው አመልክቷል። ንቅናቄው ከስድስት ወር በፊት ትጥቁን ፈትቶ በሰላማዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ ከክልሉ መንግሥት ጋር በፈረመው የሰላም ስምምነት መሠረት፣ ሦስት ሺህ የቀድሞ ታጣቂዎቹ ከማኅበረሰቡ ጋር መቀላቀላቸውን የንቅናቄው ሊቀመንበር ግራኝ ጉታ ተናግረዋል ተብሏል። የክልሉ ፖሊስ በበኩሉ፣ የሰው ሕይወት በማጥፋት ከተጠረጠሩት ውጭ ሌሎቹ በሙሉ ፕፈታሉ ማለታቸውን ዜና ምንጩ ጠቅሷል። ምርጫ ቦርድ የሰረዝኩትን የንቅናቄውን የሕጋዊ የፓርቲነት ፍቃድ መልሼ ሰጥቻለሁ ማለቱ ይታወሳል።

4፤ ባይደዋ ከተማ ላይ በብሄራዊ ጉዳዮች ላይ ምክክር ያደረጉት የሱማሊያ ፌደራል መንግሥት እና የፌደራል ግዛቶች መንግሥታት ስምምነት ላይ መድረሳቸውን በጋራ ባወጡት መግለጫ መግለጣቸውን የአገሪቱ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። የበይነ መንግሥታት ምክክሩ ያተኮረው፣ የአገሪቱን ተቋማት በማጠናከር፣ የጸጥታ መዋቅር ማሻሻያ በማድረግ እና የፋይናንስ ሥልጣኖችን ያልተማከሉ በማድረግ አስፈላጊነት ላይ ነው። በብሄራዊ ምክክሩ ላይ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሞሐመድ እና የፌደራል ግዛቶች ፕሬዝዳንቶች የተሳተፉ ሲሆን፣ የፑንትላንድ ራስ ገዝ ፕሬዝዳንት አብዱላሂ ደኒ ግን እንዳልተሳተፉ ተገልጧል። ፑንትላንድ በምክክሩ አለመሳተፏ አሳሳቢ መሆኑን የገለጸው መግለጫው፣ ምክንያቱን ለማወቅ ወደ ፑንትላንድ ኮሚቴ እንዲላክ ተወስኗል ብሏል።

5፤ ዓለማቀፉ የነፍስ አድን ድርጅት አይ አር ሲ የዩክሬን የእህል ምርት በጥቁር ባሕር በኩል ለዓለም ገበያ እንዲቀርብ ባለፈው ሐምሌ የተደረሰው ስምምነት ካልታደሰ በምሥራቅ አፍሪካ የ40 ሚሊዮን ሰዎች ሕይወት አደጋ ላይ ይወድቃል በማለት አስጠንቅቋል። ተመድ ስምምነቱ ለአንድ ዓመት እንዲታደስ እንዲያደርግ ድርጅቱ ጠይቋል። ከስምምነቱ ወዲህ በጥቁር ባሕር በኩል ወደ ውጭው ዓለም ከወጣው የዩክሬን የምግብ እህል ውስጥ፣ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ሱማሊያ፣ የመን እና አፍጋኒስታን የደረሰው 10 በመቶው ብቻ እንደሆነ ድርጅቱ ገልጧል። ሩሲያ ስምምነቱ ለሁለት ወራት ብቻ እንዲታደስ ሃሳብ አቅርባለች። በተመድና ቱርክ አደራዳሪነት ሩሲያና ዩክሬን የደረሱበት ስምምነት ባለፈው ኅዳር አንድ ጊዜ የታደሰ ሲሆን፣ ቀነ ገደብም ዛሬ ይጠናቀቃል። #share ይደረግ

ወሳኝ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ቻናሉን ይቀላቀሉ

                                   @emsmereja