2023-04-11 20:22:21
«ዩኒቨርሲቲውን ወደሚፈለገው የዕድገት ደረጃ ለማሻገር በተቀናጀ አግባብ ምቹ ሁኔታዎችን ወደ መልካም ውጤት መቀየር ተገቢ ነው።» ፕ/ር ታከለ ታደሰ-የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት
በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ ተቋማዊ የምክክር መድረክ በዛሬው ዕለት ተካሂዷል።
____
የዩኒቨርሲቲው ምክር ቤት አባላት፣ መምህራን እና የቴክኒክ ሰራተኞች፣ የመምህራን ማህበር አመራሮች እንዲሁም የተማሪዎች ሕብረት አመራሮች በምክክር መድርኩ ተሳትፈዋል።
በመድረኩ የዩኒቨርሲቲው የ2015 በጀት አመት የ6 ወር የስራ አፈጻጸም ሪፖርት እንዲሁም የመምህራን ማህበር የ2015 በጀት አመት የሥራ እቅድ ቀርቦ ከተሳታፊዎች ጋር ውይይት ተካሂዷል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ፕ/ር ታከለ ታደሰ የተቋሙን የ2015 በጀት አመት የ6 ወር የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን፤ አመራርና አስተዳደርን ከማጠናከር እንዲሁም ተቋማዊ የማስፈፀም አቅምን ከማጎልበት ረገድ ሠፊ ስራ መሰራቱን አብራርተዋል።
አዲሱ የሰው ሀይል አደረጃጀት መዋቅር ተሰርቶና በሲቭል ሰርቪስ ኮሚሽን ፀድቆ የተላከ መሆኑን ፕዝሬዳንቱ ገልጸው፤ ለትግበራ ተገቢው ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል ሲሉም አሳውቀዋል።
የኦዲትና የህግ የበላይነትን ለማስከበር የተሰሩ ተግባራትን ፕሬዝዳንቱ ሲያብራሩ፡ “በ2013 በጀት ዓመት በኦዲት ውጤቶች ላይ የድርጊት መርሃ ግብር ተዘጋጅቶ የማስተካከያ እና የእርምት እርምጃ እየተወሰደ ይገኛል” ብለዋል።
ሰላማዊ መማር መስተማርን ለማረጋገጥና ለማዝለቅ ባለፉት 6 ወራት፡ የውስጥ ተጋላጭነትን የመቀነስ፥ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት የመስራት፥ የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ እና የተደራጀ ችግር ፈቺ የክትትል እና ድጋፍ ሥራ የተሰራ መሆኑንም ፕ/ር ታከለ ጠቁመዋል።
የትምህርት ጥራት፣ አግባብነት፣ ፍትሐዊነት፣ ተደራሽነት እንዲሁም የመምህራንን ብቃትን ከማረጋገጥ ረገድ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ተከናውኗል ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ ባለፉት 6 ወራት 24 ያህል የአካዳሚክ ፕሮግራሞችን የማስፋፋት ስራ ተጀምሯል ብለዋል።
የመዉጫ ፈተና ዝግጅትን በተመለከተ፡ ግብረ-ኃይል በማቋቋምና የድርጊት መርሀ ግብር በማዘጋጀት መጠነ ሰፊ የቅድመ ዝግጅት ስራ መሰራቱን ፕ/ር ታከለ ገልጸው ፤ችግር ፈቺ የክትትልና ድጋፍ ሥራ በተቀናጀ አግባብ እየተሰራ እንደሆነም አመላክተዋል።
የምርምር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የፈጠራ ስራዎች ተደራሽነት፣ ጥራት እና ፍትሀዊነትን ከማሳደግ ረገድ ውጤታማ ስራ መሰራቱን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፤ የምርምር፥ ማኅበረሰብ አገልግሎትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ተግባራት የትኩረት መስክና የፕሮጄክቶቹን የወደፊት ተጠባቂ ውጤት መሰረት በማድረግ ተፈጻሚ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በአረንጓዴ አሻራ ዙሪያ የተከናወኑ ተግባራት አፈጻጸምን ፕሬዝዳንቱ ሲያብራሩ፡ “አሻራችን ለትውልዳችን በሚል መሪ ቃል” 15 ሺህ አቮካዶ ችግኝ በአንድ ጀምበር መተከሉን ገልጸው፤ በቀጣይ የክረምት ወራት ለተከላ እንዲውል 330 ሺሕ የአቮካዶ ፍሬ እየፈላ ይገኛል ብለዋል።
በዩኒቨርሲቲው መሰረተ ልማት፣ ፋሲሊቲንና የዲጂታል ክህሎት ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ከማሻሻል ረገድ መጠነ ሰፊ ስራ የተከናወነ መሆኑን ፕ/ር ታከለ ገልጸው፤ በመሠረተ ልማት ዙሪያ የሚከናወኑ ተግባራት የበለጠ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።
አደረጃጀቶችን በማጠናከር ሰላማዊ መማር ማስተማር መቀጠሉ፤ የውስጥ አቅምን በመጠቀም ከፍተኛ ወጪዎችን መቀነሱ፤ ከሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ትስስር በመፍጠር ሀብት ማመንጨት መቻሉ፤ የድጋፍ፥ ክትትልና ግምገማ ሥርዓትን በማጠናከር የመልካም አስተዳደር ችግሮች መፈታት መቻሉ በመልካም ተሞክሮነት ተገልጿል።
ሰላማዊ መማር ማስተማር ሂደት ማረጋገጥና ማዝለቅ፤ የትምህርት ጥራትና ተገቢነትን ማረጋገጥ (የመውጫ ፈተና)፤ የመሠረተ ልማትና ግንባታ ፕሮጄክቶች አፈፃፀም ማሻሻል፤ የሃብት አስተዳደርና ተጠያቂነት ማስፈን (የኦዲት ግኝቶችን በፍጥነት ማረም)፤ ለመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በወቅቱ ምላሽ መስጠት፤ አዲሱን የሰው ሀይል አደረጃጀት መዋቅር ስራ ላይ ማዋል፤ ከምርምር ተቋማትና ኢንዱስትሪዎች ጋር ትስስር ማጠናከር እንዲሁም የተደራጀና ችግር ፈቺ የክትትልና ድጋፍ ሥራ መስራት በቀጣይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ይተገበራል ሲሉም ፕ/ር ታከለ አሳውቀዋል።
ዩኒቨርሲቲው በርካታ የሰለጠነ የሰው ኃይል፣ የተትረፈረፈ ሀብት እንዲሁም ሕጋዊ የሆነ የአስተዳደር ስርዓት እንዳለው የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፤እንደ ተቋም ዩኒቨርሲቲውን ወደሚፈለገው የዕድገት ደረጃ ለማሻገር በተቀናጀ አግባብ ምቹ ሁኔታዎችን ወደ መልካም ውጤት መቀየር ተገቢ ነው” ብለዋል።
የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ማህበር ፕሬዝዳንት መምህር ደጉ መና የማህበሩን የ2015 በጀት አመት የሥራ እቅድ በመድረኩ አቅርበዋል።
የመርሃ ግብሩ ተሳታፊዎችም በቀረቡ ሰነዶች ላይ በጥልቀት በመወያየት ሀሳብ አስተያየት የሰጡ ሲሆን፤ በመድረኩ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ተሰጥቶ መርሃ ግብሩ ተጠናቋል።
ዕውቀትን በተግባር!!
የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት
2.3K viewsedited 17:22